1ያዕቆብ በአርባ አራተኛው ኢዮቤልዩ በሁለተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ወደ ካራን ይሄድ ዘንድ ከዐዘቅተ መሐላ ወጣ። በተራራ ወዳለች ወደ ሎዛም ደረሰ። ይህችውም ቤቴል ናት። 2በዚህ ሱባዔ በመጀመሪያው ወር መባቻ በመሸ ጊዜ ወደ ቦታው ደረሰ። በዚያችም ሌሊት ከመንገዱ ወደ ምዕራብ አለፍ አለ። ፀሐይ ገብቶ ነበርና በዚያ ተኛ። ከዚያ ቦታ ድንጋዮችም አንድ ድንጋይ አምጥቶ በዚያ ዛፍ ሥር አኖረው። እርሱም ብቻውን ይሄድ ነበር። 3በዚያችም ሌሊት ተኝቶ ሳለ ሕልምን አየ። እነሆ፥ መሰላል በምድር ላይ ተተክላ ጫፍዋ እስከ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡባትና ሲወርዱባት፥ እነሆም፥ እግዚአብሔር በውስጥዋ ተቀምጦ አየ። 4ከያዕቆብም ጋር ተነጋገረ። እንዲህም አለ፥ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ ነኝ። ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ እሰጣታለሁ። ዘርህም እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል። በምዕራብና በምሥራቅ፤ በሰሜንና በደቡብ ትበዛለህ። የአሕዛብም ሀገሮች ሁሉ በአንተና በዘርህ ይባረካሉ፥ 5እነሆ፥ እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ፤ ሁልጊዜም እጠብቅሃለሁ። ያልሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልለይህምና ከሄድህበት ወደዚህች ሀገር በሰላም እመልስሃለሁ።” 6ያዕቆብም ተኝቶ ነበር። እንዲህም አለ፥ “ይህ ቦታ በእውነት የእግዚአብሔር ቤት ነው፤ እኔ ግን አላወቅሁም ነበር” አለ 7እርሱም ፈራ እንዲህም አለ፥ “ይህ ቦታ ግሩም ነው፥ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ምንም ተራ ቦታ አይደለም። ይህችም የሰማይ ደጃፍ ናት” አለ። 8ያዕቆብም ሲነጋ ገሥግሦ ተነሥቶ፥ በራስጌው ትራስ አድርጎ ያኖረውን ድንጋይ ወሰደ፤ ለምልክትም ሐውልት አድርጎ አቆመው፥ በራሱም ላይ ዘይትን አፈሰሰበት። 9የዚያንም ቦታ ስም ቤቴል አለው። ቀድሞ ግን የሀገሩ ስም ሎዛ ነበረ። 10ያዕቆብም ለእግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ፤ “እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢኖር፥ እኔ በምሄድባትም በዚህች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ እበላ ዘንድ እንጀራን ቢሰጠኝ፥ እለብስም ዘንድ ልብስን ቢሰጠኝ፥ ወደ አባቴም ቤት በሰላም ብመለስ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆነኛል። 11ይህም በዚህ ቦታ ለምልክት ሐውልት አድርጌ ያቆምሁት ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፤ ከዚህም ከሰጠኸኝ ሁሉ እኔ ለአንተ ለአምላኬ ዐሥራት እሰጣለሁ።” 12እግሩንም አንሥቶ ወደ መስጴጦምያ ወደ ምሥራቅ ወደ ርብቃ ወንድም ወደ ላባ ተጓዘ። 13ከእርሱም ጋር ኖረ፤ ስለ ልጁ ስለ ራሔልም አንድ ሱባዔ ተገዛለት፤ በሦስተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት፥ “ስለ እርስዋ ለአንተ ሰባት ዓመት የተገዛሁላትን ሚስቴን ስጠኝ” አለው። 14ላባም ያዕቆብን፥ “እኔ ሚስትህን እሰጥሃለሁ” አለው። ላባም ሰርግ አደረገ፤ ትልቂቱን ልጁን ልያን ወስዶ ለያዕቆብ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው፤ የምታገለግላት ባሪያውን ዘለፋንም ሰጣት። 15ያዕቆብ ግን ራሔል መስላዋለችና አላወቀም ነበር፤ ወደ እርስዋም ገባ፤ እርስዋ ግን እነሆ ልያ ነበረች። 16ያዕቆብም በላባ ተቈጣ። “የተገዛሁልህ ስለ ልያ ያይደለ፤ ስለ ራሔል አይደለምን? ለምን እንዲህ አደረግኸኝ? ለምንስ በደልኽኝ? ልጅህን ውሰድ፤ በእኔ ክፉ አድርገሃልና እኔ እሄዳለሁ” አለው። 17የልያ ዐይንዋ ልም ነበረና ያዕቆብ ከልያ ይልቅ ራሔልን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን መልክዋ እጅግ መልካም ነበረ። ራሔል ግን ዐይነ መልካም ነበረች፤ መልክዋም ያማረ እጅግ ደመ ግቡ ነበረች። 18ላባም ያዕቆብን እንዲህ አለው፥ “እንዲህ አይደለም፤ በሀገራችን ታላቂቱ ሳለች ታናሽቱን መስጠት የለም። ይህንም ማድረግ አግባብ አይደለም። ታላቂቱ ሳለች ታናሽቱን ልጁን የሚሰጥ እንደሌለ በሰማይ ጽላት እንዲህ ታውቆአል፤ ተጽፎአልም፤ ታላቂቱን ልጅ አስቀድሞ ይሰጣል። ከእርስዋም በኋላ ታናሽቱን ይሰጣልና። 19እንዲህ በሚያደርግም ሰው ስለ እርሱ በደልን በሰማይ ጽላት ይጽፉበታል። 20ይህ ሥራ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነውና ይህን ሥራ የሚሠራ ሰው የሚጸድቅ አይደለም። 21አንተም ለእስራኤል ልጆች፦ እጅግ ክፉ ነውና ይህን ነገር እንዳያደርጉ፤ አስቀድመው ታላቂቱን ሳይሰጡ ታናሽቱን እንዳይሰጡ እዘዝ። 22ላባም ያዕቆብን፥ “የዚህች የሰርግዋ በዓል ሰባቱ ቀን ይለፍ። ዳግመኛም ሰባት ዓመት ትገዛልኝ ዘንድ፥ በመጀመሪያው ሱባዔ እንዳደረግህ በጎችን ትጠብቅልኝ ዘንድ ራሔልን እሰጥሀለሁ” አለው። 23የልያ ሰርግ በዓል ሰባቱ ቀን በአለፈ ጊዜ ሁለተኛ ሰባት ዓመት ይገዛለት ዘንድ ላባ ለያዕቆብ ራሔልን ሰጠው። ለራሔልም የዘለፋን እኅት ባላን አገልጋይ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። ልያ በብላሽ ተሰጥታለችና ስለ ራሔል ዳግመኛ ሰባት ዓመት ተገዛ። 24እግዚአብሔርም የልያን ማኅፀን ከፈተ፤ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ወንድ ልጅን ወለደች፤ በሦስተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት በዘጠነኛው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ስሙን ሮቤል አለው። 25እግዚአብሔርም ልያ እንደምትጠላ፥ ራሔል ግን እንደምትወደድ አይቶአልና የራሔል ማኅፀን ተዘጋ። 26ያዕቆብም ዳግመኛ ወደ ልያ ገባ፤ ፀነሰች፤ ሁለተኛም ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ ስሙንም በዐሥረኛው ወር በሃያ አንደኛው ቀን ስምዖን አለው። 27በዚህ ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ያዕቆብ ዳግመኛ ወደ ልያ ገባ፤ ፀነሰች፥ ሦስተኛ ወንድ ልጅንም ወለደችለት፤ በመጀመሪያው ወር መባቻ ስሙን ሌዊ አለው። 28በዚህ ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት ያዕቆብ ዳግመኛ ወደ ልያ ገባ፤ ፀነሰች፤ አራተኛ ወንድ ልጅንም ወለደችለት፤ በአራተኛው ሱባዔ በሦስተኛው ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን በመጀመሪያው ዓመት ስሙን ይሁዳ አለው። 29እርስዋ አትወልድም ነበርና በዚህ ሁሉ ራሔል በልያ ትቀና ነበር። ያዕቆብንም፥ “ልጅ ስጠኝ” አለችው። 30ያዕቆብም፥ “የማኅፀንሽን ፍሬ የከለከልሁሽ እኔ ነኝን? እኔ አስተውሁሽን?” አላት። 31ራሔልም ልያ ለያዕቆብ አራት ልጆች ሮቤልንና ስምዖንን፥ ሌዊንና ይሁዳን እንደ ወለደች ባየች ጊዜ፥ “ወደ ባሪያዬ ወደ ባላን ግባ፤ ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልድልኛለች” አለችው። 32ያዕቆብም ወደ ባላን ገባ፤ እርስዋም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅንም ወለደችለት፤ በሦስተኛው ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት በስድስተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን ስሙን ዳን አለው። 33ያዕቆብም ዳግመኛ ወደ ባላን ገባ፤ እርስዋም ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ዳግመኛ ወንድ ልጅን ወለደችለት። በአራተኛው ሱባዔ በሁለተኛው ዓመት በሰባተኛው ወር በአምስተኛው ቀን ራሔል ስሙን ንፍታሌም አለችው። 34ልያም እንደ መከነች፥ ልጅም እንደማትወልድ በአየች ጊዜ እርስዋ በራሔል ቀናች፤ እርስዋም አገልጋይዋን ዘለፋን ለያዕቆብ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው። እርስዋም ጸነሰች፤ ወንድ ልጅንም ወለደችለት። በአራተኛው ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ስሙን ጋድ አለችው። 35ዳግመኛም ወደ እርስዋ ገባ፤ እርስዋም ፀነሰች፤ ሁለተኛ ወንድ ልጅንም ወለደችለት፤ በአራተኛው ሱባዔ በአምስተኛው ዓመት በዐሥራ አንደኛው ወር በሁለተኛው ቀን ልያ ስሙን አሴር አለችው። 36ያዕቆብም ወደ ልያ ገባ፤ እርስዋም ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ በአራተኛው ሱባዔ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር በአራተኛው ቀን ስሙን ይሳኮር አለችው፤ ለሞግዚትም ሰጠችው። 37ያዕቆብም ዳግመኛ ወደ እርስዋ ገባ፤ ፀነሰች፤ ወንድና ሴት ሁለት ልጆችን ወለደችለት። በአርባ አራተኛው ኢዮቤልዩ በስድስተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት በሰባተኛው ወር የወንዱን ስም ዛብሎን አለችው፤ የሴቲቱን ስም ዲና አለቻት። 38እግዚአብሔርም ራሔልን ይቅር አላት፤ ማኅፀንዋም ተከፈተ፤ ፀነሰችም ወንድ ልጅንም ወለደች፤ በአራተኛው ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት በአራተኛው ወር መባቻ ስሙን ዮሴፍ አለችው። 39ዮሴፍም በተወለደ ጊዜ ያዕቆብ ላባን፥ “ሚስቶችንና ልጆችን ስጠኝ፤ ወደ አባቴ ወደ ይስሐቅ ልሂድ፤ ስለ ሁለቱ ልጆችህ ለአንተ የተገዛሁላቸውን ዘመኖች ፈጽሜአለሁና ቤት እሠራለሁ፤ ወደ አባቴም ቤት እሄዳለሁ” አለው። 40ላባም ያዕቆብን፥ “በደመወዝህ ከእኔ ጋር ተቀመጥ፤ ዳግመኛም መንጋዎችን ጠብቅልኝ፤ ደመወዝህንም ውሰድ፤” አለው። 41አመድማ፥ ዥንጕርጕር፥ ነጭ ሆኖ የተወለደው ደመወዝ ሊሆነው ከፍየሉ ጠቦትና ከበጉ ጠቦት፥ በጉን ሁሉ ደመወዝ ይሰጠው ዘንድ እርስ በርሳቸው ተዋዋሉ። 42በጎቹም ሁሉ ምልክት ያለውን ሁሉ አመድማውን፥ ዥንጕርጕሩን ይወልዱ ጀመር። ዳግመኛም በጎቹ በእነዚያ አምሳል ይወልዱ ጀመር። ምልክት ያለው ሁሉ ለያዕቆብ፥ ምልክት የሌለውም ለላባ ሆነ። 43የያዕቆብም ገንዘቡ እጅግ በዛ፤ ላሙንና በጉን፥ አህያውንና ግመሉን ገዛ። ወንድ ልጅንና ሴት ልጅን ወለደ። 44ላባና ልጆቹም በያዕቆብ ቀኑበት። ላባም በጎቹን ከእርሱ ሰበሰበ፤ በክፉ አስተያየትም ይመለከተው ጀመር። 45ራሔልም ዮሴፍን ከወለደች በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ላባ በጎቹን ይሸልት ዘንድ ሄደ። የሦስት ቀን ጎዳና ያህል ከእርሱ ርቀው ነበሩ። 46ያዕቆብም ላባ በጎቹን ይሸልት ዘንድ እንደሚሄድ አይቶ ልያንና ራሔልን ጠርቶ ከእርሱ ጋር ወደ ከነዓን ይመጡ ዘንድ ከልባቸው የሚገባ ነገር ነገራቸው። በሕልም ያየውን ሁሉ፥ ወደ አባቱም ቤት ይመለስ ዘንድ የነገረውን ሁሉ ነግሮአቸዋልና። 47እነርሱም፥ “ወደምትሄድበት ቦታ ሁሉ ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት። 48ያዕቆብም የአባቱን የይስሐቅን አምላክ የአያቱን የአብርሃምን አምላክ አመሰገነው። 49ተነሥቶም ሚስቶቹንና ልጆቹን በበቅሎ አስቀመጠ፤ ገንዘቡንም ሁሉ ያዘ። ወንዙንም ተሻግሮ ወደ ገለዓድ ምድር ደረሰ። 50ያዕቆብም ለላባ አሳቡን ሰወረው፤ አልነገረውም። በአራተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሃያ አንደኛው ቀን ያዕቆብ ወደ ገለዓድ ተመለሰ። ላባም በኋላው ተከተለው። 51በሦስተኛው ወር በዐሥራ ሦስተኛው ቀን ያዕቆብን በገለዓድ ተራራ አገኘው። በሕልም ሌሊት ተናግሮታልና ላባ በያዕቆብ ላይ ክፉ ነገርን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር አላሰናበተውም፤ ላባም ለያዕቆብ ነገረው። 52በዚያም ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን ያዕቆብ ለላባ፥ ከእርሱም ጋር ለመጡ ሰዎች ሁሉ ፍሪዳ አረደ። 53አንዱም አንዱን በተንኰል እንዳይፈልገው በዚያች ቀን በገለዓድ ተራራ ያዕቆብ ለላባ ማለለት፤ ላባም ለያዕቆብ ማለለት። በዚያም ምስክር ይሆን ዘንድ ኮረብታን ሠራ፤ ስለዚህም የዚያ ቦታ ስም “ፍስሐተ ስምዕ” ተባለ፤ 54ቀድሞ የገለዓድ ምድር የራፋኢም ምድር ተብሎ ይጠራ ነበር፤ የራፋኢም ምድር ነበረና። ቁመታቸው ዐሥር ክንድ፥ ዘጠኝ ክንድም፥ ሰባት ክንድም፥ ስምንት ክንድም የሚሆኑ የራፋኢም ልጆች ተወለዱ። መኖሪያቸውም ከአሞን ልጆች ሀገር ጀምሮ እስከ ኤርሞን ተራራ ድረስ ነበር። 55የመንግሥታቸውም ከተማ ቆሬናኤምና አስጣሮስ፥ አድራኦና ሜሱር፥ ቢዖንም ነበሩ። እነርሱ እጅግ ክፉዎች ነበሩና ከክፉ ሥራቸው የተነሣ እግዚአብሔር አጠፋቸው። 56ስለ እነርሱ ፋንታ ክፉ ኀጢአተኛ የሚሆን አሞሬዎን በሀገራቸው ኖረ። ዛሬ የእነርሱን ኀጢአት ሁሉ የፈጸመ ሰው የለም። ከዚህም በኋላ በምድር የዘመን ብዛት የላቸውም። 57ያዕቆብም ላባን አሰናበተው፤ ወደ ምሥራቅ ምድር መስጴጦምያ ሄደ። ያዕቆብም ወደ ገለዓድ ምድር ተመለሰ። በዘጠነኛው ወር ከወሩም በዐሥራ አንደኛው ቀን ኢያቦቅን ተሻገረ። በዚያም ቀን ወንድሙ ዔሳው ወደ እርሱ ደረሰና ተወቃቀሱ። 58ከእርሱም ተለይቶ ወደ ሰዒር ምድር ሄደ። ያዕቆብ ግን በድንኳን አደረ። 59በዚህ ኢዮቤልዩ በአምስተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ዮርዳኖስን ተሻግሮ በዮርዳኖስ ማዶ አደረ። በኮረብታው አጠገብ ከአለ ባሕር ጀምሮ እስከ ዶታንና እስከ ቤተ ሶን ድረስ፥ እስከ ዖመ አቅራቢትም ድረስ በጎቹን ያሰማራ ነበር። ለአባቱ ለይስሐቅም ከገንዘቡ ልብሱንና ምግቡን፥ ሥጋውንና መጠጡን፥ ወተቱንና ቅቤውን፥ ዳቦውንም፥ ከቆላውም ተምር ሁሉ ይሰድ ነበር። 60ለእናቱ ለርብቃም በዐሥራ ሁለቱ ወር ጊዜዎች መካከል፥ በዘርና በአዝመራ መካከል፥ በበልግና በመከር፥ በክረምትና በበጋ መካከል በዓመት አራት ጊዜ ወደ አብርሃም ድንኳን ይልክላት ነበር። 61ይስሐቅም ከዐዘቅተ መሐላ ተመልሶ ወደ አባቱ ወደ አብርሃም ድንኳን ወጥቶ ነበረና፤ ከልጁ ከዔሳው ተለይቶ በዚያ ኖረ። 62ያዕቆብም ወደ መስጴጦምያ በሄደ ጊዜ ዔሳው ማአሊትን ሚስት አድርጎ አገባ። ይህችውም የይስማኤል ልጅ ናት። የአባቱን መንጋዎች ሁሉና ሚስቶቹንም ሰበሰበ። 63ወጥቶም በሴይር ተራራ ኖረ። አባቱን ይስሐቅንም በዐዘቅተ መሐላ ብቻውን ተወው። 64ይስሐቅም ከዐዘቅተ መሐላ ወጥቶ በኬብሮን ተራራ በአባቱ በአብርሃም ግንብ ኖረ። 65ከዚያም ያዕቆብ ለእናቱና ለአባቱ ሁሉን ይሰድ የነበረውን በየጊዜውም የፈለጉትን ሁሉ ይልክ ነበር። 66ያዕቆብንም በፍጹም ልቡናቸው፥ በፍጹም ነፍሳቸውም ይመርቁት ነበር። በስድስተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ወደ ሰቂማ ምሥራቅ ወደ ሳሌም በአራተኛው ወር በሰላም ወጣ።