1ዮሴፍም እርስ በርሳቸው የደኅንነትና የሰላም ዐሳብ እንዳላቸው፥ ያም ባይሆን የጠብ ዐሳብ እንዳላቸው፥ ዐሳባቸውን ያውቅ ዘንድ ዐሰበ። 2በቤቱ ላይ የተሾመውንም ሹም፥ “በአቅማዳቸው ሁሉ እህልን ምላላቸው፥ ወርቃቸውንም በየአቅማዳቸው አድርግላቸው፤ የምጠጣበትንም የብሩን ጽዋ በታናሹ ልጅ አቅማዳ አድርገህ ስደዳቸው” አለው። 3እርሱም ዮሴፍ እንዳዘዘው አደረገ። በየአቅማዳውም እህሉን ሁሉ መላ፥ ወርቃቸውንም በየአቅማዳቸው ጨመረላቸው። የብሩንም ጽዋ በብንያም አቅማዳ ጨመረ፤ በነጋም ጊዜ ፈጥነው ሄዱ። 4ከዚያም በወጡ ጊዜ እንዲህ ሆነ። ዮሴፍ በቤቱ የተሾመውን ሹም፥ “ፈጥነህ ተከተላቸው፦ በጎ ነገርን ስላደረግሁላችሁ ፋንታ ክፉ ነገር ከፈላችሁኝ፤ ጌታዬም የሚጠጣበትን የብር ጽዋ ሰረቃችሁኝ ብለህ ተከራክረህ ታናሽ ወንድማቸውን መልስልኝ፥ ወደ አደባባይ ሳልወጣ ፈጥነህ አምጣው” አለው። 5በኋላቸውም ፈጥኖ ተከትሎ እንዲህ ባለ ነገር ተናገራቸው። እነርሱም አሉት፥ “ለእኛ ለባሪያዎችህ እንዲህ ያለ ነገር አግባባቸው አይደለም። ይህን ነገር አያደርጉም፤ ከጌታህም ቤት ምንም ገንዘብ አይሰርቁም። 6እኛ ባሪያዎችህ ቀድሞ በአቅማዳችን ያገኘነውን ወርቃችንን ስንኳ ከከነዓን መልሰናል፥ እንዴት ገንዘብ እንሰርቃለን? እነሆ፥ እኛም አለን፤ አቅማዳችንም አለ፤ በርብር። 7ከእኛም ጽዋውን ያገኘህበት አንዱ ሰው ይገደል፤ እኛም አህዮቻችንም ለጌታህ እንገዛ።” 8እርሱም አላቸው፥ “ነገሩ እንዲህ አይደለም፤ ጽዋውን ያገኘሁበትን ሰው እርሱን ብቻ ይዤ አገልጋይ አደርገዋለሁ፤ 9እናንተ ግን በሰላም ወደ ቤታችሁ ተመለሱ።” 10ገንዘባቸውንም ሲበረብር ከትልቁ ጀምሮ በታናሹ ጨረሰ፤ በታናሹም በብንያም አቅማዳ ተገኘ። ደንግጠውም ልብሶቻቸውን ቀደዱ። አህዮቻቸውንም ጭነው ወደ ከተማ ተመለሱ። ወደ ዮሴፍም ቤት ደረሱ። ሁሉም በግንባራቸው በምድር ላይ ተደፍተው ሰገዱለት። 11ዮሴፍም፥ “ክፉ አደረጋችሁ” አላቸው። እነርሱም አሉ፥ “ምን እንናገራለን? ምንስ እንመልሳለን? አንተ ጌታችን የእኛን የአገልጋዮችህን በደል አገኘህብን፤ 12እነሆ፥ እኛ ለጌታችን ባሪያዎች ነን፤ አህዮቻችንም ለአንተ ናቸው።” 13ዮሴፍም አላቸው፥ “እኔስ እግዚአብሔርን እፈራለሁ፤ እናንተም ወደ ሀገራችሁ ሂዱ፥ ክፉ ሥራ ሠርቶአልና ወንድማችሁ ብቻ ተገዢ ይሁን፤ ሰው ጽዋውን እንደሚወድ፥ እኔም በዚህ ጽዋ እንደምጠጣ አታውቁምን? እርሱንም ሰረቃችሁኝ።” 14ይሁዳም አለ፥ “ጌታዬ፥ አንተ በጆሮህ እየሰማህ አንድ ቃል ልናገር። የዚህ የአገልጋይህ እናት ለአባታችን ሁለት ልጆች ወለደች፤ አንዱ ወጥቶ ጠፋ፤ ያገኘውም የለም፤ ይህ ግን ለእናቱ እርሱ ብቻ ቀርቶአል። 15አገልጋይህ አባታችንም ይወደዋል። ልቡናውም ከዚህ ከልጁ ልቡና ጋር የታሰረች ናት። ወደ ባሪያህ ወደ አባታችን ብንሄድ፥ ይህም ሕፃን ከእኛ ጋር ካልሄደ ይሞታል። 16ለሞት እስኪደርስ ድረስ አባታችንን በኀዘን እንገድላለን። ነገር ግን እኔ አገልጋይህ ስለዚህ ልጅ ፋንታ ለጌታዬ ተገዥ ሆኜ ልኑር፤ ልጁም ከወንድሞቹ ጋር ይሂድ። ከአገልጋይህ አባታችን እጅ ዋስ ሆኜ አምጥቼዋለሁና እኔ አገልጋይህ መልሼ ባልወስደው በዘመኑ ሁሉ አባታችንን እበድላለሁ።” 17ዮሴፍም የሁሉ ልቡና አንዱ ከአንዱ ጋር በበጎ ነገር እኩል እንደ ሆነ ባየ ጊዜ መታገሥ ተሳነው። 18እርሱም ዮሴፍ እንደ ሆነ ነገራቸው፥ በዕብራይስጥም ቋንቋ ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ። አንገታቸውንም አቅፎ አለቀሰ። እነርሱ ግን አላወቁትም ነበር፤ እነርሱም ያለቅሱ ጀመር። 19እርሱም አላቸው “በእኔ አታልቅሱ፥ አባቴን ፈጥናችሁ ወደ እኔ አምጡት፤ ሳልሞትም አባቴን ልየው፥ የወንድሜ የብንያምም ዐይኖች እያዩ ልየው። ይህ የራቡ ዘመን እነሆ፥ ሁለተኛ ዓመት ነው። ገናም አምስት ዓመት አለ፤ አዝመራ የለም፥ የእንጨት ፍሬም የለም፥ እርሻም የለም። እናንተም ከጓዛችሁ ጋር ፈጥናችሁ ኑ፤ በራብም አትሙቱ። ስለ ጓዛችሁም አትጨነቁ። 20ብዙ ወገኖች ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር እኔን አስቀድሞ ለማዘጋጀት ልኮኛልና። እኔም ገና በሕይወት እንዳለሁ ለአባቴ ንገሩት። 21ለፈርዖን እንደ አባቱ እሆን ዘንድ፥ በቤቱና በግብፅ ሀገርም ሁሉ እሠለጥን ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ሾመኝ እነሆ፥ እናንተ ታያላችሁ። 22ለአባቴም፦ ጌትነቴን ሁሉ፥ እግዚአብሔርም የሰጠኝን ብልጽግናና ክብርን ሁሉ ንገሩት።” 23በፈርዖንም ትእዛዝ ለመንገድ ሰረገላዎችንና ስንቅን ሰጣቸው። ለሁሉም አራት ኅብር ያለው ልብስና ብርን ሰጣቸው። ለአባታቸውም ልብስና ብርን፥ ስንዴ የሚወስዱባቸውንም ዐሥር አህዮች ላከ። አሰናበታቸውም። 24ወጥተውም ለአባታቸው፥ ዮሴፍ በሕይወት እንደ አለ፥ በምድር ላሉ አሕዛብ ሁሉ ስንዴን እንደሚሰፍር፥ በግብፅ ሀገር ሁሉም ላይ እንደ ሠለጠነ ነገሩት። 25አባታቸው ግን ልቡናው ደንግጦአልና አላመናቸውም። 26ከዚህ በኋላ ዮሴፍ የላከለትን ሰረገላዎች አይቶ ሰውነቱ እንደ ገና ታደሰ። 27እርሱም አለ፥ “ይህ ለእኔ ታላቅ ነው። ዮሴፍ ሕያው ነውና ሳልሞት ወርጄ ልየው” አለ። 28ያዕቆብም በሦስተኛው ወር መባቻ ከከንዓን ከቤቱ ተነሥቶ በቤርሳቤህ ጎዳና ሄደ። በዚህም ወር በሰባተኛው ቀን ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ መሥዋዕትን ሠዋ። 29ያዕቆብም በቤቴል ያየውን ሕልም ዐሰበ፥ ወደ ግብፅ መውረድንም ፈራ። ዮሴፍ ወደ እርሱ እንዲመጣ እርሱም ወደ ግበፅ እንዳይወርድ ይልክበት ዘንድ ሲያስብ ሰነበተ።