1በዚያም ወራት የፈርዖን ልጅ ተርሙት በወንዝ ትታጠብ ዘንድ ወጣች። ስታለቅስም ቃልህን ሰምታ ያመጡህ ዘንድ ደንገጥሮችዋን አዘዘች። ወደ እርስዋም አመጡህ፤ ከሣጥንም አወጣችህ፤ ራራችልህም። 2እኅትህም፥ “ከዕብራውያት ወገን ይህን ሕፃን አጥብታ የምታሳድገው ሞግዚት ሄጄ ልጥራልሽ?” አለቻት። ሄዳም እናትህን ኢዮካብድን ጠራቻት፤ ደመወዝዋንም ሰጠቻት፤ አሳደገችህም። 3ከዚህም በኋላ ባደግህ ጊዜ ወደ ፈርዖን ቤት ወሰዱህ። ልጁም ሆንኸው። አባትህም አብራን መጽሐፍን አስተማረህ። 4ሦስቱንም ሱባዔ ከፈጸምህ በኋላ ወደ ቤተ መንግሥት አገባህ፥ ከቤተ መንግሥትም እስከምትወጣበት ወራት ድረስ ሦስት የዓመት ሱባዔ በቤተ መንግሥት ኖርህ። ከእስራኤል ልጆች ወገን የሚሆን ጓደኛህን ዕብራዊውንም ሲደበድበው ግብፃዊውን አየኸው፤ ገድለህም በአሸዋ ውስጥ ቀበርኸው። 5በሁለተኛውም ቀን ከእስራኤል ልጆች ወገን ሁለት ሰዎች ሲጣሉ አገኘህ። በደለኛውንም፥ “ወንድምህን ለምን ትመታዋለህ?” አልኸው። ፈጽሞም ተቈጣ፥ “በእኛ ላይ አለቃና ፈራጅ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ወይስ ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ትገድለኝ ዘንድ ትወዳለህን?” አለህ። 6ከዚህም ነገር መገለጥ የተነሣ ፈርተህ ሸሸህ። 7በአርባ ዘጠነኛው ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ በስድሰተኛው ዓመት ወደዚያ ሄድህ፤ ስድስት ሱባዔ ከአንድ ዓመትም ተቀመጥህ። በዳግመኛው ሱባዔም በሁለተኛው ዓመት ወደ ግብፅ ተመለስህ፤ ይኸውም ኀምሳ ኢዮቤልዩ ነው። 8በደብረ ሲና የተናገረህን አንተ ታውቃለህ፤ ወደ ግብፅ በተመለስህ ጊዜ በጎዳና በዳስ በዓል ቀን ገዢው መስቴማ ከአንተ ጋር ምን ሊያደርግ ወደደ? በፍጹም ኀይሉ ይገድልህ ዘንድ አይደለምን? 9በግብፃውያንም በቀልንና ፍርድን ታደርግ ዘንድ እንደ ተላክህ ባየህ ጊዜ ግብፃውያንን ከእጅህ ያድናቸው ዘንድ የወደደ አይደለምን? ከእጁም አዳንሁህ፤ በግብፅም በፈርዖንና በቤተ ሰቡ ሁሉ ላይ፥ በባሪያዎቹና በሕዝቡም ላይ በእውነት ታደርግ ዘንድ በተላክህበት ተአምራትንና ድንቅን አደረግህ። 10እግዚአብሔርም ስለ እስራኤል በእነርሱ ጽኑ በቀልን አደረገ። በደምና በጓጉንቸር፥ በትንኝና በውሻ ዝንብ፥ በክፉ ቍስልና በሚፈላ ደዌ ሥጋ ፈጽሞ አጠፋቸው። 11ከብቶቻቸውንም በሞትና በበረድ ድንጋይ አጠፋ፤ አዝመራቸውንም በዚህ ሁሉ አጠፋ። ከበረድ የቀረውንም ቀሪውን በሚበላ አንበጣ አጠፋ። በጨለማ፥ በሰውና በከብት በኵር፥ በጣዖቶቻቸውም ሁሉ እግዚአብሔር በቀልን አደረገ። በእሳትም አቃጠላቸው፤ ሳይደረግም ታደርግ ዘንድ ሁሉ በአንተ እጅ ተላከ። 12የግብፅንም ንጉሥ በአገልጋዮቹ ሁሉ ፊትና በሕዝቡ ፊት ትናገረው ነበርህ። ሁሉም በቃልህ ተደረገ። ታላላቆችና ክፉዎች ዐሥሩ መቅሠፍቶች ለእስራኤል በቀልን ትመልስለት ዘንድ በግብፅ ሀገር መጡ። እግዚአብሔርም ስለ እስራኤል ሁሉን አደረገ። በግፍ እንደ ገዙአቸው በእነዚያ ላይ በቀልን ይመልስ ዘንድ ከአብርሃም ጋር መሐላን እንደ ተማማለበት ፈቃዱ አደረገ። 13ገዢው መስቴማ በፊትህ ይከራከርህ ነበር፥ በፈርዖንም እጅ ይጥልህ ዘንድ ይወድ ነበር፥ የግብፅንም ሰዎች በምዋርታቸው ይረዳቸው ነበር። ይቃወምላቸውም ነበር። በፊትህም ክፉ ሥራ ይሠሩ ነበር። በፊትህም ክፉ ሥራን ይሠሩ ዘንድ ተውናቸው። ድኅነት ግን በእጃቸው ይደረግ ዘንድ አልፈቀድንላቸውም። እግዚአብሔርም በክፉ ቍስል አጠፋቸው፤ አንድ ተአምራትን ስንኳ ምንም ከማድረግ አሳጥተናቸዋልና መቃወም ተሳናቸው። 14ግብፃውያንም በሠራዊቶቻቸው ሁሉ፥ በፈረሶቻቸውና በሰረገላዎቻቸው፥ በግብፅም ሠራዊት ሁሉ ብዛት ከአንተ በኋላ ይከተሉ ዘንድ እስኪበረታና ለግብፃውያን እስኪያሰማቸው ድረስ ደርሶ፥ ገዥ መስቴማ በተአምራትና በድንቅ ሁሉ አላፈረም። 15እኔም በአንተና በግብፃውያን መካከል በእስራኤልም መካከል ቆምሁ። እስራኤልንም ከእጁና ከሠራዊቱ እጅ አዳንናቸው። 16እግዚአብሔርም እንደ ደረቅ ምድር በባሕር መካከል አሻገራቸው። እስራኤልንም ይከተሉ ዘንድ ያወጣቸውን ወገኖች ሁሉ የግብፅ ሰዎች የእስራኤልን ልጆች በባሕር እንደ ጣሉ፥ አምላካችን እግዚአብሔር በባሕር መካከል ከእስራኤል ልጆች በታች በወንዙ ጥልቅ ጣላቸው። ዐሥር እልፍ ጊዜ በቀልን ተበቀላቸው። ከእስራኤል ልጆች ወገን በፈሳሽ መካከል ስለ ጣሉት ስለሚጠባ አንድ ሕፃን ፋንታም በሦስት ወገን የሚመክቱ ሺህ አርበኞችን ተበቀላቸው። 17በዐሥራ አራተኛውና በዐሥራ አምስተኛው፥ በዐሥራ ስድስተኛውና በዐሥራ ሰባተኛው፥ በዐሥራ ስምንተኛውም ቀን ገዢው መስቴማ እንዳይጣላቸው ከእስራኤል ልጆች በኋላ ታስሮ ተግዞ ነበር። 18በዐሥራ ዘጠነኛው ቀን ግን የግብጽን ሰዎች ይረዱአቸው ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች ይከተሉ ዘንድ አሰናበትናቸው። ልቡናቸውንም አጸና፥ አበረታቸውም፤ ግብፃውያንንም ያጠፋቸው ዘንድ፥ በባሕርም መካከል ይጥላቸው ዘንድ በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ ታሰበ። 19ከግብፅ ሰዎች ልብስንና ገንዘብን፥ የብሩን ዕቃና፥ የወርቁን ዕቃ፥ የናሱንም ዕቃ በሚጠይቁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች እንዳይጣላቸው፥ በግፍም ስለ ገዙአቸው ፋንታ ይማርኩአቸው ዘንድ በዐሥራ አራተኛው ቀን አሰርነው። የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ ባዶአቸውን አላወጣናቸውም። 20መጀመሪያው ወር በባተ በዐሥራ አራተኛው ቀን ገና ሳይመሽ ትሠዋው ዘንድ፥ በዐሥራ አምስተኛውም ቀን ማታ ፀሐይ ከሚገባበት ጊዜ ጀምሮ በሌሊት ይበሉት ዘንድ እግዚአብሔር ስለ ፋሲካው ያዘዘህን ትእዛዝ ዐስብ፤ ይህችም ሌሊት የበዓል መጀመሪያ ናት፤ የፋሲካም መጀመሪያ ናት። 21እናንተም በግብፅ የፋሲካ በዓል አድርጋችሁ ትበሉ ዘንድ ትቀመጣላችሁ፤ የመስቴማ ሠራዊትም ሁሉ በግብፅ ሀገር ከፈርዖን በኵር ጀምሮ ተማርካ በወፍጮ ሥር እሰከምታገለግል ባሪያ በኵር ድረስ የበኵር ልጁን ይገድል ዘንድ፤ ከብቱንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ተላከ። 22በበሩ የደም ምልክት አለና በቤት ያሉ ሰዎች ሁሉ ይድኑ ዘንድ ሠራዊቱ አልፈው ይሄዳሉ እንጂ ዓመት የሆነውን የበግ ደም በበሩ ወዳዩበት ቤት ለመግደል እንዳይገቡ እግዚአብሔር የሰጣቸው ምልክት ይህች ናት። 23የእግዚአብሔርም ሠራዊት ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው መጠን ሁሉን አደረጉ። ከእስራኤልም ልጆች ሁሉ አልፈው ሄዱ። ከከብት ጀምሮ እስከ ሰው ድረስ፥ እስከ ውሻም ድረስ ከእነርሱ ሰውን ሁሉ ለማጥፋት መቅሠፍት ወደ እስራኤል አልገባም። 24መቅሠፍቱም በግብፅ እጅግ ጽኑ ሆነ፤ በግብፅም በድን፥ ልቅሶና ጩኸት በውስጡ የሌለበት ቤት አልነበረም፤ እስራኤል ሁሉ ግን ተቀምጦ የፋሲካውን ሥጋ እየበላና ወይኑን እየጠጣ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ያመሰግንና ይባርክ ነበር። ከጽኑ አገዛዝና ክፉ ከምትሆን ከግብፅም ለመውጣት ተዘጋጅቶ ነበር። 25አንተም ባለ በዘመንህ ሁሉ ይህችን ቀን ዐስብ፤ ከአንዱ ዘመን እስከ አንዱ ዘመን በሕይወት በኖርህበት ዘመን ሁሉ እንደ ሥርዐቱ ሁሉ በዕለቱ በዓመት አንድ ጊዜ አድርጋት። 26የዘለዓለም ሥርዐት ነውና ከቀን ቀንን፥ ከወርም ወርን አታስተላልፍ። በየዓመቱ ሁሉ ከዓመት አንድ ቀን በየትውልዳቸው ሁሉ ዕለቱን በዓል ያደርጉት ዘንድ በእስራኤል ልጆች ላይ ሥርዐት እንደ ሆነ በሰማይ ጽላት ተጽፏል። የዘለዓለም ሥርዐት ነውና የተወሰነ ዘመንም የለውም። 27ሰው ንጹሕ ሆኖ ሳለ በጊዜው በዕለቱ ያደርገው ዘንድ በዓሉ በሚከበርባት ቀን እግዚአብሔር ወድዶ የሚቀበለውን ቍርባን ለማቅረብ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ለመብላትና ለመጠጣት ባይመጣ የእግዚአብሔርን ቍርባን በጊዜው አላቀረበምና ንጹሕ የሆነው፥ ሀገሩም ቅርብ የሆነው ያ ሰው ይጥፋ። ያም ሰው ለራሱ የኀጢአቱን ፍዳ ይቀበላል። ቀኑ ሁለቱ እጅ ለብርሃን፥ ሦስቱ እጅ ለጨለማ ተሰጥቶአልና፥ መጀመሪያው ወር በባተ በዐሥራ አራተኛው ቀን በምሽቱ መካከል ከቀኑ ሦስተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ሌሊቱ ሦስተኛ ክፍል ድረስ የእስራኤል ልጆች መጥተው ከቀኑ በጊዜው በዓል ያድርጉ። 28በምሽቶች መካከል በዓል ታደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ሥርዐት ይህ ነው። የሚሠዋበትም በምሽቱ ወሰን ጊዜ ይሁን እንጂ በብርሃኑ ጊዜ ሁሉ አይሁን። እስከ ሌሊቱ ማግሥት ድረስ ማታ ጊዜ ይብሉት። ከሌሊቱ ማግሥት፥ ከዚያም በኋላ የተረፈውን ሥጋ ሁሉ በእሳት ያቃጥሉት። 29በእሳት ጠብሰው አብስለው ይብሉት እንጂ ቅቅሉንና ብርንዶውን አይብሉት። ከእግሩና ከሆድ ዕቃውም ጋር ራሱን በማስተንተን በእሳት ይጥበሱት። ከእስራኤልም ልጆች ምንም የሚሰበር ሰውነት የለምና ከእርሱ የሚሰበር አጥንት አይኑር። 30ስለዚህ ነገር በጊዜው ጊዜ ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች አዘዛቸው። ከእርሱም ምንም አጥንትን መስበር አይኑር። የበዓል ቀን ናትና፥ የታዘዘችም ቀን ናትና፥ በዓል የሚደረግባትም ቀን ስለ ሆነች ከእርስዋ ከቀን ወደ ቀን፥ ከወርም ወደ ወር መተላለፍ የለምና።