1ያዕቆብ ከልጆቹ ጋር ከግብፅ ምድር በምትሻለው በጌሴም ምድር ኖረ። ያዕቆብም ወደ ግብፅ በገባ ጊዜ የመቶ ሠላሳ ዓመት ሰው ነበረ። 2ዮሴፍም ለአባቱና ለወንድሞቹ ለቤተሰቦቻቸውም ለሰባቱ የራብ ዓመት የሚበቃ ምግብን ሰጣቸው። ከራቡ ጽናት የተነሣም የግብፅ ምድር ተጨነቀች። 3ዮሴፍም መላዋን የግብፅ ምድርን በእህል ምክንያት ለፈርዖን እጅ አደረጋት። ሰውንና ከብቱን፥ ሁሉንም ለፈርዖን ገንዘብ አደረገ። የራቡም ዘመን ተፈጸመ። 4ዮሴፍ በስምንተኛው ዓመት ዘር ይዘሩ ዘንድ በግብፅ ላሉ ሰዎች ዘርንና ምግብን ሰጠ። ፈሳሹ በግብፅ ሀገር ሁሉ መልቶአልና፥ በሰባቱ የራብ ዐመታት በወንዝ አጠገብ ካሉ ከጥቂቶች ቦታዎች በቀር አያጠጣም ነበርና። 5ዛሬ ግን ወንዙ መልቶአል፤ የግብፅ ሰዎችም ምድሩን ዘሩ፤ ምድርም በዚያ ዓመት ብዙ ስንዴን አፈራች። ያም ዓመት የአርባ አምስተኛው ኢዮቤልዩ የአራተኛው ሱባዔ መጀመሪያ ነው። 6ዮሴፍም ከዘሩት እህል አምስተኛውን እጅ ወስዶ ለንጉሥ አገባ። አራቱንም እጅ ለዘርና ለምግብ ሊሆናቸው ተወላቸው። ዮሴፍም እስከዚህ ቀን ድረስ ለግብፅ ሀገር ሰዎች ይህን ሥርዐት አደረገላቸው። 7ያዕቆብም በግብፅ ሀገር ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ። የኖረባቸውም ዓመታት ሁሉ ሦስት ኢዮቤልዩ ሆኑ፥ ሦስት ኢዮቤልዩም መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነው። በአርባ አምስተኛው ኢዮቤልዩ በአምስተኛው ሱባዔ በአራተኛው ዓመት ሞተ። 8ያዕቆብም ሳይሞት ልጆቹን መረቃቸው። በግብፅ ሀገር የሚያገኛቸውን ሁሉ፥ በኋለኛውም ዘመን በእነርሱ ላይ የሚመጣባቸውን ሁሉ ነገራቸው፤ መረቃቸውም። 9ለዮሴፍም በምድር ላይ ሁለት ዕጣ ሰጠው። እንደ አባቶቹም አንቀላፋ። በከነዓንም ሀገር ደርብነት ባላት ዋሻ በአባቱ በአብርሃም አጠገብ ተቀበረ። ይኸውም በከነዓን ሀገር ደርብነት ባላት ዋሻ ለራሱ በቈፈራት መቃብር ነው። የእርሱን መጽሐፎችና የአባቶቹን መጽሐፎች ሁሉ እስከዚህ ቀን ድረስ ለልጆቹ ይጠብቃቸውና ያድሳቸው ዘንድ ለልጁ ለሌዊ ሰጠው። 10ያዕቆብም ከሞተ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የእስራኤል ልጆች በግብፅ ሀገር በዙ፤ ብዙ ወገንም ሆኑ። ወንድም ወንድሙን ይወድ ዘንድ፥ ባልንጀራም ከባልንጀራው ጋር ይረዳዳ ዘንድ ሁሉም በልቡናቸው የተካከሉ ሆኑ። 11ዮሴፍም በኖረበት ዘመን ሁሉ በዐሥሩ የሱባዔ ዓመታት እጅግ በጣም በዙ። ዮሴፍም በኖረበት ዘመን ሁሉ የእስራኤልን ልጆች የግብፅ ሰዎች ሁሉ ያከብሩአቸው ነበረና አባቱ ያዕቆብ ከሞተ በኋላ ዮሴፍ በኖረበት በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ባላጋራ አልነበረም፤ ምንም ክፉ አልነበረም። 12ዮሴፍም የመቶ ዐሥር ዓመት ሰው ሲሆን ሞተ፤ በከነዓን ምድር ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ዐሥር ዓመት ሲያገለግል ኖረ፥ ሦስት ዓመት በግዞት ቤት ኖረ፤ ሰማንያ ዓመት ከንጉሥ በታች ሆኖ የግብፅን ሀገር ሁሉ እየገዛ ኖረ። ሞተም፤ ወንድሞቹም ሁሉ ሞቱ። ያችም ትውልድ ሁላ ሞተች። 13ከግብፅም በሚወጡበት ወራት ዓፅሙን ይወስዱ ዘንድ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች አዘዛቸው። የግብፅ ሰዎች ዕለቱን አውጥተው ዳግመኛ በከነዓን ሀገር እንደማይቀብሩት ዐውቆአልና ስለ ዓፅሙ አማላቸው። የከነዓን ንጉሥ መምከሮን አሱር በሚባል ሀገር ሲኖር ከግብፅ ንጉሥ ጋር በቆላ ተዋግቶአልና፥ በዚያም ገድሎታልና። 14እስከ ኤርሞንም በር ድረስ ግብፃውያንን አሳደደ፤ በግብፅም ሁለተኛ ሌላ ንጉሥ ነግሦአልና መግባት ተሳነው፤ ከእርሱም ይልቅ በርትቶአልና ወደ ከነዓን ሀገር ተመለሰ፤ የግብፅ በሮችም ተዘጉ፤ ወደ ግብፅም የሚወጣና የሚገባ አልነበረም። 15ዮሴፍም በአርባ ሰባት ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ በሁለተኛው ዓመት ሞተ። በግብፅም ሀገር ቀበሩት፤ ከእርሱም በኋላ ወንድሞቹ ሁሉ ሞቱ። 16በአርባ ሰባተኛው ኢዮቤልዩ በሁለተኛው ሱባዔ በሁለተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ከከነዓን ንጉሥ ጋር ይዋጋ ዘንድ ወጣ። 17የእስራኤልም ልጆች ከዮሴፍ ዓፅም በቀር የያዕቆብን ልጆች ዓፅሞች ሁሉ በምድረ በዳ በተራራ ላይ ባለች ደርብነት ባላት ዋሻ ቀበሩ። 18ብዙ ሰዎችም ወደ ግብፅ ተመለሱ፤ ከእነርሱም ጥቂት ሰዎች በኬብሮን ቀሩ፤ አባትህ አብራንም ከእነርሱ ጋር ቀረ። 19የከነዓን ንጉሥ የግብፅን ንጉሥ ድል ነሣው። 20የግብፅንም ሰዎች እንዲህ አላቸው፥ “የእስራኤል ልጆች ከእኛ እነሆ፥ ፈጽመው በዙ፤ ሳይበዙም እንጠበብባቸው፤ ጦርነትም ሳይመጣብን፥ እነርሱም ሳይወጉን በአገዛዝ መከራ እናጽናባቸው፤ ይህ ካልሆነ ግን እነርሱ ከጠላቶቻችን ጋር አንድ ሆነው ይወጉናል፤ ልቡናቸውና ፊታቸውም ወደ ከነዓን ነውና ከምድራችን ይወጣሉ።” 21በሥራም መከራ ያጸኑባቸው ዘንድ፥ የሠራተኛ አለቆችን ሾመባቸው፤ አዘዙአቸውም። ለፈርዖንም ፊጦምና ራሚስ የሚባሉ ጽኑ አንባዎችን ሠሩ። በግብፅም ሀገር ቅጥሩንና የፈረሰውን ግንብ ሁሉ ሠሩ። በግፍም ይገዙአቸው ነበር። ነገር ግን ክፉ ነገር የሚያደርጉባቸውን ያህል እንደዚሁ ፈጽመው ይበዙ ነበር። የግብፅም ሰዎች የእስራኤልን ልጆች ይጸየፉአቸው ነበር። 22በአርባ ሰባተኛው ኢዮቤልዩ በሰባተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት አባትህ ከከነዓን መጣ፤ በአርባ ስምንተኛው ኢዮቤልዩ በአራተኛው ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት ተወለድህ፤ ይኸውም በእስራኤል ልጆች ላይ መከራ የጸናበት ዘመን ነው። 23የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም የተወለደውን ወንድ ልጃቸውን ሁሉ ወደ ባሕር ይጥሉ ዘንድ በእነርሱ ላይ ትእዛዝን አዘዘ። 24አንተም እስክትወለድ ድረስ ሰባት ወር ልጆቻቸውን ሲጥሉ ኖሩ። እናትህም ሦስት ወር ሸሸገችህ። ለእርስዋም ነገሩአት። ሣጥንም አሠራችልህ፥ በሙጫና አደሮ ማርም ለበጠችው፥ በወንዙም ዳር በፊላ ሣር ውስጥ አኖረችው። በውስጡም ሰባት ቀን አኖረችህ፥ እናትህም በሌሊት እየመጣች ታጠባህ ነበር፥ እኅትህ ማርያምም በቀን ከአሞራዎች ትጠብቅህ ነበር።