1በዚያም ወራት ፈርዖን በምድር ሁሉ ስለሚሆነው ጥጋብና ራብ በአንዲት ሌሊት ሁለት ሕልሞችን አየ። 2ከእንቅልፉም ነቃ፤ በግብፅ ያሉ ሕልም የሚተረጕሙትንና ጠንቋዮችን ሁሉ ጠርቶ ሁለቱን ሕልሞቹን ነገራቸው። ነገር ግን ሊተረጕሙ አልቻሉም። 3ከዚህም በኋላ የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ዮሴፍን አሰበው፤ የእርሱንም ነገር በንጉሡ ዘንድ ተናገረ። 4ከእስር ቤትም አወጡት። ሁለቱን ሕልምቹንም በፊቱ ተናገረ። 5እርሱም ሁለቱ ሕልሞቹ አንድ እንደ ሆኑ፥ በፈርዖን ፊት ተናገረ። 6እንዲህም አለው፥ “በግብፅ ሀገር ሁሉ ጥጋብ የሚሆንበት ሰባት ዓመት ይመጣል፤ ከዚህ በኋላ በሀገሩ ሁሉ ተመሳሳይ የሌለው ሰባት የራብ ዓመት ይመጣል፤ 7አሁንም የግብፅ ሰዎች ሁሉ ለፈርዖን ጎተራ ይሥሩ፤ ጥጋብ በሆነበት ዘመንም በሀገር የተገኘውን እህል ለሀገር ምግብ ሊሆን ያኑሩት፤ ሰባት ዓመት ራብ ለሚሆንበትም ዘመን ምግብ ይሆናል፤ ራቡም እጅግ የጸና ይሆናልና ከራብ ጽናት የተነሣ ሀገር አትጠፋም።” 8እግዚአብሔርም በፈርዖን ፊት ለዮሴፍ ባለምዋልነትንና ምሕረትን ሰጠው። 9ፈርዖንም ሹሞቹን፥ “የእግዚአብሔር መንፈስ አድሮበታልና እንደዚህ ሰው ያለ ብልህና ዐዋቂ ሰው አናገኝም” አላቸው። 10በመንግሥቱም ሁለተኛ ሰው አድርጎ ሾመው፤ የግብፅንም ሀገር ሁሉ አስገዛው፤ በፈርዖንም ሁለተኛ ሰረገላ ላይ አስቀመጠው፤ የነጭ ሐር ቀሚስም አለበሰው፤ በአንገቱም ዝርግፍ ወርቅ አሰረለት። 11“ኤል ኤል አብሪር” ብሎ በፊቱ ዐዋጅ ነገረለት፤ በእጁም የወርቅ ቀለበት አደረገለት፤ በቤቱ ሁሉ ላይ አሠለጠነው፤ ከፍ ከፍም አደረገው። እንዲህም አለው፥ “ከዙፋኔ ብቻ በቀር ከአንተ አልበልጥም።” 12ዮሴፍም በግብፅ ሀገር ሁሉ ሠለጠነ፤ የፈርዖንም መኳንንት ሁሉ ሹሞቹም ሁሉ፥ የንጉሡንም ሥራ የሚሠሩ ሁሉ ወደዱት፤ በቅንነት ይሔዳልና፥ ትዕቢትም የለውምና፥ ኵራት፥ ፊት አይቶም ማድላት የለውምና፥ መማለጃንም መቀበል የለውም ነበርና። በግብፅ ላሉ አሕዛብ ሁሉ በሚገባ ይፈርድላቸው ነበርና። 13የግብፅም ሀገር በዮሴፍ ምክንያት በፈርዖን ፊት ሰላም ሆነች። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር አለና። በፈርዖን ዘመዶች ሁሉ፥ በሚያውቁት ሰዎችም ሁሉ ፊት፥ ለእርሱም ምስክርነትን በሚሰጡ ሰዎች ፊት ባለምዋልነትንና ምሕረትን ሰጠው። የፈርዖንም መንግሥት ቀናች። ባለጋራ አልነበረም። ክፉም አልነበረም። 14ንጉሡም ዮሴፍን “ሰፋንጢፋንስ” ብሎ ጠራው። ለዮሴፍ ሚስት ትሆነው ዘንድ የእንጀራ አሳላፊዎች አለቃ የሚሆን የኤሌዮጲስ ካህን ልጅ የፋጢፋራንን ልጅ ሰጠው። 15ዮሴፍም በፈርዖን ፊት በቆመ ጊዜ የሠላሳ ዓመት ሰው ነበር። 16በዚያም ዓመት ይስሐቅ ሞተ። ስለ ሁለቱ ሕልሞች ትርጓሜ ዮሴፍ እንደ ተናገረው ደረሰ። 17በግብፅ ሀገር ሁሉ ሰባት ዓመት ጥጋብ ሆነ፤ የግብፅ ምድርም ብዙ ፍሬን አፈራች፤ አንዲቱ መስፈሪያ ሺህ ስምንት መቶ መስፈሪያ ሆነች። 18ዮሴፍም ስንዴው እስኪመላ ድረስ፥ ከብዛቱም የተነሣ መቍጠርና መስፈር እስኪሳናቸው ድረስ፥ የከተማውን ምግብ በየሀገሩ ሰበሰበ። 19በአርባ አምስተኛው ኢዮቤልዩ፥ በሁለተኛውም ሱባዔ፥ በሁለተኛው ዓመት፥ ይሁዳ ለበኵር ልጁ ለኤር ከአራም ልጆች ወገን ሚስትን አጋባው፤ ስምዋም ትእማር ይባላል። 20ጠላትም፥ ከእርስዋም ጋር አልተኛም፤ እናቱ ከከነዓን ልጆች ነበረችና፤ ከእናቱም ወገን ሚስትን ያገባ ዘንድ ወደደ፥ አባቱ ይሁዳ ግን አልፈቀደለትም። 21ያም የይሁዳ የበኵር ልጅ ኤር ክፉ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው። 22ይሁዳም ልጁን አውናንን አለው፥ “ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ፤ ዋርሳም አድርጋት። ለወንድምህም ዘር ተካለት።” 23አውናንም የእርሱ ልጅ እንደማይሆንና የወንድሙ ልጅ እንደሚሆን ዐወቀ፤ ወደ ወንድሙ ሚስትም ገባ። ነገር ግን ዘሩን በምድር ላይ ያፈስስ ነበር። ይህም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ፥ ቀሠፈውም። 24ይሁዳም ምራቱን ትእማርን፥ “ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ መበለት ሆነሽ በአባትሽ ቤት ተቀመጪ፤ ለእርሱም ሚስት ትሆኚው ዘንድ እሰጥሻለሁ” አላት። 25እርሱም አደገ፥ የይሁዳ ሚስት ቢድሱኤል ግን ያገባ ዘንድ ለልጅዋ ሴሎም አልፈቀደችም፤ የይሁዳ ሚስት ቢድሱኤልም በዚህ ሱባዔ በአምስተኛው ዓመት ሞተች። 26በስድስተኛው ዓመት ይሁዳ በጎቹን ይሸልት ዘንድ ወደ ቴምናታ ወጣ፤ ለትእማርም “እነሆ፥ አማትሽ በጎቹን ይሸልት ዘንድ ወደ ቴምናታ ይወጣል” ብለው ነገሩአት። 27የመበለትነቷንም ልብስ ትታ መጐናጸፊያዋን ለበሰች። አጊጣም በቴምናታ ጎዳና በር ተቀመጠች። 28ይሁዳም ሲሄድ አገኛት፥ ጋለሞታም እንደ ሆነች ተጠራጥሮ፥ “ወደ አንቺ ልግባ” አላት፤ እርሷም፥ “ግባ” አለችው፥ ገባም፥ እርስዋም፥ “ዋጋዬን ስጠኝ” አለችው። “በጣቴ ካለ ቀለበቴ፥ ከኵፍየቴና በእጄ ካለ ዘንጌ በቀር በእጄ የለኝም” አላት። 29እርስዋም፥ “ዋጋዬን እስክትሰድልኝ ድረስ እነርሱን ስጠኝ” አለችው፤ እርሱም፥ “አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። ለእርስዋም እነርሱን ሰጣት። 30እርስዋም ፀነሰችለት፤ ይሁዳም ወደ በጎቹ ሄደ፥ እርስዋም ወደ አባቷ ቤት ሄደች። 31ይሁዳም በበግ ጠባቂው በአዶላማዊው እጅ የፍየሉን ጠቦት ሰደደላት፤ እርሱም አጣትና፥ “በዚያ የነበረችው ጋለሞታ ወዴት አለች?” ብሎ የሀገሩን ሰዎች ጠየቃቸው፤ እነርሱም፥ “በዚህ ጋለሞታ የለችም፥ በእኛ ዘንድም ጋለሞታ የለችም” አሉት። 32ተመልሶም፥ “አጣኋት፥ የሀገሩንም ሰዎች ጠየቅኋቸው እነርሱም፦ በዚህስ ጋለሞታ የለችም አሉኝ” ብሎ ነገረው። 33እርሱም፥ “መዘባበቻ እንዳንሆን ተነሥ እንሂድ” አለው። ከዚህም በኋላ ሦስት ወር በሆናት ጊዜ እርስዋ እንደ ፀነሰች ታወቀች፤ ለይሁዳም፥ “እነሆ፥ ምራትህ ትእማር በዝሙት ፀነሰች” ብለው ነገሩት። 34ይሁዳም ወደ አባቷ ቤት ሄደ፥ እናቷንና አባቷን፥ ወንድሞችዋንም፥ “በእስራኤል ዘንድ ኀጢአት ሠርታለችና በእሳት ያቃጥሉአት ዘንድ አውጡአት” አላቸው። 35እንዲህም ሆነ፥ ያቃጥሉአት ዘንድ ባወጡአት ጊዜ፥ “ለእርሱ ፀንሻለሁና ይህ የማን እንደ ሆነ ዕወቅ ብላ ቀለበቱን፥ ኵፍየቱንና ዘንጉን ለአማቷ ላከች። 36ይሁዳም፥ “ትእማር ከእኔ ይልቅ እውነተኛ ሆነች፤ ከእንግዲህም አያቃጥሉአት” አለ። ስለዚህም ነገር ለሴሎም አልተሰጠችም። ከዚያም በኋላ ዳግመኛ አልቀረባትም። 37ከፀነሰችም በኋላ በዚህ በሁለተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት ሁለቱን ልጆች ፋሬስንና ዛራን ወለደች። 38ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ለፈርዖን የነገረው ሰባቱ የጥጋብ ዐመት ተፈጸመ።