1በዚያም የያዕቆብን ልጅ ዲናን ወደ ሀገሩ ገዥ ወደ ኤውያዊው ሰው ወደ ኤሞር ልጅ ወደ ሴኬም ቤት ነጥቀው ወሰዱአት። ከእርስዋም ጋር ተኛ፤ አስነወራትም፤ እርስዋም የዐሥራ ሁለት ዓመት ትንሽ ልጅ ነበረች። ሚስትም ሆና ትሰጠው ዘንድ ከአባቷና ከወንድሞችዋ ማለደ። 2ያዕቆብም ተቈጣ። እኅታቸውንም ዲናን አስነውረዋታልና ልጆቹ በሰቂማ ሰዎች ተቈጡ፤ ከእነርሱም ጋር በተንኰል ተናገሩ፤ አታልለውም በዘበዙአቸው። 3ስምዖንና ሌዊ ድንገት ወደ ሰቂማ ገብተው በሰቂማ ሰዎች ሁሉ ቅጣትን አደረጉ። 4በውስጥዋም ያገኙትን ሰው ሁሉ ገደሉ። አንድ ሰው ስንኳን አላስቀሩም። ቈስለውም ሳሉ ሁሉን ገደሉ፤ እኅታቸውን ዲናን አስነውረዋልና። 5ከእንግዲህ ወዲህ ከዛሬ ጀምሮ የእስራኤልን ልጅ ለማስነወር እንዲህ አታድርጉ። በእስራኤል ኀፍረትን ስለአደረጉ የሰቂማን ሰዎች ሁሉ በሰይፍ ያጠፏቸው ዘንድ በሰማይ ጽላት በእነርሱ ቅጣት ተጽፎአልና። 6በሰይፍ ያጠፉአቸው ዘንድ፥ በእነርሱም ላይ ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ፥ የእስራኤልን ድንግል ማስነወር በእስራኤል ዘንድ ከእንግዲህ ወዲህ እንዲህ እንዳይደረግ እግዚአብሔር በያዕቆብ ልጆች እጅ ጣላቸው። 7በእስራኤል ዘንድ ልጁንም ቢሆን፥ እኅቱንም ቢሆን ከአሕዛብ ልጆች ለተወለደ ሰው ሁሉ ይሰጥ ዘንድ የወደደ ሰው ቢኖር፥ ሞትን ይሙት። ኀጢአትን ሠርቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ኀፍረትን አድርጎአልና በድንጋይ ደብድበው ይግደሉት። 8ሴቲቱንም የአባቷን ወገን ስም አስነቅፋለችና በእሳት ያቃጥሏት፤ ከእስራኤልም ተለይታ ትጥፋ። እስራኤል ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነውና በምድር ትውልድ ዘመን ሁሉ በእስራኤል ዘንድ ሴሰኛ ኀጢአተኛም አይገኝ። 9ነውር የሠራ ሰው ሁሉ ሞትን ይሙት፤ በድንጋይም ይደብድቡት። ስለ እስራኤልም ልጆች ሁሉ በሰማይ ጽላት እንዲህ ተሠርቶአል፤ ተጽፎአልምና የእስራኤልን ልጅ የሚያስነውር ሁሉ ሞትን ይሙት፤ በድንጋይም ይደብድቡት። 10ለዚህም ሕግ የተወሰነ ዘመን የለውም፤ የሚተውበትም የለም። ልጁን ለጣዖት ሰጥቶአልና፥ ራሱንም ለማሳደፍ እግዚአብሔርን በድሎአልና በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ልጁን ያስነወረ ሰው ይጠፋል እንጂ ይቅር የሚባልበት የለም። 11አንተም ሙሴ! የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። ከልጆቻቸውም ለአሕዛብ እንዳያጋቡ፥ ከአሕዛብም ልጆች እንዳያገቡ በእነርሱ ላይ አዳኝባቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት የተናቀ ነውና። 12ስለዚህ ነገር የሕጉን ነገር፥ በዲና ላይ ያደረጉትን የሰቂማን ሰዎች ሥራ ሁሉ፥ የያዕቆብም ልጆች፥ “ለእኛ ስድባችን ነውና እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው አንሰጥም” ብለው እንደ ተናገሩ ጻፍሁልህ። 13ልጃቸውን ለአሕዛብ ልጆች ለሚሰጡ፥ ከአሕዛብም ልጆች ሚስትን ለሚያገቡ ለእስራኤል ስድብ ነውና፥ ርኩስም ነውና፥ ለእስራኤልም የተናቀ ነውና። 14ከአሕዛብም ልጆች ሚስት ያለው፥ ከልጆቹም ከአሕዛብ ወገን ለተወለደ ሰው የሰጠ እስራኤል ከዚህ ኀጢአት አይነጻም። በመቅሠፍት ላይ መቅሠፍት፥ በመርገም ላይ መርገም፥ ቅጣትም፥ መቅሠፍትም፥ መርገምም ሁሉ ይመጣባታልና። 15ይህንም ነገር ቢያደርግ ኀጢአት ከሚሠሩ ከእነዚህ ወገኖች በዐይኖቹ አይቶ ቸል ቢል፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ ከሚያጐሳቍሉ፥ የከበረ ስሙንም ከሚያሳድፉ ወገን አይቶ ቸል ቢል፥ ስለዚች ኀጢአትና ስለዚች ሁሉ በደል ሕዝቡ ሁሉ በአንድነት ይጠፋሉ። 16ፊት መመለስ የለም። ፊት አይቶ ማድላት የለም። በጎ መዓዛ አድርጎ ይቀበለው ዘንድ መሥዋዕቱንና ቀዳምያቱን፥ ስቡንና የሚጤሰውን ከእጁ መቀበል የለም። 17ወንድም ቢሆን፥ ሴትም ብትሆን፥ በእስራኤል ዘንድ ሰውነቱን በኀጢአት የሚያሳድፍ አይሁን። ስለዚህ ነገር ይህችን ምስክር በእስራኤል አሰማባቸው ብዬ አዘዝሁህ። 18በሰቂማና በልጆችዋ የተደረገውን፥ በሁለቱ በያዕቆብ ልጆች ለጥፋት እንደ ተሰጠች፥ ታመው ሳሉ እንዳጠፉአቸው፥ ጽድቅ ሆኖ እንደ ተቈጠረላቸው እይ። 19እነርሱም ለጽድቅ እንደ ተቈጠሩ የሌዊም ልጅ ለክህነት እንደ ተመረጠ፥ እኛ በዘመኑ ሁሉ እንዳገለገልን፥ ሌዋውያንም በእግዚአብሔር ፊት ያገለግሉ ዘንድ እንደ ተመረጡ እይ። እውነት ነገርን ይሠራ ዘንድ፥ ፍርድንም ይፈርድ ዘንድ፥ በእስራኤል ላይ በጠላትነት ከሚነሡ ብድራትን ይመልስ ዘንድ ቀንቶአልና ሌዊ ይባረክ፤ ልጆቹ ለዘለዓለም ይባረኩ። 20በሰማይ ጽላት ምስክር ሊሆን ወደ ሁሉ አምላክ ጽድቅንና በረከትን እንዲህ ያቀርቡለታል። ሰው በሕይወት ሳለ የሠራውን ጽድቅ እናስባለን። በዓመት በዓመት በሚመላለሱ ጊዜያት ሁሉ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ያቀርባሉ። በረከት ይመጣለታል፥ ከእርሱም በኋላ ለልጆቹ። 21በሰማይ ጽላት የእግዚአብሔር ወዳጅ ደግ ሰውም ተብሎ ተጻፈ። ይህን ሁሉ ነገር ጻፍሁልህ። ኀጢአት እንዳይሠሩ፥ ከሥርዐትም እንዳይተላለፉ፥ ይሠሩአት ዘንድ፥ ይጽፉአትም ዘንድ፥ የእግዚአብሔር ወዳጆችን ሁነው ይጽፉ ዘንድ፥ የተሠራላቸውን ቃል ኪዳን እንዳያፈርሱ ለእስራኤል ልጆች ትነግር ዘንድ አዘዝሁህ። 22ቃል ኪዳኑንም ቢያፈርሱ፥ ከኀጢአት ሥራ ወገንም ሁሉ ቢሠሩ ግን ጠላቶች ሆነው በሰማይ ጽላት ይጻፋሉ፤ ከሕያዋንም መጽሐፍ ይደመሰሳሉ፤ የሚጠፉ ሰዎች በሚጻፉበትም መጽሐፍ ይጻፋሉ። ከምድር ላይ ከሚጠፉ ሰዎችም ጋር ይቈጠራሉ። 23የያዕቆብም ልጆች ሰቂማን ባጠፉበት ቀን ጽድቅንና የቀና ሥራን እንደ ሠሩ፥ በኀጢአተኞችም ብድርን እንደ መለሱ በሰማይ ጽላት ተጻፈላቸው። ለበረከትም ተጻፉ። 24እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት አወጡ። በሰቂማ ያለውንም ሁሉ፥ በጎቻቸውንም፥ ላሞቻቸውንም፥ አህዮቻቸውንም፥ ገንዘባቸውንም ሁሉ፥ መንጋቸውንም ሁሉ ማረኩ። ሁሉንም ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ አመጡ። 25በዚያ ከሚኖሩ ከከነዓናውያንና ከፍሪዛውያን የተነሣ ፈርቶአልና ሀገሩን ስላጠፉ ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ። 26በሰቂማ ዙሪያ ባሉ ሀገሮች ሁሉ የእግዚአብሔር መፈራት ሆነ። በእነርሱ ድንጋጤ ወድቆባቸዋልና የያዕቆብን ልጆች ለማሳደድ አልተነሡም። 27በወሩ መባቻ ያዕቆብ ለቤተ ሰቡ ሁሉ፥ “ከኀጢአት ንጹሓን ሁኑ፤ ልብሳችሁንም ለውጡ” ብሎ ተናገረ። 28“ከወንድሜ ከዔሳው ፊት በሸሸሁ ጊዜ ከእኔ ጋር ላለ፥ ወደዚህችም ሀገር በሰላም ለመለሰኝ ለእግዚአብሔር ወደ ጸለይሁበት ወደ ቤቴል ተነሥተን እንውጣ። 29በመካከላችሁም ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ። ልዩ የሆኑ አማልክትንም አጥፉአቸው፤ በጆሮአችሁ ያለውንም፥ በአንገታችሁም ያለውን ጌጥ አስወግዱ።” 30ራሔል ከአባቷ ከላባ የሰረቀችውን ጣዖት፥ ገንዘብዋንም ሁሉ ለያዕቆብ ሰጠች። እርሱም አቃጠለው፤ ሰበረውም፤ አጠፋውም፤ በሰቂሞን ሀገር ባለ በዮርዳኖስም በታች ቀበረው።