1ከዚህም በኋላ እነዚያ የያዕቆብ ልጆች፥ ባሪያዎቻቸውም ተከፍለው በግንቡ በአራቱ ማዕዘን ወጡ። 2ይሁዳ በፊት ወጣ፤ ንፍታሌምና ጋድ፥ አምሳ ብላቴኖችም በግንቡ ደቡብ ከእርሱ ጋር ነበሩ። በፊታቸው ያገኙትን ሁሉ ገደሉ። ከእነርሱም አንድ ሰው ስንኳ ያመለጠ የለም። 3ሌዊ፥ ዳንና አሴር በግንቡ ምሥራቅ ወጡ፤ አምሳ ብላቴኖችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ። የሞዓብንና የአሞንንም ተዋጊዎች ገደሉ። 4ሮቤል፥ ይሳኮርና ዛብሎንም በግንቡ ሰሜን ወጡ፥ አምሳ ብላቴኖችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ፤ የፍልስጥኤምንም አርበኞች ገደሉ። 5ስምዖን፥ ብንያምና የሮቤል ልጅ ኤናክ በግንቡ ምዕራብ ወጡ፥ አምሳ ብላቴኖችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ። ከኤዶምና ከኮራውስ አራት መቶ ጠንካሮች ተዋጊዎች ሰዎችን ገደሉ። ስድስት መቶዎቹ ግን ሸሹ፤ አራቱ የዔሳው ልጆችም። 6አባታቸው በኮረብታው ላይ ሞቶ እንደ ወደቀ ትተውት ከእነርሱ ጋር ሸሹ። ይህችውም በአዱራም ያለች ኮረብታ ናት፤ የያዕቆብም ልጆች በኋላቸው ተከትለው እስከ ሴይር ተራራ ድረስ አሳደዱአቸው። 7ያዕቆብ ግን በአዱራም ኮረብታ ወንድሙን ቀብሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ። የያዕቆብ ልጆች የዔሳውን ልጆች በሴይር ተራራ አስጨነቁአቸው። ለያዕቆብ ልጆችም ተገዢዎች ይሆኑ ዘንድ አንገታቸውን ዝቅ አደረጉ። 8ከአነርሱም ጋር ሰላምን ያደርጉ እንደ ሆነ ይወጉአቸውም እንደ ሆነ፥ ወደ አባታቸው ላኩ። 9ያዕቆብም ሰላምን ያደርጉ ዘንድ ወደ ልጆቹ ላከ፤ ከእነርሱም ጋር ሰላምን አደረጉ። 10በዘመኑ ሁሉ ለያዕቆብና ለልጆቹ ይገብሩ ዘንድ የመገዛት ቀንበርን በእነርሱ ላይ አኖሩ። 11ያዕቆብ ወደ ግብፅ እስከሚወርድበት ቀን ድረስ ለያዕቆብ ሲገብሩ ኖሩ፤ የኤዶም ልጆችም፥ ዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች በእነርሱ ላይ ከሠሩት ከመገዛት ግብር እስከዚያች ቀን ድረስ አላጐደሉም። 12እስከዚያች ቀን ድረስ ለእስራኤል ልጆች ንጉሥ ሳይነግሥ በኤዶምያስ የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ናቸው። 13በኤዶምያስ የቢዖር ልጅ ባላቅ ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዲናባ ነበር፤ ባላቅም ሞተ። 14በእርሱም ፋንታ ከቦሶር ወገን የዛራ ልጅ ዮባብ ነገሠ። የዛራ ልጅ ዮባብም ሞተ። በእርሱም ፋንታ ከቴማን ሀገር አሳም ነገሠ፤ አሳምም ሞተ። 15በእርሱም ፋንታ በሞዓብ ምድረ በዳ የምድያምን ሰዎች የገደለ የባሬድ ልጅ አዶታ ነገሠ፤ የከተማውም ስም አውት ነበር። አዶታም ሞተ። 16በእርሱም ፋንታ ከአሜሴቅ ወገን ሰልማን ነገሠ። ሰልማንም ሞተ። በእርሱም ፋንታ ከሮባኦት ወንዝ የመጣ ሳኦል ነገሠ፤ ሳኦልም ሞተ። በእርሱም ፋንታ የአክቡር ልጅ ብዑሉናን ነገሠ፤ የአክቡር ልጅ ብዑሉናንም ሞተ። 17በእርሱም ፋንታ አዳት ነገሠ፤ የሚስቱ ስም ማየጦቢት ነበር፤ ይህችውም የሜትቤድዘብ ልጅ የመጥሪት ልጅ ናት። በኤዶምያስ ሀገር የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ናቸው። 18ያዕቆብም አባቱ ተሰዶ በኖረበት ያዕቆብ በተዛመዳቸው ሀገር በከነዓን ኖረ። 19ዮሴፍም የዐሥራ ሰባት ዓመት ልጅ ሳለ ወንድሞቹ ከሸጡት በኋላ ወደ ግብፅ አወረዱት። የፈርዖን ባለሙዋል የአዛዦች አለቃ ፋጢፋራን ገዛው። ዮሴፍንም በቤቱ ሁሉ ላይ ሾመው። 20በዮሴፍ ምክንያት የእግዚአብሔር በረከት በግብፃዊው ሰው ቤት ሆነ። እግዚአብሔርም የሚሠራውን ሁሉ ያቀናለት ነበር። 21ግብፃዊውም ሰው እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንደ አለ፥ የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር እንዲያቀናለት አይቶአልና ሁሉን በዮሴፍ ፊት ተወ። 22ዮሴፍም መልከ መልካም፥ እጅግም የተዋበ ነበረ። 23የጌታውም ሚስት ዐይኖችዋን አንሥታ ዮሴፍን አየችው። ወደደችውም፤ ከእርስዋም ጋር ይተኛ ዘንድ ለመነችው፤ እርሱ ግን ልቡን አልሰጣትም። 24እግዚአብሔርንም አሰበው፤ ባል በአላት ሴት ማንም ሰው እንዳያመነዝር ከአብርሃም ቃላት አባቱ ያዕቆብ ያነበበላቸውን ነገሮች አሰበ። በሰማይ በልዑል እግዚአብሔር ፊት የተሠራለት የሞት ቅጣት እንደ አለ አሰበ። በዘመኑ ሁሉ ኀጢአት ስለ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት በዘለዓለም መጽሐፍ እንደምትጻፍ አሰበ። 25ዮሴፍም ይህን ነገር አሰበ፤ ከእርስዋም ጋር ይተኛ ዘንድ አልወደደም፤ አንድ ዓመት አባበለችው፤ ከለከላትም፤ መስማትንም እንቢ አላት። 26እርስዋ ግን ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ ልትጣላው በቤት አስጨንቃ ያዘችው፤ የቤቷንም ደጃፍ ዘጋች፤ በገሃድም ያዘችው፤ እርሱ ግን ከእጅዋ አመለጠ፤ ልብሱንም በእጅዋ ትቶ፥ ሳንቃውንም ሰብሮ ከፊቷ ወደ ውጭ ሸሸ። 27ያቺም ሴት ከእርስዋ ጋር እንደማይተኛ በአየች ጊዜ እንዲህ ብላ በጌታው ፊት አጣላችው፥ “የምትወድደው ይህ ዕብራዊ ባሪያህ ይደፍረኝ ዘንድ ወደደ። 28እንዲህም ሆነ፥ ቃሌን ከፍ አድርጌ በጮኽሁ ጊዜ ልብሱን በእጄ ትቶ፥ በያዝሁትም ጊዜ ሳንቃውን ሰብሮ ሸሸ።” 29ግብፃዊውም የዮሴፍን ልብስና የተሰበረውን መዝጊያ አየ፤ 30የሚስቱንም ነገር ሰምቶ ዮሴፍን ንጉሥ ያሰራቸው እስረኞች ወደ አሉበት እስር ቤት አገባው። 31በዚያም በእስር ቤት ኖረ። እግዚአብሔርም ለዮሴፍ በእስር ቤት ጠባቂዎች አለቃ ፊት ሞገስን፥ ምሕረትንም በፊቱ ሰጠው። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ አለ፥ የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር እንዲያቀናለት አይቶአልና ሁሉን በፊቱ ተወ። 32ዮሴፍ ሁሉን ያደርግ ነበርና፥ እግዚአብሔርም ይፈጽምለት ነበርና የእስር ቤት ጠባቂዎች አለቃ ያለ እርሱ ምንም የሚያውቀው አልነበረም። በዚያም ሦስትዓመት 33በዚያም ወራት የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን በሁለቱ ባለምዋሎቹ በጠጅ አሳላፊዎች አለቃና በእንጀራ አሳላፊዎች አለቃ ላይ ተቈጣ። ዮሴፍ ተይዞ በዚያ በታሠረበት በእሥር ቤቱ አለቃ ቤትም በእስራት አኖራቸው። 34የእስረኞች አለቃም በፊታቸው ይላላካቸው ዘንድ፥ በፊቱም ይላላከው ዘንድ ዮሴፍን ሾመው። 35ሁለቱም የጠጅ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ አሳላፊዎች አለቃ ሕልም አለሙ። ለዮሴፍም ነገሩት፤ ዮሴፍም እንደ ተረጐመላቸው እንዲሁ ሆነላቸው። 36ፈርዖንም ዮሴፍ እንደ ተረጐመላቸው የጠጅ አሳላፊዎችን አለቃ ወደ ሥራው መለሰው፤ የእንጀራ አሳላፊዎችን አለቃ ግን ገደለው፤ 37የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ግን ዮሴፍን በእስር ቤት ረሳው። ዮሴፍ የሚሆንለትን ነግሮት ነበርና እንደ ነገረው ለፈርዖን ይነግረው ዘንድ አላሰበም። ረስቶታልና።