1በሰባተኛውም ወር መባቻ ወደ ቤቴል ወጣ። በዚያ በተኛበትም ቦታ መሠዊያ ሠራ። በዚያም ሐውልት አቆመ። 2ወደ እርሱ፥ ወደ መሥዋዕቱም ይመጣ ዘንድ ያዕቆብ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ላከ፤ ወደ እናቱ ወደ ርብቃም ላከ። 3ይስሐቅም፥ “ልጄ ያዕቆብ ወደ እኔ ይምጣ፤ ሳልሞትም ልየው” አለ። 4ያዕቆብም ወደ አባቱ ይስሐቅና ወደ እናቱ ወደ ርብቃ ወደ አባቱ ወደ አብርሃም ቤት ሄደ። 5ከልጆቹም ሁለቱን ልጆች ይሁዳንና ሌዊን ከእርሱ ጋር ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅና ወደ እናቱ ወደ ርብቃ መጣ። 6ርብቃም፥ “እነሆ፥ ልጅሽ ያዕቆብ ደረሰ” እንደ አሉአት በሰማች ጊዜ ልቡናዋን ደስ ብሎአታልና ያዕቆብን አቅፋ ትስመው ዘንድ ከአንዱ ግንብ ወደ ሌላው ግንብ በር ወጣች። 7ሳመችው፤ ሁለቱንም ልጆቹን ባየች ጊዜ ዐወቀቻቸው። “ልጄ ሆይ፥ እነዚህስ ልጆችህ ናቸውን?” አለችው፤ አቅፋም ሳመቻቸው። እንዲህም ብላ መረቀቻቸው፥ “የአብርሃም ዘር በእናንተ ይክበር፤ እናንተም በምድር ላይ ለበረከት ትሆናላችሁ።” 8ያዕቆብም አባቱ ይስሐቅ ወደ ተኛበት እልፍኝ ገባ። ሁለቱም ልጆቹ ከእርሱ ጋር ገቡ። 9የአባቱን እጅ ይዞ ዘንበል ብሎ ሳመው። ይስሐቅም በልጁ በያዕቆብ አንገት ላይ ተጠምጥሞ አንገቱን እቅፍ አድርጎ አለቀሰ። የይስሐቅንም ዐይኖች ሸፍኖአቸው የነበረው ተገፈፈ። 10የያዕቆብን ሁለቱን ልጆቹን ይሁዳንና ሌዊን አይቶ፦ እንዲህ አለ፥ “ልጄ ሆይ፥ ይመስሉሃልና እነዚህ ልጆችህ ናቸውን?” እርሱም በእውነት ልጆቹ እንደ ሆኑ ነገረው፤ “በእውነት ልጆች እንደ ሆኑ በእውነት አየህ” አለው። 11ወደ እርሱም ቀረቡ፤ መለስ ብሎም ሁሉን በአንድነት አቅፎ ሳማቸው፤ ትንቢት የሚያናግር መንፈስ ቅዱስ በአፉ አናገረው። ሌዊንም በቀኝ እጁ ያዘው፤ ይሁዳንም በግራ እጁ ያዘ። 12በመጀመሪያ ወደ ሌዊ ተመልሶ አስቀድሞ ይመርቀው ጀመር። እንዲህም አለው፥ “እርሱ እግዚአብሔር ይባርክህ፥ የዓለማት ሁሉ ጌታ አንተንና ልጆችህን በዓለሙ ሁሉ ያክብር፤ ክብር ሊሆንህ እግዚአብሔር ለአንተ ገናናነትን ይስጥህ፤ ለልጆችህም ይስጣቸው። 13አንተን ወደ እርሱ ያቅርብህ፤ በቤተ መቅደስም ያገለግሉት ዘንድ ከሰው ሁሉ ለይቶ ልጆችህን ወደ እርሱ ያቅርባቸው፤ እንደ መላእክተ ገጽና እንደ ቅዱሳንም እንደ እነርሱ ልጆችህ ለክብር፥ ለጌትነትና ለምስጋና ይሁኑ፤ በዓለሙ ሁሉ ከፍ ከፍ ያድርጋቸው፤ ለያዕቆብም ልጆች ወገኖች ሁሉ መሳፍንትና መኳንንት፥ አለቆችም ይሆናሉ። 14የእግዚአብሔርንም ቃል በእውነት ይናገራሉ፤ ፍርዱንም ሁሉ በእውነት ይፈርዳሉ፤ ለያዕቆብ መንገዶችን፥ ለእስራኤልም ፍለጋዬን ይናገራሉ፤ የተወዳጁን ዘር ሁሉ ይመርቁ ዘንድ የእግዚአብሔር በረከት በአፋቸው ይነገራል። 15“አንተንም እናትህ ስምህን ሌዊ ብላ ጠራች። ስምህንም በእውነት ጠራች፤ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ትሆናለህ፤ ከያዕቆብ ልጆች ሁሉ ጋር አንድ ትሆናለህ፤ ማዕዱ ለአንተ ትሁን። 16አንተና ልጆችህ ብሉአት፤ ማዕድህም ለልጅ ልጅ ሁሉ የመላች ትሁን፤ በዓለሙ ሁሉ እህልህ አይጕደል፤ የሚጠሉህም ሰዎች ሁሉ በፊትህ ይውደቁ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ፈጽመው ይጥፉ፤ የሚባርክህ የተባረከ ይሁን፤ የሚረግሙህም ሕዝብ ሁሉ የተረገሙ ይሁኑ።” 17ይሁዳንም እንዲህ አለው፥ “የሚጠሉህን ሰዎች ሁሉ ታጠፋቸው ዘንድ እግዚአብሔር ኀይልንና ጽናትን ይስጥህ፤ አንተ ገዥ ሁን፤ ከልጆችህም አንዱ ለያዕቆብ ልጆች ገዥ ይሁን፤ ስምህና የልጆችህ ስም በሀገሩና በከተማው ሁሉ ሲጠራ የሚኖር ይሁን። 18ያንጊዜ አሕዛብ ከፊትህ የተነሣ ይፈራሉ፤ አሕዛብም ሁሉ ይታወካሉ፤ ሕዝቡም ሁሉ ይሸበራሉ፤ የያዕቆብ ረድኤት በአንተ ይደር፤ የእስራኤልም ድኅነት በአንተ ትገኛለች። 19እውነተኛ ክብር በአለው ዙፋንም በተቀመጥህ ጊዜ ለተወዳጁ ልጆች ዘር ታላቅ ሰላም ይሆናል፤ የሚመርቅህ ሰው የተመረቀ ነው፤ የሚጠሉህና መከራንም የሚያጸኑብህ፥ የሚረግሙህም ሁሉ ከምድር ፈጽመው ይጥፉ፤ የተረገሙም ይሁኑ።” 20ዳግመኛ ተመልሶ እቅፍ አድርጎ ሳመው፤ በእውነት የወለዳቸውን የልጁ የያዕቆብን ልጆች አይቶአልና ፈጽሞ ደስ አለው። 21ከእግሮቹ መካከል ወጥቶ በግንባሩ ወድቆ ሰገደለት፥ ባረካቸው፤ በአባቱ በይስሐቅም አጠገብ ተቀመጠ፤ በዚያችም ሌሊት ደስ ብሎአቸው በሉ፥ ጠጡም። 22ሁለቱንም የያዕቆብን ልጆች አንዱን በቀኙ፥ አንዱንም በግራው አቆመ፤ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። 23ያዕቆብም እግዚአብሔር ለእርሱ ብዙ ይቅርታ እንደ አደረገ፥ ጎዳናውን ሁሉ እንዳቀናለት፥ ከክፉም ነገር ሁሉ እንደ ጠበቀው ሌሊት ለአባቱ ሁሉን ነገረው። 24ይስሐቅም ከባሪያው ከይስሐቅ ልጅ ቸርነቱንና ይቅርታውን ያላራቀ የአባቱን የአብርሃምን አምላክ አመሰገነው። 25ያዕቆብም ሲነጋ ለአባቱ ለይስሐቅ ለእግዚአብሔር የተሳለውን ስእለት፥ ያየውንም ራእይ፥ መሠዊያውንም እንደ ሠራ፥ በእግዚአብሔርም ፊት እንደ ለመነው ለማድረግ፥ ለመሥዋዕት የሚሆነውም ሁሉ እንደ ተዘጋጀ፥ በበቅሎውም አስቀምጦ ይወስደው ዘንድ እንደ መጣ ነገረው። 26ይስሐቅም ልጁን ያዕቆብን እንዲህ አለው፥ “አርጅቻለሁና ከአንተ ጋር መምጣት አልችልም፤ ጎዳናውንም መታገሥ አልችልም፤ ልጄ ሆይ፥ በሰላም ሂድ፥ እኔ አሁን የመቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሰው ነኝና እንግዲህ ወዲህ መሄድ አልችልም። 27እናትህን በበቅሎ አስቀምጠህ ከአንተ ጋር ይዘሃት ሂድ፤ ልጄ ሆይ፥ ስለ እኔ እንደ መጣህ አውቃለሁ፤ በሕይወትህ ሳለህ እኔን ያየህባት፥ እኔም በሕይወት ሳለሁ አንተን ያየሁባት ይህች ቀን የተባረከች ትሁን። 28ልጄ ሆይ፥ ተዘጋጅተህ የተሳልኸውን ስእለትህን ስጥ፤ ስእለት ቢያስቀሩት በፍዳ ይመረምራልና ስእለትህን አታዘግይ። 29አሁንም ታደርጋት ዘንድ ቸኩል፤ ሁሉን የፈጠረ እግዚአብሔር የተሳልኸውን ስእለት ወድዶ ይቀበልህ።” 30ርብቃንም፥ “ከልጅሽ ከያዕቆብ ጋር ሂጂ” አላት። ርብቃም ከልጅዋ ከያዕቆብ ጋር ሄደች፤ ዲቦራም ከእርስዋ ጋር ሄደች፤ ወደ ቤቴልም ደረሱ። 31ያዕቆብም ስእለቱን፥ አባቱ ይስሐቅም ከሁለቱ ልጆቹ ከይሁዳና ከሌዊ ጋር የመረቀውን ምርቃት አስቦ ደስ ብሎት የአባቶቹን የይስሐቅንና የአብርሃምን አምላክ አመሰገነው። 32“አሁንም በሁሉ አምላክ ፊት ለዘለዓለም ተስፋ እንዳለኝ፥ ለልጆችም ተስፋ እንዳላቸው ዐወቅሁ” አለ። 33ስለ ሁለቱ ሁሉ እንደዚህ ሠርቶአል። ይስሐቅ እንደ መረቃቸው ለዘለዓለም ምስክር ሊሆን በሰማይ ጽላት ይጽፉላቸዋል፤ በዚያችም ሌሊት በቤቴል አደረ። 34ሌዊም እንደ ሾሙት፥ ለልዑል አምላክም እርሱን አገልጋይ እንደ አደረጉት፥ ልጆቹንም እስከ ዘለዓለም ድረስ አገልጋዮች እንደ አደረጉአቸው ሕልም አየ። 35ከእንቅልፉም ተነሥቶ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ይህ ወር በባተ በዐሥራ አራተኛው ቀን ያዕቆብ በጥዋት ገሠገሠ። 36ከእርሱም ጋር ከመጣው ሁሉ ዐሥራት አወጣ፥ ከሰው ጀምሮ እስከ ከብት ድረስ፥ ከወርቅም ጀምሮ እስከ ሌላው ገንዘብ ሁሉ፥ እስከ ልብስም ድረስ፥ ከሁሉም ዐሥራት አወጣ። 37በዚያም ወራት ራሔል ልጅዋን ብንያምን ፀነሰች፤ ያዕቆብም ከእርሱ ጀምሮ ልጆቹን ቈጠረ። 38ዕጣም ጣለ፤ የእግዚአብሔርም ዕጣ በሌዊ ወጣ፤ አባቱም የክህነት ልብስን አለበሰው፤ እጁንም ቀባው።