1ይህን አዝዞአቸውና መርቆአቸው ከጨረሰ በኋላ በፊቱ በአንድነት በሉ፤ ጠጡም። 2በመካከላቸውም መተካከል ሆኖአልና ደስ አላቸው። ከእርሱም ዘንድ ወጡ፤ በዚያችም ቀን ዐርፈው ተኙ። 3ይስሐቅም ደስ ብሎት በዚያች ቀን በአልጋው ላይ ተኛ፤ የዘለዓለምንም እንቅልፍ አንቀላፋ። 4የመቶ ሰማንያ ዐመት ሰው ሆኖ ሞተ። ሃያ አምስት ሱባዔንና አምስት ዓመትን ጨረሰ። ሁለቱ ልጆቹ ዔሳውና ያዕቆብም ቀበሩት። 5ዔሳውም በኤዶምያስ አውራጃ ወደ አለች ወደ ሴይር ተራራ ሄደ፤ በዚያም ኖረ። 6ያዕቆብም አባቱ አብርሃም ተሰዶ ይኖርበት በነበረ በኬብሮን ምድር ባለ ግንብ ኖረ። 7እንደ ተወለደበት ወራት እንደሚታየው ትእዛዝ አድርጎ በፍጹም ልቡናው እግዚአብሔርን አመለከው። 8በአርባ አምስተኛው ኢዮቤልዩ በሁለተኛው ሱባዔ በአራተኛው ዓመት ሚስቱ ልያ ሞተች። በአባቱ እናት በሳራ መቃብር በስተግራ በእናቱ በርብቃ መቃብር አጠገብ ደርብነት በአላት ዋሻ ቀበራት። 9ልጆቹና ልጆችዋ ሁሉ ለሚስቱ ለልያ ከእርሱ ጋር ያለቅሱላት ዘንድ፥ ስለ እርስዋም ያረጋጉት ዘንድ መጡ፤ ያለቅስላት ነበርና። በሥራዋም ሁሉ ፈጽማ ቅን ስለሆነች እኅቷ ራሔል ከሞተች ጀምሮ ፈጽሞ ይወድዳት ነበርና። 10ያዕቆብንም ታከብረው ነበር፤ ከእርሱም ጋር በኖረችበት ዘመን ሁሉ ክፉ ነገር ከአፍዋ አልሰማም፤ የዋህና ሰላማዊት ነበረችና፥ ሰላም፥ ቅንነት፥ ክብርም ያላት ነበረችና። 11በሕይወት ሳለች የሠራችውን ሥራ ሁሉ ያስብ ነበር፤ ያለቅስላትም ነበር። በፍጹም ሰውነቱና በፍጹም ልቡናው ፈጽሞ ይወድዳት ነበርና። 12የዔሳውና የያዕቆብ አባት ይስሐቅ በሞተባት ቀን የዔሳው ልጆች ይስሐቅ ለታናሹ ልጁ ለያዕቆብ ብኵርናውን እንደ ሰጠው ሰሙ። 13ፈጽመውም ተቈጡ፤ “አንተ ታላቅ ሳለህ፥ ያዕቆብ ያንተ ታናሽ ሲሆን፥ አባትህ አንተን ትቶ ለያዕቆብ ብኵርናን ለምን ሰጠው?” ብለው ከአባታቸው ጋር ተከራከሩ። 14እርሱም አላቸው፥ “እኔ ብኵርናዬን በትንሽ ምስር ንፍሮ ሸጫለሁና ስለዚህ ነው። 15በልቶ ሊመርቀኝ አድኜ አመጣለት ዘንድ አባቴ በላከኝ ቀን በተንኰል መጥቶ የሚበላውንና የሚጠጣውን ለአባቴ አቀረበ። አባቴም መረቀው፤ እኔንም ከእርሱ በታች አደረገኝ። 16አሁንም ወንድም ከወንድሙ ጋር በክፉ ነገር እንዳንፈላለግ፤ ነገር ግን ወንድም ከወንድሙ ጋር በፍቅርና በሰላም ጸንተን እንድንኖር፥ መንገዳችንንም እንዳናጠፋ፥ አባታችን እኔንና እርሱን አማማለን።” 17እነርሱም አሉት፥ “ከእርሱ ጋር ፍቅር ለማድረግ አንሰማህም፤ ከእርሱ ኀይል የእኛ ኀይል ይጸናልና፥ እኛም ከእርሱ እንበረታለንና ወደ እርሱ ሄደን እንገድለዋለን፤ ልጆቹንም እንገድላለን፤ ከእኛ ጋር ካልሄድህም በአንተ ላይ ክፉ ነገር እናደርግብሃለን። 18አሁንም ስማን፤ ወደ አራም፥ ወደ ፍልስጥኤም፥ ወደ አሞንና ወደ ሞዓብ ልከን በሰልፍ የሚመክቱ የተመረጡ ሰዎችን ለራሳችን እንምረጥ፤ 19ወደ እርሱም ሄደን ከእርሱ ጋር እንዋጋ፤ ኀይልም ሳይዝ ከምድር እናጥፋው።” 20አባታቸውም፥ “አትሂዱ፤ በፊቱም እንዳትጠፉ፥ ከእርሱ ጋር ጠብን አታድርጉ” አላቸው። 21እነርሱም አሉት፥ “ከልጅነትህ ጀምሮ እስከዚህች ቀን ድረስ ሥራህ ይህ ብቻ ነውን? አንተ አንገትህን ወደ ቀንበሩ ታገባለህ፤ እኛስ ይህን ነገር አንሰማም።” 22ወደ አራምና ወደ አባታቸው ወዳጅ ወደ አዱራም ልከው የተመረጡ አርበኞችና ጦረኞች የሚሆኑ ሺህ ሰዎችን ለመቅጠር ከእነርሱ ጋር ተስማሙ። 23ከተወዳጁአቸው ከአሞንና ከሞዓብ ልጆች የተመረጡ ሺህ አርበኞች፥ 24ከፍልስጥኤም የተመረጡ ሺህ አርበኞች፥ 25ከኤዶምና ከኮራውስ የተመረጡ ሺህ አርበኞች፥ 26ከኬጤዎንም ጽኑዓን የሆኑ አርበኞች ወደ እነርሱ መጡ። 27አባታቸውንም፥ “ወጥተህ ምራቸው፤ ይህ ካልሆነ እንገድልሃለን” አሉት። እርሱም ወደ ወንድሙ ወደ ያዕቆብ ሊመራቸው ይሄድ ዘንድ ልጆቹ እንደ ተበራቱበት በአየ ጊዜ ፈጽሞ ቍጣን ተመላ። 28ከዚህም በኋላ በልቡ የተሰወረ ክፋትን ሁሉ በወንድሙ በያዕቆብ ላይ አሰበ። ነገር ግን በዘመኑ ሁሉ በወንድሙ በያዕቆብ ላይ ክፉ ነገርን እንዳይፈልግ ለእናቱና ለአባቱ የማለውን መሐላ አላሰበም። 29ያዕቆብ ግን እነርሱ ለመዋጋት ወደ እርሱ እንደሚመጡ ይህን ሁሉ አላወቀም። እርሱም ከተመረጡ ከአራት ሺህ አርበኞችና ጦረኞች ጋር በግንቡ አጠገብ ወደ እርሱ እስኪቀርቡ ድረስ ለሚስቱ ለልያ ያለቅስ ነበር። 30የኬብሮን ሰዎችም፥ “እነሆ፥ ወንድምህ ይዋጋህ ዘንድ ሰይፍ ከታጠቁ፥ ጋሻቸውንና ጦራቸውንም ከያዙ ከአራት ሺህ ሰዎች ጋር መጣ” ብለው ወደ እርሱ ላኩ። 31ከዔሳው ይልቅ ያዕቆብን ይወዱት ነበርና ነገሩት፤ ያዕቆብ ለጋስ ሰው ነበረና፥ ከዔሳውም ይልቅ ቸር ነበረና። ያዕቆብም ወደ ግንቡ አጠገብ እስኪቀርቡ ድረስ የነገሩትን አላመነም። የግንቡንም በር ዘጋ። 32በግንቡም ላይ ቆሞ ከወንድሙ ከዔሳው ጋር ተነጋገረ፤ እንዲህም አለ፥ “ሚስቴ ስለ ሞተች በበጎ ማረጋጋት ታረጋጋኝ ዘንድ መጣህን? 33እናትህና አባትህ ሳይሞቱ ዳግመኛ ፈጥነህ የማልኸው መሐላ ይህ ነውን? 34ከማልኸው መሐላ ወጥተህ በደልህ፤ ለአባትህም በማልህበት ጊዜ ተፈረደብህ።” ዔሳውም ያንጊዜ መለሰ። 35እንዲህም አለው፥ “ለምድር አራዊትና ለሰው ልጆች በእውነት የተማማሉት መሐላ እስከ ዘለዓለም ድረስ የለም። 36በየቀኑ ይህ ለዚህ ክፋትን ይፈልጋል። እያንዳንዱም ጠላት ጠላቱን ይገድለው ዘንድ ይፈልጋል። 37አንተም እኔን ከልጆች ጋር እስከ ዘለዓለም ድረስ ትጠላኛለህ፤ ከአንተ ጋርም ወንድማማችነት ማድረግ የለም። እኔ የምነግርህን ይህን ነገሬን ስማ። እሪያ ጠጕሩንና ቁርበቱን እንደ ባዘቶ ቢለውጥ፥ 38እንደ በግና እንደ ዋልያም በራሱ ላይ ቀንድ ቢወጣ፥ ያንጊዜ ከአንተ ጋር ወንድማማችነትን አደርጋለሁ። 39ጡቶች ከእናቶች ቢለዩ ወንድም በሆንኸኝ ነበር። ተኵላዎችም እንዳይበሉአቸውና እንዳይነጣጠቁአቸው ከበጎች ጋር ሰላምን ቢያደርጉ፥ ልቡናቸውም ለእነርሱ በጎ ነገርን ለማድረግ ቢያስብ፥ 40ያንጊዜ በልቡናዬ ለአንተ ሰላም ይሆናል። አንበሳ ለላም ወዳጁ ቢሆን፥ ከእርሱም ጋር በአንድ ቀንበር ቢጠመድ፥ ከእርሱም ጋር ቢያርስ፥ ከእርሱም ጋር ሰላምን ቢያደርግ፥ ያንጊዜ ከአንተ ጋር ሰላምን አደርጋለሁ። 41ቁራዎች እንደ ሳቢሳ ቢነጡ፥ ያንጊዜ እንደ ወደድሁህ፥ ከአንተም ጋር ሰላምን እንዳደረግሁ አውቃለሁ፤ አንተም ትጠፋለህ፥ ልጆችህም ይጠፋሉ። ለአንተም ሰላም አይደረግልህም።” 42ያንጊዜም ያዕቆብ በእርሱ ልቡናውን እንዳስጨከነ፥ ይገድለውም ዘንድ በፍጹም ልቡናው እንዳሰበ ዐወቀ። 43እርያ በጦር ወግቶ ወደሚገድለው ሰው ፈጥኖ እንደሚወጣ፥ ከእርሱም እንደማይሸሽ ዔሳው ፈጥኖ መጣ። 44ያንጊዜም ባሪያዎቹንና ወገኖቹን፥ ወዳጆቹንም ሁሉ ይከቡት ዘንድ አዘዘ። 45ከዚህም በኋላ ይሁዳ አባቱን ያዕቆብን ተናገረው፤ እንዲህም አለው፥ “አባቴ ሆይ፥ ቀስትህን ሳብ፥ ፍላጻህንም ወርውረህ ጠላትህን ውጋ፤ ጠላትህንም ግደል። ኀይልም ይሁንልህ። 46እኛ ወንድምህን አንገድልምና፤ እርሱም በአንተ ዘንድ አለና፥ በእኛም ዘንድ ለመከበር እንደ አንተ ነውና።” 47ያንጊዜም ያዕቆብ ቀስቱን ስቦ ፍላጻውን ወርውሮ ወንድሙን ዔሳውን ወግቶ ገደለው። 48ዳግመኛም ፍላጻውን ወርውሮ የአሕዛብ ወገን የሚሆን አዱራንን የግራ ጡት ሥሩን ወጋው፤ አሳድዶም ገደለው።