1ይቀር ዘንድ፥ ወይም ይወርድ ዘንድ ራእይ ያይ እንደ ሆነ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጠ። ከከረመውም ስንዴ የመጀመሪያውን ፍሬ በዓል አደረገ። 2በአውሬዎችና በከብቶች፥ በወፎችና በሰዎች ሁሉ ድርቅ ስለ ሆነ ከከነዓን ሀገር ሁሉ በምድር የሚዘሩት ምንም እፍኝ ሙሉ ዘር አልነበረምና። 3በዐሥራ ስድስተኛውም ቀን እግዚአብሔር ተገለጠለት፥ “ያዕቆብ፥ ያዕቆብ” ብሎ ጠራው። ያዕቆብም፥ “እነሆ፥ አለሁ” አለ። እርሱም አለው፥ “የአባቶችህ የአብርሃምና የይስሐቅ አምላክ እኔ ነኝ። በዚያ ብዙ ወገን አደርግሃለሁና ወደ ግብፅ መውረድን አትፍራ፤ እኔ ከአንተ ጋር እወርዳለሁ። እኔም እወስድሃለሁ፥ በዚያችም ምድር ትቀበራለህ። 4ዮሴፍም እጁን በዐይኖችህ ላይ ያኖራል፤ አትፍራ፤ ወደ ግብፅም ውረድ።” 5ያዕቆብም ተነሣ፤ ልጆቹና የልጅ ልጆቹም ተነሡ፤ አባታቸውንና ጓዛቸውንም በሰረገላ ጫኑ። 6በዚህ በሦስተኛው ወር በዐሥራ ስድስተኛው ቀን ያዕቆብ ከዐዘቅተ መሐላ ተነሥቶ ወደ ግብፅ ሄደ። 7ያዕቆብም ከእርሱ አስቀድሞ የጌሼምን ምድር ይጐበኝ ዘንድ ልጁን ይሁዳን ወደ ልጁ ዮሴፍላከ። ለእርሱ አቅራቢያ ይሆኑ ዘንድ፥ በዚያ ሊኖሩ እንዲመጡ ዮሴፍ ነግሮአቸዋልና። 8ይህችውም በግብፅ ምድር መልካም ነበረች። ለእርሱም ቅርብ ነበረች፥ ለእስራኤልና ለከብቶቻቸውም የተመቸች ነበረች። 9ከአባታቸው ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የወረዱ የያዕቆብ ልጆች ስማቸው ይህ ነው። የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል ነው። የልጆቹም ስማቸው ኤኖክ፥ ፋሉስ፥ ኤስሮም፥ ከርሚ፥ ከእርሱ ጋር እነዚህ አምስቱ ናቸው። 10ስምዖንና ልጆቹ፥ የልጆቹም ስማቸው ይህ ነው። ኢሙኤል፥ ኢያሚን፥ አዕዎት፥ ኢያኪም፥ ሳዖር፥ የስፍንስዋቅ ልጅ ሳውል፥ ከእርሱ ጋር እነዚህ ሰባቱ ናቸው። 11ሌዊና ልጆቹ፥ የልጆቹም ስም ይህ ነው። ጌድሶር፥ ቀዓት፥ ሜራሪ፥ እኒህ አራቱ ናቸው። 12ይሁዳና ልጆቹ፥ የልጆቹም ስም ሴሎም፥ ፋሬስ፥ ዛራ፥ እሊህ አራቱ ናቸው። 13ይሳኮርና ልጆቹ፥ የልጆቹም ስም ይህ ነው። ቶላ፥ ፉኣ፥ ኢያስብ፥ ሳምሮን፥ እኒህ አምስቱ ናቸው። 14ዛብሎንና ልጆቹ፥ የልጆቹም ስም ይህ ነው። ሳኦር፥ 15የያዕቆብ ልጆች፥ ልጆቻቸውም እነዚህ ናቸው፤ በመስጴጦምያ ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ስድስት ናቸው። አንዲቱ እኅታቸው ዲና ናት። ከልያ የተወለዱ ልጆች ሁሉ ከአባታቸው ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የወረዱ ልጆቻቸውም ሃያ ዘጠኝ ናቸው። አባታቸው ያዕቆብም ከእነርሱ ጋር ተቈጥሮ ሠላሳ ሆኑ። 16የያዕቆብ ሚስት የልያ አገልጋይ ዘለፋ ለያዕቆብ የወለደችለት ልጆች ጋድና አሴር ናቸው። ከእነርሱ ጋር ወደ ግብፅ የወረዱት የልጆቻቸውም ስም ይህ ነው። 17የጋድ ልጆች ሳፍዮን፥ አሐዲ፥ 18የአሴርም ልጆች፥ ኢያምና፥ ይሱአ፥ በርያ አንዲት እኅታቸውም ሣራ ናቸው። እነዚህ አምስቱ ናቸው። 19የዘለፋም ልጆች ዐሥራ አራት ናቸው። የልያም ሁሉ አርባ አራት ሆኑ። 20የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች ዮሴፍና ብንያም ናቸው። አባቱ ወደ ግብፅ ሳይወርድ ለዮሴፍ በግብፅ ልጆች ተወለዱለት። የኤልዮጶሊስ ካህን የሚሆን የፋጢፋራ ልጅ አስኔት የወለደችለት ምናሴና ኤፍሬም ናቸው።፥ እነዚህ ሦስቱ ናቸው። 21የብንያምም ልጆች ላውባኤል፥ አስቤል፥ ጎአው፥ ንዕማን፥ አብሮድዮ፥ ራኤፍስ፥ ያኒማ፥ አፊም፥ የአም፥ ጋዐም፥ 22ዳንና ንፍታሌምን የወለደችለት የያዕቆብ ሚስት የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆች እነዚህ ናቸው። ከእነርሱ ጋር ወደ ግብፅ የወረዱት የልጆቻቸውም ስም ይህ ነው። 23የዳን ልጆች ኩሲም፥ ሰሞን፥ አሱድ፥ ኢያሳክ፥ ሰሎሞን ናቸው፥ እኒህ ስድስቱ ናቸው። በገቡበት ዓመት በግብፅ ሞቱ። ለዳንም ኩሲም ብቻ ተረፈለት። 24የንፍታሌምም ልጆች ስማቸው ይህ ነው። ኢያስኤል፥ ገሀን፥ አስዓር፥ ያኩም፥ አው ናቸው፤ ከረሃቡ ዘመን በኋላ የተወለደ አው በግብፅ ሞተ። የራሔል ሰዎች ሁሉ ሃያ ሰባት ሆኑ፥ ወደ ግብፅ የወረዱ የያዕቆብ ልጆች ሁሉ ሰባ ሰዎች ናቸው። 25እንግዲህ እነዚህ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ሁሉ ሰባ ናቸው። ሚስትም ሳያገቡ በግብፅ የሞቱት አምስት ናቸው፤ ልጅም አልነበራቸውም። 26የይሁዳ ሁለቱ ልጆቹ ኤርና አውናን በከነዓን ሀገር ሞቱበት፥ ልጅም አልነበራቸውም፤ የሞቱትንም የእስራኤል ልጆች ቀበሩአቸው። እነዚህም ወገኖች ከሰባው ሰዎች ጋር ተቈጠሩ። 27ያዕቆብም በአርባ አምስተኛው ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ በሁለተኛው ዓመት በአራተኛው ወር መባቻ ወደ ግብፅ ወደ ጌሴም ምድር ገባ። 28ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብን ይቀበል ዘንድ ወደ ጌሴም ምድር መጣ። የአባቱንም አንገት አቅፎ አለቀሰ። ያዕቆብም ዮሴፍን፥ “አይችሃለሁና እንግዲህ ወዲህ ልሙት” አለው። 29“አሁንም ከአገልጋዩ ከያዕቆብ ምሕረቱንና ይቅርታውን ያላራቀ የእስራኤል አምላክ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ ይመስገን፤ በቤቴል ያየሁት ራእይ እውነተኛ ሕልም ነውና እኔ በሕይወት ፊትህን ማየቴ ለእኔ ታላቅ ነው፤ አምላኬ እግዚአብሔር ለዘለዓለሙ ይመስገን፤ ስሙም የተመሰገነ ነው” አለ። 30ዮሴፍና ወንድሞቹ በአባታቸው ፊት እንጀራን በሉ፤ ወይንንም ጠጡ፤ ያዕቆብም ዮሴፍን ከወንድሞቹ ጋር በፊቱ ሲበላና ሲጠጣ አይቶታልና ፈጽሞ ደስ አለው። እርሱን የጠበቀውን፥ ዐሥራ ሁለቱን ልጆቹንም የጠበቀለትን፥ የሁሉን ፈጣሪ አመሰገነው። 31ዮሴፍም በጌሴም ምድርና በራምሴ በፈርዖን ፊት እነርሱ በሚገዙት በአውራጃዋም ሁሉ ይኖሩ ዘንድ ለአባቱ ገንዘብ ሰጠው፤ ለወንድሞቹም ሰጣቸው።