1ከዚህ ከአርባ አራተኛው ኢዮቤልዩ በዚህ ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት በጎችን ይጠብቁ ዘንድ ያዕቆብ ልጆቹን ላካቸው። አገልጋዮቹንም ከእነርሱ ጋር ወደ ሰቂሞን መስክ ላካቸው። 2በዛፍ ሥር ተሰውረው ያጠፉአቸው ዘንድ፥ ሚስቶቻቸውንና ከብቶቻቸውንም ይማርኩ ዘንድ ሰባቱ የአሞሬዎን ነገሥታት በእነርሱ ላይ ተሰበሰቡ። 3የያዕቆብም ልጆች፥ ሌዊ፥ ይሁዳና ዮሴፍ ከአባታቸው ከያዕቆብ ጋር በቤት ነበሩ። ልቡናው ያዝንበት ነበርና፥ እርሱንም መተው አልተቻላቸውምና፤ ስለዚህም ታናሹ ልጁ ብንያም በእርሱ ዘንድ ነበረ። 4የታፋ ነገሥታት፥ የአሬሳ ነገሥታት፥ የሳራጋን ነገሥታትና የሴሎን ነገሥታት፥ የጋዒዝ ንጉሥ፥ የቤቴሮን ንጉሥና የማአኒሲኪሮስ ንጉሥ በተራራ የሚኖሩ ሁሉ። 5በከነዓን ባለ ዛፍ ሥር የሚኖሩ ሁሉ መጡ። ለያዕቆብም፥ “እነሆ፥ የአሞሬዎን ነገሥታት ልጆችህን ከበቡአቸው፤ መንጋቸውንም ተነጠቁ” ብለው ነገሩት። 6እርሱም ከቤቱ ተነሣ፤ ሦስቱም ልጆቹ፥ የአባቱም ብላቴኖች ሁሉ፥ የእርሱም ብላቴኖች ተነሡ። 7መሣሪያ የያዙ ዘጠኝ ሺህ ሰዎች ይዞ ሄዶ በሰቂሞን መስክ ወጉአቸው። 8የሸሹትንም ተከትለው በሰይፍ አጠፉአቸው፤ ታፋና አሬሳን፥ ሴሎንና ሰራጋን፥ ማአኒሲኪሮስን፥ ጋኤዝንም አጠፋቸው፤ መንጋውንም ሰበሰበ። 9በእነርሱ ላይ ከፍ ከፍ አለ። እነዚህ አምስት እጅ የምድራቸውን ፍሬ ግብር ይሰጡት ዘንድ በእነርሱ ላይ ግብር ሠራ። 10ታምናን ታሬስንና ሮቤልን ቀጸረ፤ በሰላምም ተመለሰ። 11ከእነርሱ ጋር ሰላምን አደረገ። እርሱና ልጆቹ ወደ ግብፅ እስከወረዱበት ቀን ድረስ አገልጋዮች ሆኑት። 12በዚህ ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት የወንድሞቹን ደኅንነት ያውቅ ዘንድ ዮሴፍን ከቤቱ ወደ ሰቂሞን ምድር ላከው። 13በዶታኤም ምድርም አገኛቸው፤ በዘበዙት፥ ይገድሉትም ዘንድ፦ መከሩበት። 14ተመልሰውም ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች ሸጡት። እነሱም ወደ ግብፅ አውርደው የኤሌው ሀገር ካህን ለሚሆን፥ ለእንጀራ አሳላፊዎች አለቃ፥ ለፈርዖን ባለምዋል ለፋጢፋራን ሸጡት። 15የያዕቆብም ልጆች አውራ ፍየል አርደው የዮሴፍን ልብስ በደም ነከሩ። 16ሰባተኛው ወርም በባተ በዐሥረኛው ቀን ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ላኩ። በዚያች ቀን ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ አለቀሰ። 17ልብሱንም አመጡለት፤ በሞቱ ኀዘን ተንቀጠቀጠ። ዮሴፍን ክፉ አውሬ እንደ በላው ነገሩት፤ የቤቱም ሰዎች ሁሉ በዚያች ቀን አለቀሱ፤ ቀኑን ሁሉ ከእርሱ ጋር ያዝኑና ያለቅሱ ነበር። 18ወንዶቹ ልጆቹና ሴቲቱ ልጁ ያረጋጉት ዘንድ ተነሡ። ነገር ግን ስለ ልጁ ስለ ዮሴፍ አልተረጋጋም። 19በዚያም ቀን ባላን ዮሴፍ እንደ ሞተ ሰማች። ለእርሱም ስታለቅስ ሞተች። እርስዋም በቅፍራቲፋ ትኖር ነበር። 20ልጁ ዲናም ዮሴፍ ከጠፋ በኋላ ሞተች። በያዕቆብ ላይ በአንድ ወር ይህ ሦስቱ ኀዘን ደረሰበት። ባላንም በራሔል መቃብር አንጻር ቀበሩአት፤ ልጁን ዲናንም በዚያ ቀበሩዋት። 21ከዮሴፍ መጥፋት በኋላ አንድ ዓመት ሲያለቅስ ኖረ። “ስለ ልጄ ስለ ዮሴፍ እያለቀስሁ ወደ መቃብር እወርዳለሁ” ብሎአልና ልቅሶውን አልተወም። 22ስለዚህ ነገር የዮሴፍን መርዶ ወደ አባቱ ወደ ያዕቆብ ባደረሱበት ቀን በፍየል ጠቦት ለእርሱ ያስተሰርይለት ዘንድ፥ ሰባተኛው ወር በባተ በዐሥረኛው ቀን ያዝኑ ዘንድ፥ በእስራኤል ልጆች ላይ ሥርዐት ተሠራ። 23ሰባተኛው ወር በባተ በዐሥረኛው ቀን ከዓመት አንድ ጊዜ ስለ ኀጢአታቸው ተሠራች፤ ስለ ልጁ ስለ ዮሴፍ የአባታቸውን ልቡና አሳዝነዋልና። 24ይህቺም ቀን ስለ ኀጢአታቸውና ስለ በደላቸው ሁሉ፥ ስለ ስሕተታቸውም በዚህች ቀን በዓመት አንድ ጊዜ በዚያች ቀን ራሳቸውን ሊያነጹ ያዝኑባት ዘንድ ተሠራች። 25ዮሴፍም ከጠፋ በኋላ የያዕቆብ ልጆች ለራሳቸው ሚስት አገቡ፤ የአንደኛው የሮቤል ሚስት ስምዋ አዳ ይባላል። 26የሁለተኛውም የስምዖን ሚስት ስምዋ አንዲባአ ትባላለች፤ ይህችውም የከነዓን ሴት ናት። የሦስተኛው የሌዊ ሚስት ስምዋ ሚልካ ይባላል፤ እርስዋም ከታራ ልጆች ወገን ከአራም ልጆች የተወለደች ናት። 27የአራተኛው የይሁዳ ሚስት ስምዋ ቤተ ሱኤል ይባላል፤ እርስዋም የከነዓን ሴት ናት። የአምስተኛው የይሳኮር ሚስትም ስምዋ ሒዛቃ ይባላል። 28የስድስተኛው የዛብሎን ሚስትም ስምዋ ኒኤሚን ይባላል። የሰባተኛው የዳን ሚስትም ስምዋ ኤግላ ይባላል። የስምንተኛው የንፍታሌም ሚስት ስምዋ የመስጴጦምያ ሴት የምትሆን ራሱኡ ናት። 29የዘጠነኛው የጋድ ሚስትም ስምዋ ሚካ ይባላል። የዐሥረኛው የአሴር ሚስትም ስምዋ ኢዮና ይባላል። የዐሥራ አንደኛው የዮሴፍ ሚስትም ስምዋ አስኔት ይባላል። ይህችውም የግብፅ ሴት ናት። 30የዐሥራ ሁለተኛው የብንያምም ሚስት ስምዋ ኢዮሳካ ይባላል። ስምዖንም ተመልሶ ከመስጴጦምያ እንደ ወንድሞቹ ሁለተኛ ሚስት አገባ።