1ይሁዳም ከምራቱ ጋር ተኝቶአልና የሠራው ሥራ ክፉ እንደ ሆነ ዐወቀ። በዐይኖቹ ፊት ራሱን አዋረደ። የልጁንም ኀፍረት ገልጦአልና እንደ በደለና እንደ ሳተ ዐወቀ። 2ስለ በደሉም በእግዚአብሔር ፊት ያዝንና ይለምን ጀመር። 3ፈጽሞም ስለ ለመነና ስለ አለቀሰ እንዲሰረይለት በሕልም ነገርነው። ከዚህም በኋላ ኀጢአት አልሠራም። ከኀጢአቱና ከአለማወቁ ተመልሶአልና ስርየት ሆነለት። 4በአምላካችን ፊት በድሎአልና፥ እንዲህ የሚያደርግን ሰው ሁሉ፥ ከምራቱም ጋር የሚተኛን ሰው ሁሉ ይቃጠልበት ዘንድ በእሳት ያቃጥሉት። በእነርሱ ኀጢአትና በደል ሆኖአልና ስለዚህ ነገር በእሳት ያቃጥሉአቸው። 5አንተም፥ “በመካከላቸው ርኵሰትና ኀጢአት እንዳይሆን የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ ከምራቱና ከአማቱ ጋር የሚተኛ ሁሉ ርኵሰትን አድርጎአልና ከእርስዋ ጋር የተኛውን ሰው ሴቲቱንም በእሳት ያቃጥሉ።” 6ቍጣውና መቅሠፍቱም ከእስራኤል ይርቃል። 7ለይሁዳም ሁለቱ ልጆቹ ከእርስዋ ጋር እንዳልተኙ ነገርነው፤ ስለዚህም ዘሩ ለሌላ ነገድ ሆነ። 8ለልጆቹ ከአዘዛቸው ከአብርሃም ፍርድ የተነሣ ይሁዳ በእሳት ያቃጥሉአት ዘንድ ወድዶአልና፥ በልበ ቅንነትም ሄዶአልና፥ ፍርድንም መርምሮአልና አልጠፉም። 9በአርባ አምስተኛው ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት በምድሩ ላይ ድርቅ ይመጣ ጀመር። 10ዝናብም በምድር መዝነቡን ተወ። ምንም የሚወርድ አልነበረምና። ምድርም ድርቅ ሆነች። በግብፅ ምድር ግን ምግብ ነበር፤ አዝመራ በሆነበት በሰባቱ ዓመት ዮሴፍ የግብፅን እህል ሰብስቦ ጠብቆት ነበርና። 11የግብፅ ሰዎችም ምግባቸውን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ ዮሴፍ መጡ። እርሱም የመጀመሪያው ዓመት ስንዴ ያለበትን ጎተራ ከፍቶ ለሀገሩ ሕዝብ በወርቅ ሸጠ። 12ያዕቆብም በግብፅ እህል እንዳለ ሰማ። ከግብፅም እህል ሸምተው ያመጡለት ዘንድ ዐሥሩን ልጆቹን ላከ። 13ብንያምን ግን አልላከውም። ወደ ግብፅ ከሚሄድ ነጋዴ ጋር ደረሱ። ዮሴፍም ዐወቃቸው፤ እነርሱ ግን አላወቁትም፤ ከእነርሱም ጋር ተነጋገረ። እንዲህም ብሎ ጠየቃቸው፥ “እናንተ ሰላዮች አይደላችሁምን? የሀገሩንም መግቢያ ትሰልሉ ዘንድ መጥታችኋል።” አሰራቸውም። 14ከዚህ በኋላ ፈታቸው፤ ስምዖንንም ብቻ አስቀረ። ዘጠኙ ወንድሞቹንም በአቅማዳቸው ስንዴውን ሞልቶ ሰደዳቸው። ወርቃቸውንም በአቅማዳቸው ጨመረላቸው፤ እነርሱ ግን አላወቁም። 15አባታቸው በሕይወት እንደ አለ፥ ታናሽ ወንድማቸውም እንደ አለ ነግረውታልና ታናሽ ወንድማቸውን ያመጡ ዘንድ አዘዛቸው። 16ከግብፅ ሀገርም ወጥተው ወደ ከነዓን ምድር ደረሱ፤ ያገኛቸውንም ነገር ሁሉ ፥ የሀገሩ ገዢ ከእነርሱ ጋር ጭንቅ ነገርን እንደ ተናገረ፥ ብንያምንም እስኪያመጡ ድረስ ስምዖንን መያዣ አድርጎ እንደ አስቀረው ለአባታቸው ነገሩት። 17ያዕቆብም አላቸው፥ “የወላድ መካን አደረጋችሁኝ፥ ዮሴፍ የለ፥ ስምዖን የለ፥ ብንያምንም ትወስዱብኝ ነውን? ክፋታችሁ በእኔ ደረሰ፤ ልጄ ከእናንተ ጋር አይሄድም። 18እናታቸው ሁለት ልጆች ወልዳ ነበርና አንዱ ሞተ፤ ይህንም ትወስዱብኝ ነውን? በመንገድ ታሞ ቢሞት ያረጀ ሰውነቴን በኀዘን ወደ መቃብር ታወርዳላችሁን?” አላቸው። ወርቃቸው ሁሉ ተቋጥሮ እንደ ተመለሰ አይቶአልና ስለዚህ ነገር እርሱን መላክ ፈራ። 19ከግብፅ ሰዎች ብዙዎች ዮሴፍ ብዙ እህልን እንደሚሰበስብ፥ ለረኃቡም ዓመት በጎተራ እንደሚያስቀምጥና እንደሚጠብቅ ካዩት ጀምሮ ለምግብ እህላቸውን ሰብስበዋልና ከግብፅ በቀር በከነዓንና በምድር ሁሉ ራቡ ፈጽሞ ጸና። 20የግብፅ ሰዎችም በመጀመሪያው የራብ ዓመት ተመገቡት። 21ያዕቆብም በምድር ረኃብ እጅግ እንደ ጸና፥ መዳንም እንደ ሌለ ባየ ጊዜ ልጆቹን፥ “እንዳንሞት ወደ ግብፅ ሄዳችሁ እህል ሸምታችሁ አምጡልን” አላቸው። እነርሱም፥ “ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ካልሄደ አንሄድም” አሉት። 22ያዕቆብም ብንያምን ከእነርሱ ጋር ካልሰደደው ከራቡ የተነሣ ሁሉም እንደሚጠፉ ዐሰበ፥ ሮቤልም፥ “እርሱን በእጄ ስጠኝ፤ መልሼ ባላመጣልህ ስለ እርሱ ፋንታ ሁለቱን ልጆችን ግደላቸው” አለው። 23እርሱም፥ “ከአንተ ጋር አይሄድም” አለው። ይሁዳም ቀርቦ፥ “ከእኔ ጋር ስደደው፤ መልሼ ባላመጣልህም በሕይወት ዘመኔ ሁሉ በፊትህ በደለኛ ልሁን” አለ። 24በዚህ ሱባዔ በሁለተኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር መባቻ ከእነርሱ ጋር ሰደደው፤ ከሚሄዱትም ሁሉ ጋር ወደ ግብፅ ደረሱ። ከእነርሱም ጋር እጅ መንሻቸው ልባንጃ፥ ለውዝ፥ ጠርቤንቶስና የማር ወለላ በእጃቸው ነበር። 25ደርሰውም በዮሴፍ ፊት ቆሙ። ወንድሙን ብንያምንም ባየው ጊዜ ዐወቀው። 26“ትንሽ ወንድማችሁ ይህ ነውን?” አላቸው። እነርሱም፥ “አዎን፥ ነው” አሉት። እርሱም፥ “ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይጠብቅህ” አለው፥ ወደ ቤቱም ሰደዳቸው፤ ስምዖንንም አወጣላቸው። 27ግብርም አገባላቸው፥ በእጃቸውም ያመጡትን እጅ መንሻቸውን አቀረቡለት። በፊቱም በሉ፤ ለሁሉም ፋንታ ፋንታቸውን ሰጣቸው። ከሁሉም ፋንታ ይልቅ የብንያም ፋንታ ሰባት እጅ በለጠ። በሉ፥ ጠጡም፥ ሄደውም አህዮቻቸው ባሉበት ዐደሩ።