1ይህ ወር በባተ በዐሥራ አምስተኛው ቀን፥ ከላሞች ወገን ዐሥራ አራት ፍሪዳዎችን፥ ሃያ ስምንት የበግ ሙክቶችን፥ አርባ ዘጠኝ በጎችን፥ ዘጠና ስድስት የበግ ጠቦቶችን፥ ሃያ ዘጠኝ የፍየል ጠቦቶችን ለሚቃጠልመሥዋዕት አቀረበ፤ የተወደደ ቍርባንም አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ለበጎ መዓዛ ወደ መሠዊያው አገባ። 2ዐሥራትም ያወጣ ዘንድ ከተሳለው ስእለት ከመሥዋዕታቸው ጋር ያቀረበው መባ ይህ ነው። የመጠጡም ቍርባን ከዚህ ጋር አንድ ነው። 3እሳት በበላው ጊዜም በእሳቱ ላይ ነጭ ዕጣንን ያጥን ነበር። ስለ ድኅነት መሥዋዕትም አራት ፍሪዳዎችን፥ አራት የበግ ሙክትቶችን፥ አራት በጎችን፥ አራት የፍየል ሙክቶችን፥ ዓመት የሆናቸውን ሁለት የበግ ጠቦቶችን፥ ሁለት የፍየል ጠቦቶችንም ያቀርብ ነበር። በየዕለቱ ሰባት ቀን እንዲህ ያደርግ ነበር። 4እርሱም ከቤተ ሰቦቹና ከልጆቹ ሁሉ ጋር ደስ ብሎት ሰባት ቀን በዚያ ይበላ ነበር። ከክፉ ሁሉ ያዳነውን፥ የለመነውንም የሰጠውን እግዚአብሔርን ፈጽሞ ያመሰግነው ነበር። ንጹሕ ከሆነውም ከብት ሁሉ ዐሥራት አወጣ። 5የሚቃጠል መሥዋዕትም አደረገ፤ ንጹሕ ያልሆነውን እንስሳም ለልጁ ለሌዊ ሰጠው። የሰውንም ወገን ሁሉ ሰጠው። 6ሌዊም ከዐሥሩ ወንድሞቹ ተለይቶ በአባቱ በያዕቆብ ፊት በቤቴል አገለገለ። 7በዚያም ካህን ሆኖ ኖረ፤ ያዕቆብም ስእለቱን ሰጠው፥ ዳግመኛም ለእግዚአብሔር እንደዚሁ ዐሥራትን ሰጠ። ይህንም ቀደሰው፤ ለእርሱም የተቀደሰ ሆነ። 8ስለዚህ ነገር ዐሥራትን ለማውጣት፤ ከዓመት እስከ ዓመት ስሙ ይጠራበት ዘንድ በተመረጠ በቅዱስ ቦታ ዳግመኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመብላት ሥርዐት ሆኖ በሰማይ ጽላት ተወስኖአል። 9ለዚህም ሕግ ለዘለዓለሙ የተወሰነ ዘመን የለውም፤ ይኸውም ሥርዐት ከዓመት እስከ ዓመት ሊያደርጉት፥ ዳግመኛ በእግዚአብሔር ፊት በተመረጠ ቦታ ሊበሉት በሰማይ ጽላት የተጻፈ ነው። 10የዓመቱ አዝመራ እስከሚደርስበት ወራት ድረስ ዘሩ እሰከ ዓመት ድረስ ይበላልና፤ ከዚህም ዓመት ለሚመጣው ዓመት ከእርሱ ማትረፍ የለም፤ ወይኑም ወይን እስከሚደርስበት ወራት፥ ዘይቱም ዘይት እስከሚደርስበት ወራት ይበላልና ማትረፍ የለም። 11ከእርሱም የሚተርፈውና የደለበው ሁሉ የረከሰ ይሁን፤ የረከሰም ሆኖአልና በእሳት ይቃጠል። እንደዚሁ በቤተ መቅደስ ሆነው በአንድነት ይብሉት፤ አያድልቡት። 12የበጉና የላሙ ዐሥራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። ስለ ዐሥራቱም የሚሆነው እንደዚሁ በሰማይ ጽላት ተወስኖአልና፥ ተጽፎአልምና ካህናቱ ከዓመት እስከ ዓመት በፊቱ የሚበሉት ይሁን። 13በሁለተኛዪቱ ሌሊት፥ ይህም ወር በባተ በሃያ ሁለተኛው ቀን ያዕቆብ ያን ቦታ ይሠራ ዘንድ፥ ቅጥሩንም ሠርቶ ይቀድሰው ዘንድ፥ ለእርሱም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ፥ ከእርሱም በኋላ ለልጆቹ እስከ ዘለዓለም ድረስ የተቀደሰ ያደርገው ዘንድ መከረ። 14እግዚአብሔርም በሌሊት ተገለጠለት ባረከውም፦ እንዲህም አለው፥ “ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል።” 15ዳግመኛም አለው፥ “ሰማይንና ምድርን የፈጠርሁ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ አከብርሃለሁ፥ እጅግ በጣምም አበዛሃለሁ። 16ነገሥታቱም ከአንተ ይወለዳሉ፤ በቦታውም ሁሉ ይገዛሉ፤ የሰው ልጅም የረገጠውን ቦታ ሁሉ ይገዛሉ፥ ከሰማይ በታች ያለ ሀገርን ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ እንደ ወደዱም አሕዛብን ሁሉ ይገዛሉ። 17ከዚህም በኋላ ሀገሪቱን ሁሉ እጅ ያደርጋሉ፤ ለዘለዓለምም ይወርሱአታል።” ከእርሱም ጋር ተነጋግሮ ከጨረሰ በኋላ ከእርሱ ዘንድ ወጣ። ወደ ሰማይም እስኪወጣ ድረስ ያዕቆብ ያይ ነበር። 18እርሱም በሌሊት ራእይ አየ፤ እነሆ፥ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየ፤ እነሆ፥ ሰባት ሰሌዳዎች በእጁ ነበሩ። 19ለያዕቆብም ሰጠውና አነበባቸው፤ በዓለሙ ሁሉ ለልጆቹና ለእርሱ የሚሆን በውስጣቸው የተጻፈውን ሁሉ አነበበ። በሰሌዳዎቹም የተጻፈውን ሁሉ አሳየው። 20እንዲህም አለው፥ “ይህን ቦታ አትሥራ፥ የዘለዓለም መቅደስንም አታድርገው፤ ይህ ቦታ አይደለምና በዚህ ቦታ አትደር። ወደ አባትህ ወደ አብርሃም ቤት ሂድ፤ አባትህ እስከሚሞትባት ቀን ድረስ በዚያ በአባትህ በይስሐቅ ቤት ኑር፤ በግብፅ ሳለህ በሰላም ትሞታለህና። 21በዚህች ምድር ከአባቶችህ መቃብር ከአብርሃምና ከይስሐቅ ጋር በክብር ትቀበራለህና አትፍራ፤ ሁሉ እንዳየኸውና እንዳነበብኸው እንደዚሁ ይደረጋልና። 22አንተም ያየኸውንና ያነበብኸውን ሁሉ ጻፍ።” ያዕቆብም፥ “ያነበብሁትንና ያየሁትን ሁሉ እንዴት አስታውሳለሁ?” አለ። ጌታም፥ “እኔ ሁሉን አሳስብሃለሁ” አለው። 23ከእርሱም ወጣ፥ ያዕቆብም ከእንቅልፉ ነቃ፤ ያነበበውንና ያየውንም ሁሉ ዐሰበ። ያየውንና ያነበበውንም ነገር ሁሉ ጻፈ። 24ዳግመኛም በዚያ አንድ ቀን በዓል አደረገ፥ በቀደሙት ዕለታት እንደሚሠዋው ሁሉ አድርጎ ሠዋባት። ያች ቀን ተጨምራለችና ስምዋን ተውሳክ አላት። 25የቀደሙትንም ቀኖች በዓል ብሎ ጠራቸው። እንዲህም ትሆን ዘንድ እንዲህ ይታይ ነበር፥ ይህም በሰማይ ጽላት ተጽፎአል። 26ስለዚህም ነገር በዓል ያደርጋት ዘንድ፥ በዓል በሚደረግባቸው በሰባቱ ቀኖች ላይ እርስዋን ይጨምር ዘንድ ተገለጠለት። በዓመት እንደሚመላለሱ ቀኖች ቍጥር በሰላም መሥዋዕት የሚሠዋባትና በዓል የሚደረግባት ቀን ናትና ስምዋ ተውሳክ ተባለ። 27ይህ ወር በባተ በሃያ ሦስት ቀን በዚያ ሌሊት የርብቃ ሞግዚት ዲቦራ ሞተች። ከከተማውም በታች በወንዙ አጠገብ በግራር ሥር ቀበሩአት። 28የዚያንም ወንዝ ስም “ፈለገ ዲቦራ” አለው። ግራሩንም “የዲቦራ ልቅሶ ግራር” አለው። 29ርብቃም ተመልሳ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ቤት ሄደች። ያዕቆብም አባቱ እንደሚወድደው አድርጋ ለአባቱ ምግብ ታዘጋጅ ዘንድ የፍየሎችን ሙክቶችና የበጎችንም ሙክቶች፥ በጎችንም በእጅዋ ላከ። 30ክብራታን ወደምትባል ሀገር እስኪቀርብ ድረስ ከእናቱ ኋላ ሄደ። በዚያም አደረ። 31ራሔልም ሌሊት ወንድ ልጅ ወለደች። በወለደችውም ጊዜ ተጨንቃ ነበርና ስሙን የኀዘኔ ልጅ አለችው። 32አባቱ ግን ስሙን ብንያም አለው። በዚህ ኢዮቤልዩ በስድስተኛው ሱባዔ በአንደኛው ዓመት ስምንተኛው ወር በባተ በዐሥረኛው ቀን ራሔል ሞተች። ኤፍራታ በምትባል ምድርም በዚያ ተቀበረች፤ ይህችውም ቤተ ልሔም ናት። 33ያዕቆብም በጎዳና ዳር ባለ በራሔል መቃብር ላይ ሐውልትን አቆመ። 34ያዕቆብም ሄዶ በመግደላ ድራኤፍ ደቡብ አደረ ከሚስቱ ከልያም ጋር ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ሄዱ። 35በዐሥረኛው ወር መባቻ ሮቤል የአባቱ ዕቅብት የምትሆን የራሔልን አገልጋይ ባላንን ተሰውራ በውኃ ስትታጠብ አይቶ ወደዳት። 36በሌሊትም ተሰውሮ ወደ ባላን ቤት ገባ፤ እርስዋም በቤቷ ብቻዋን በአልጋዋ ላይ ተኝታ አገኛት። ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ በነቃችም ጊዜ እነሆ፥ ሮቤል ከእርስዋ ጋር በመኝታዋ ተኝቶ አየች። 37እጅዋንም ዘርግታ ያዘችውና ጮኸች፤ ሮቤል እንደ ሆነም ዐወቀች። ከእርሱም የተነሣ አፈረች። ከእርሱም ላይ እጅዋን አነሣች። እርሱም ሸሸ። በዚህም ነገር ፈጽማ ታለቅስ ነበር፤ ለማንም ሰው አልተናገረችም። 38ያዕቆብም መጥቶ በፈለጋት ጊዜ፥ “ሮቤል ስላሳደፈኝ ሌሊትም ስለደረሰብኝ ከአንተ ተለይቻለሁና ለአንተ የምገባ አይደለሁም፤ እኔ ግን እንቅልፍ ይዞኝ ነበር፤ ልብሴን ገልጦ ከእኔ ጋር እስኪተኛ ድረስ አላወቅሁትም ነበር” አለችው። 39ከባላን ጋር ተኝቶአልና፥ የአባቱንም ኀፍረት ገልጦአልና ያዕቆብ በሮቤል ፈጽሞ ተቈጣ። 40ሮቤል አሳድፎአታልና ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ወደ እርስዋ አልቀረበም። የአባቱን ኀፍረት የገለጠ ሰው ሁሉ ርኩስ ነው፤ ነገሩ እጅግ ክፉ ነውና፥ በእግዚአብሔርም ፊት የተናቀ ነውና። 41ስለዚህ ነገር ሰው ከአባቱ ሚስት ጋር እንዳይተኛ፥ የአባቱንም ኀፍረት እንዳይገልጥ በሰማይ ጽላት ተጽፎአል፤ ርኩስም ስለ ሆነ ሞትን ይሙት። 42ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ ሰው ጐስቋላ ነው። ሴትም ብትሆን ጐስቋላ ናት። በምድር ርኩስ ሥራን ሠርተዋልና። እርሱም እርስዋም ይሙቱ። በአምላካችን ፊት ለአገዛዝ በመረጠው ወገን መካከል ርኵሰት አይሁን። 43ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ ሰው የአባቱን ኀፍረት ገልጦአልና የተረገመ ይሆን ዘንድ ዳግመኛ ተጽፎአል። 44የእግዚአብሔር ወዳጆች ሁሉ፥ “ይሁን፥ ይሁን” አሉ። 45አንተም ሙሴ ይህን ነገር ይጠብቁ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፥ ለሞት የሚያበቃ ፍርድ ነውና፥ የረከሰም ነውና። 46ይህን ክፉ ሥራ ለሠራ ሰው ከመገደልና በድንጋይ ከመደብደብ፥ ከእግዚአብሔርም ሕዝብ መካከል ተለይቶ ከመጥፋት በቀር በኀጢአቱ ይቅርታና ስርየት የለውም፤ በእስራኤልም መካከል ይህን ሥራ የሚሠራ ማንኛውም ሰው የተናቀና የተጠላ ስለ ሆነ በምድር አንድ ቀን እንኳ መኖር አይገባውም። 47ለእርስዋ ባልዋ አባቱ ያዕቆብ በሕይወት ሳለ ከአባቱ ዕቅብት ጋር ከተኛ በኋላ ለሮቤል ሕይወትና ስርየት ነበረው አይበሉ። 48በዚያን ጊዜ ለሁሉ ሥርዐትና ሕግ፥ ፍርድም አልተሠራምና፤ ነገር ግን በዘመናችሁ የዘመናትና የቀናት ሕግ እንደ ዘለዓለም ሆኖ ለዘለዓለም ትውልድ ተሠርቶአል። 49ለዚህም ሕግ የዘመን ፍጻሜ የለውም። በሕዝቡ መካከል ሁለቱ ሁሉ በአንድነት ይጠፉ ዘንድ፥ ይህችን ኀጢአት በሠሩባት ቀን ይገድሉአቸው ዘንድ ነው እንጂ ለኀጢአታቸው ምንም ስርየት የለውም። 50አንተም ሙሴ ለእስራኤል ጻፍላቸው፤ ይጠብቁአት፤ እንደዚህ ያለ ሥራም አይሥሩ፤ ለሞት የሚያበቃ በደልንም አይበድሉ። ፊት አይቶ የማያዳላ፥ መማለጃን የማይቀበል እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር እውነተኛ ፈራጅ ነውና። 51ይሰሙ ዘንድ፥ ይጠብቁም ዘንድ፥ ከእነርሱም ይለዩ ዘንድ ከምድር ፈጽመው እንዳይጠፉ ይህን የሥርዐት ነገር ንገራቸው። ዓለም በፈጣሪያችን ፊት ይህችን ኀጢአት ለሚሠሩአት ሰዎች ሁሉ የተጠላ፥ የተናቀና የተነቀፈ ነውና፥ በምድር ላይ ከሚሠሩት ከዝሙት የበለጠ ታላቅ ኀጢአት የለምና። 52እስራኤል ለእግዚአብሔር የተለየ ወገን ነውና፥ ለአምላኩም የተለየ ወገን ነውና፥ የክህነትና የመንግሥት ወገን ነውና፥ ገንዘብም ነውና። በቅዱስ ሕዝብ መካከል እንዲህ ያለ ኀጢአት ሊታይ አይገባም። 53በዚህ በስድስተኛው ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ያዕቆብና ልጆቹ ሄደው በአባቱ በይስሐቅና በእናቱ በርብቃ አቅራቢያ በአብርሃም ቤት አደሩ። 54የያዕቆብም ልጆች ስማቸው ይህ ነው፤ መጀመሪያው ሮቤል ይባላል፤ ሁለተኛው ስምዖን ይባላል፤ ሦስተኛው ሌዊ ይባላል፤ አራተኛው ይሁዳ ይባላል፤ አምስተኛው ይሳኮር ይባላል፤ ስድስተኛው ዛብሎን ይባላል፤ እነዚህ የልያ ልጆች ናቸው። 55የራሔልም ልጆች ዮሴፍና ብንያም ናቸው። 56የባላንም ልጆች ዳንና ንፍታሌም ናቸው። 57የዘለፋም ልጆች ጋድና አሴር ናቸው። 58ልያ ለያዕቆብ የወለደቻት ሴት ልጅ ዲና ብቻ ናት። ሄደውም ለያዕቆብና ለርብቃ ሰገዱ። 59ባዩአቸውም ጊዜ ያዕቆብንና ልጆቹን ሁሉ መረቁአቸው። የትንሹን ልጁን የያዕቆብን ልጆች አይቶአልና ይስሐቅ ፈጽሞ ደስ ብሎት መረቃቸው።