1በአርባ አምስተኛው ኢዮቤልዩ በመጀመሪያው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ርብቃ ልጅዋን ያዕቆብን ጠርታ በያዕቆብ በዘመኑ ሁሉ ያከብራቸው ዘንድ፥ ስለ ወንድሙና ስለ አባቱ አዘዘችው። 2ያዕቆብም እንዲህ አለ፥ “ይህ ነገር ለእኔ ክብር፥ ጌትነትም ነውና፥ አከብራቸውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት በጎ ነገር ነውና እኔ ያዘዝሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ። 3እናቴ ሆይ፥ ከተወለድሁባት ቀን ጀምሮ እስከዚህች ቀን ድረስ በዘመኔ ሁሉ ለሁሉ በጎ ነገር እንደማስብ ሥራዬን ሁሉና በልቤ ያለውን ሁሉ ታውቂያለሽ። 4ወንድሜንና አባቴን አከብር ዘንድ ያዘዝሽኝን ነገር እንዴት አላደርግም? በእኔ ምን ጥመት አየሽብኝ? እናቴ፥ እስኪ ንገሪኝ፤ እኔም ከእርሱ ፈጽሜ እርቃለሁ፤ ይቅርታም ይደረግልኛል” አላት። 5እርሱዋም አለችው፥ “ልጄ ባለ በዘመኔ ሁሉ የቀና ሥራን ነው እንጂ በአንተ ያየሁት ምንም ጠማማ ሥራ የለም። 6ነገር ግን ልጄ! እውነት ነገርን እነግርሃለሁ። እኔ በዚህች ዓመት እሞታለሁ። ከመቶ አምሳ አምስት ዓመት በላይ እንዳልኖር፥ የምሞትባትን ቀን በሕልሜ አይቻለሁና ይህችን ዓመት በሕይወት አላልፋትም። 7እኖርበት ዘንድ ያለኝን ዘመኔን ሁሉ እነሆ፥ እኔ ፈጽሜአለሁ።” ያዕቆብ እናቱ፥ “እሞታለሁ” ብላዋለችና ስለ እናቱ ነገር ሳቀ። 8እርስዋ ግን በአንጻሩ ተቀምጣ ነበር፤ ኀይልም ነበራት፤ ትወጣና ትገባ ነበርና፥ ታይም ነበርና። ጕልበቷም አልደከመም ነበር፤ ጥርስዋም ጽኑ ነበር፤ በሕይወት በኖረችበት ዘመን ሁሉ ምንም በሽታ አላገኛትም ነበር። 9ያዕቆብም አላት፥ “እናቴ ሆይ! ዘመኔ በሕይወት ወደ ኖርሽበት ዘመን ከቀረበ እኔ እድለኛ ነኝ፤ ኀይሌም እንደ አንቺ ኀይል እንዲህ በእኔ ጸንቶ ይኖራል፤ ስለ ሞትሽም ከእኔ ጋር በዋዛ ከንቱ ነገርን ትናገሪያለሽና አትሞቺም።” 10ወደ ይስሐቅም ገብታ እንዲህ አለችው፥ “አንድ ልመናን እለምንሃለሁ፤ የዔሳው ልቡ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ክፉ እንደ ሆነ ታውቃለህና፥ በእርሱም ቸርነት የለምና፤ ከሞትህ በኋላ እርሱ ይገድለው ዘንድ ይወድዳልና፥ በያዕቆብም ላይ ክፉ ነገርን እንዳያደርግ፥ በጠብም አስወጥቶ እንዳይሰድደው ዔሳውን አምለው። 11ወንድሙ ያዕቆብ ወደ ካራን ከሄደ ጀምሮ እስከዚህች ቀን ድረስ በዘመኑ ሁሉ ያደረገውን አንተ ታውቃለህ፤ በፍጹም እንደ ተወን፥ በእኛም ክፉ ነገርን እንዳደረገ አንተ ታውቃለህ፤ መንጋህን ሰበሰበ፤ ገንዘብህንም ሁሉ ከፊትህ ቀማህ። 12ገንዘባችንን ይሰጠን ዘንድ ስንለምነው እርሱ እንደሚመጸውተን ሰው ያደርገዋል፤ ፍጹምና ቅን የሚሆን ልጅህ ያዕቆብንም ስለ መረቅኸው አንተን ይጠላሃል። 13ከደግነት በቀር ክፋት የለውምና ከካራን ከመጣ ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ ምንም ያጐደለብን የለም፤ ሁሉን በየጊዜው ዕለት ዕለት ያመጣልን ነበርና ያመጣልንንም ከእጁ በተቀበልን ጊዜ በፍጹም ልቡናው ደስ ይለው ነበር፤ ያከብረንም ነበር፤ ከካራንም ከመጣ ጀምሮ እስከዚህች ቀን ድረስ ከእኛ አልተለየም። 14እርሱም እያከበረን ከእኛ ጋር ሁልጊዜ በቤት ይኖራል።” 15ይስሐቅም እንዲህ አላት፥ “እርሱ በፍጹም ልቡናው እንደሚያከብረን፥ ከእኛ ጋር ያለ የያዕቆብን ሥራ ዐውቃለሁ፤ አያለሁም። ቀድሞ ከተወለደበት ቀን ጀምሮ ከያዕቆብ ይልቅ ዔሳውን እወደው ነበር፤ 16ዛሬ ግን ከዔሳው ይልቅ ያዕቆብን እወድዳለሁ። ክፉ ሥራውን አብዝቶአልና፥ ለእርሱም በጎ ሥራ የለውምና፥ ሥራው ሁሉ ዐመፅና ግፍ ነውና፥ በዙሪያውም እውነት ነገር የለውምና። 17አሁንም ስለ ክፉ ሥራው ሁሉ ልቡናዬ ይታወካል። የአብርሃምንም ፈጣሪ ትቶ ሚስቶቹን ስለ ተከተለ፥ ጣዖታቸውንም ስላመለከ፥ እርሱም ከልጆቹ ጋር ስሕተታቸውን ስለ ተከተለ ለእርሱና ለዘሩ ድኅነት የለውም። እነርሱ ከሰማይ በታች ካለ ከዚህ ዓለም የሚጠፉ ናቸውና። 18አንቺ ግን ወንድሙን ያዕቆብን እንዳይገድል አምለው ዘንድ አምለው ትያለሽ፤ ቢምልም በመሐላው ጸንቶ አይኖርም፤ ከክፉ ነገርም በቀር በጎ ሥራን አይሠራም። 19ወንድሙን ያዕቆብንም ይገድል ዘንድ ቢወድ በያዕቆብ እጅ ይወድቃል። በእጁም ይወድቃልና ከእጁ አያመልጥም። 20ዔሳውን ከሚጠብቀው ይልቅ ያዕቆብን የሚጠብቀው ገናናና ኀያል፥ የከበረና የተመሰገነም ነውና አንቺ ስለ ያዕቆብ አትፍሪ” አላት። 21ርብቃም ልካ ዔሳውን ጠራችው፤ ወደ እርስዋም መጣ፤ እርስዋም፥ “ልጄ ሆይ፥ ከአንተ የምለምነው ልመና አለኝ፤ ልጄ ሆይ፥ የምለምንህን ታደርግልኝ ዘንድ እሺ በለኝ” አለችው። 22እርሱም፥ “ያልሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ልመናሽንም እንቢ አልልም” አላት። እርሱዋም እንዲህ አለችው፥ “በሞትሁ ጊዜ በአባትህ እናት በሳራ መቃብር አቅራቢያ ትቀብረኝ ዘንድ፥ ወንድምህ ያዕቆብና አንተም እርስ በርሳችሁ ትፋቀሩ ዘንድ፥ 23ከፍቅርም በቀር አንዱም አንዱ በወንድሙ ላይ ክፉ ነገርን እንዳያደርግ፥ ልጆች በሥራችሁ ትከናወኑ ዘንድ፥ በዚህ ዓለምም ትከብሩ ዘንድ፥ ጠላትም በእናንተ ደስ እንዳይለው እኔ ከአንተ እለምናለሁ። 24በሚወዱአችሁም ሰዎች ሁሉ ፊት ለይቅርታና ለበረከት ትሆናላችሁ።” 25እርሱም እንዲህ አለ፥ “እኔ ያልሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ በሞትሽም ጊዜ አጥንቶችሽ በአጥንቶችዋ አቅራቢያ ይኖሩ ዘንድ አጥንቶችዋን እንደ ወደድሽ በአባቴ እናት በሳራ አቅራቢያ እቀብርሻለሁ፤ ወንድሜ ያዕቆብንም ከሰው ሁሉ ይልቅ እኔ እወድደዋለሁ። 26ከእርሱ ብቻ በቀር በምድር ሁሉ ለእኔ ሌላ ወንድም የለኝም፤ ወንድሜ ነውና እርሱን ብወድደው ይህ ለእኔ ታላቅ አይደለም፤ በማኅፀንሽም መካከል በአንድነት ተዘርተናል፤ 27ከማኅፀንሽም በአንድነት ወጥተናል፤ ወንድሜንስ ያልወደድሁ ማንን እወዳለሁ? 28ስለ ልጆችና ስለ እኔ ያዕቆብን ትመክሪው ዘንድ እኔ እንዲህ እለምንሻለሁ፤ አባቴ ከመረቀው ቀን ጀምሮ እርሱን ታላቅ፥ እኔንም ታናሽ አድርጎአልና በልጆች ላይና በእኔ ላይ እንዲነግሥ አውቃለሁ። 29እኔም በሕይወት በምኖርበት ዘመን ሁሉ እንደምወድደውና መቼም መች ከበጎ ነገር በቀር በእርሱ ላይ ክፉ ነገርን እንደማልፈልግ እምልልሻለሁ።” 30ስለዚህ ሁሉ ነገር ማለላት፤ ያዕቆብንም በዔሳው ፊት ጠርታ ከዔሳው ጋር እንደ ተነጋገረችው ነገር አዘዘችው። 31እርሱም አላት፥ “እኔ ፈቃድሽን እፈጽማለሁ፤ በወንድሜም በዔሳው ላይ ከእኔና ከልጆች ክፉ ነገር እንደማይወጣ፥ ከፍቅርም በቀር መቼም መች አስቀድሜ እንደማልጣላ ተዋሽኝ።” እርስዋና ልጆችዋም በሉ፤ ጠጡም። 32በዚያችም ሌሊት የሦስት ኢዮቤልዩ፥ የአንድ ሱባዔና የአንድ ዓመት ሰው የነበረችው ርብቃ ሞተች። በዚያችም ሌሊት ሁለቱ ልጆችዋ ዔሳውና ያዕቆብ ደርብነት ባላት ዋሻ በአባታቸው እናት በሳራ መቃብር አጠገብ ቀበሩአት። 33በዚህ ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት ይስሐቅ ሁለቱን ልጆቹን ዔሳውንና ያዕቆብን ጠራቸው፤ ወደ እርሱም መጡ። 34እንዲህም አላቸው፥ “ልጆች ሆይ! እኔ አባቶች በሄዱበት ጎዳና አባቶች በዚያ ለዘለዓለም ወደሚኖሩበት ቤት እሄዳለሁ፤ አብርሃም ለመቃብር በገዛው፥ እኔ ለራሴ ባስቈፈርሁት፥ በኬጢ ሰው በኤፍሮን እርሻ ውስጥ ባለች ደርብነት ባላት ዋሻ በአባቴ በአብርሃም አጠገብ ቅበሩኝ።” 35ልጆች ሆይ! እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ ያደርግ ዘንድ የነገረውን ሁሉ ለእናንተ እንዲያደርግላችሁ በዚህ ዓለም እውነትንና ቅንነትን ትሠሩ ዘንድ ይህን አዘዝኋችሁ። 36ልጆች ሆይ! ሰው ራሱን እንደሚወድድ እርስ በርሳችሁ ወንድሞቻችሁን እየወደዳችሁ ኑሩ። 37ሰው ለወንድሙ በጎ ነገርን ያደርግለት ዘንድ ፈልጎ፥ ይህንም በምድር ላይ በልቡናው በአንድነት አድርጎ፥ እርስ በርሳቸው እንደ ራሳቸው እንደሚፋቀሩ፥ እርስ በርሳችሁ የምትፋቀሩ ሁኑ። 38ስለ ጣዖቱም ነገር ትንቁአቸውና ትጠሉአቸው ዘንድ፥ እንዳትወዱአቸውም እኔ አዝዛችኋለሁ። ለሚያመልኳቸውና ለሚሰግዱላቸው ሰዎች ስሕተትን የተመሉ ናቸውና፤ 39ልጆች ሆይ፥ የአባታችሁን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን ዐስቡት። 40ከዚህም በኋላ እኔ አመለክሁት። በእውነትና በሰፊ ልቡና ተገዛሁለት። በደስታ ያበዛችሁ ዘንድ፥ ልጆቻችሁንም እንደ ሰማይ ኮከብ ለማብዛት ያሳድግላችሁ ዘንድ፥ ለዘለዓለም ትውልድም ሁሉ የማይነቀል የእውነተኛ ተክል አድርጎ በምድር ይተክላችሁ ዘንድ ዐስቡት። 41“አሁንም እኔ በታላቅ መሐላ አምላችኋለሁ። ከእርሱ የሚበልጥ በሌላ፥ በተመሰገነና፥ በከበረ፥ ገናናና ድንቅ በሆነ፥ ኀያል ጽኑ በሆነ፥ ሰማይንና ምድርን በፈጠረ፥ ሁሉንም አንድ አድርጎ በያዘ በእግዚአብሔር ስም ከመማል የሚበልጥ መሐላ የለምና፥ እያንዳንዱም በይቅርታና በቸርነት ወንድሙን እየወደደ የምትፈሩትና የምታመልኩት ትሆኑ ዘንድ አምላችኋለሁ። 42ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ፥ በሥራችሁ ሁሉ ትከናወኑ ዘንድ፥ እንዳትጠፉም ሰው በወንድሙ ክፉ ነገር ማድረግን አይውደድ። 43ከእናንተ በወንድሙ ክፉ ነገርን ያደርግ ዘንድ የሚፈልግ ሰው ቢኖር በእጁ እንደሚወድቅ፥ ከሕያዋን ምድርም ከዛሬ ጀምሮ እንደሚጠፋ ዕወቁ። 44ዘርዑም ክርክር፥ መዓትና ቍጣ በሚደረግባት ቀን ከሰማይ በታች ካለ ከዚህ ዓለም ይጠፋል፤ እግዚአብሔርም በሚነድና በሚያቃጥል እሳት ሰዶምን እንዳቃጠለ እንደዚሁ ሀገሩንና ከተማውን ያቃጥላል። የእርሱ ገንዘብ የሆነውንም ሁሉ ያጠፋል፤ የሰው ልጅ ተግሣጽ ከተጻፈበትም መጽሐፍ ይጠፋል። 45እርሱ የሚጠፋ ነውና፥ ለዘለዓለም ርግማንም የሚያልፍ ነውና፥ በዘመኑ ሁሉ ቍርጥ ፍርዳቸው በመርገምና በስድብ፥ በጭንቅና በቍጣ፥ በዘለዓለም ደዌና መቅሠፍትም የታደሰ ይሆን ዘንድ በሕይወት መጽሐፍ አይጻፍም። 46ልጆች ሆይ፥ በወንድሙ ክፉ ነገርን ያደርግ ዘንድ በሚወድ ሰው ላይ ቅጣት እንደሚመጣ፥ እንደሚጠፋም እነግራችኋለሁ፥ አዳኝባችኋለሁም።” 47ያለውንም ገንዘብ ሁሉ በዚያች ቀን ለሁለቱ አደለ፤ ክብርንም አስቀድሞ ለተወለደው ልጁ ሰጠ። ግንቡንና በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ሰጠ። 48አብርሃም በዐዘቅተ መሐላ ያጠራቀመውንገንዘብ ሁሉ ሰጠው። እንዲህም አለ፥ “ይህን ታላቅ ክብር አስቀድሞ ለተወለደው ልጅ ሰጠሁ።” 49ዔሳውም አለ፥ “ለያዕቆብ ብኵርናዬን ሸጥሁለት፤ ክብርም ይሰጠው ዘንድ ብኵርናዬን ለያዕቆብ ሰጠሁ፤ በእርሱ ዘንድ አለችና ስለ እርስዋ ምንም የምናገረው ነገር የለኝም።” 50ይስሐቅም እንዲህ አለ፥ “ልጆች ሆይ፥ አሳርፋችሁኛልና፥ በእርስዋም ምክንያት ክፉ ሥራን እንዳትሠሩ ስለ ብኵርና ልቡናዬ አላዘነችምና በዚህች ቀን በእናንተና በልጆቻችሁ ላይ በረከት ትደር፤ በጎ ሥራ የሚሠራ ሰውን ልዑል እግዚአብሔር ያክብረው፤ እርሱንና ዘሩንም ለዘለዓለም ይባርክ።”