1በዚህ ኢዮቤልዩ፥ በዚህ ሱባዔ በሁለተኛው ዓመት ርብቃ ልጅዋን ያዕቆብን ጠርታ ተናገረችው፤ እንዲህም አለችው፥ “ልጄ ሆይ፥ ከከነዓን ሴቶች ሁለት ሚስቶችን እንዳገባ እንደ ወንድምህ እንደ ዔሳው ከከነዓን ልጆች ሚስት አታግባ። ሥራቸው ሁሉ ዝሙትና መዳራት ነውና በሚያጸይፍ ሥራቸው ሁሉ ሰውነቴን አሳዘኗት፤ ሥራቸው ክፉ ነውና በእነርሱ ምንም እውነት የለም። 2ልጄ ሆይ፥ እኔ እጅግ እወድሃለሁ። ልቡናዬና ቸርነቴ በቀኑ ጊዜና በሌሊቱ ጥበቃ ይመርቁሃል። 3አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ስማ፤ የእኔን የእናትህንም ፈቃድ አድርግ። ከአባትህ ቤት በቀር፥ ከአባትህም ወገን በቀር ከዚህ ሀገር ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ። የምታገባትንም ከአባቴ ወገን አግባ። ልዑል አምላክም ይባርክሃል፤ ልጆችህም የእውነት ልጆች ይሆናሉ፤ ዘርህም ቅዱስ ይሆናል።” 4ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ከእናቱ ከርብቃ ጋራ ተነጋገረ፤ እንዲህም አላት፥ “እናቴ፥ እነሆ፥ እኔ የዘጠኝ ሱባዔ ዓመት ሰው ነኝ፤ ምንም ምን ሴት አላውቅም፤ አልዳሰስሁም፤ አላጨሁምም። ከከነዓን ወገን ልጆች ምንም ምን ሴት እንዳላገባ እንደ አዘዘኝ ከአባታችን ከአብርሃም ነገር የተነሣ አስባለሁና፥ ከከነዓን ልጆች ወገን ሁሉ ሚስት አገባ ዘንድ አላስብም። ከአባቴ ወገን ልጆች ከዘመዶች ሚስት አገባለሁና። 5ለወንድምሽ ለላባ ሴቶች ልጆች እንደ ተወለዱለት አስቀድሜ ሰማሁ። ከእነርሱም ሚስት አገባ ዘንድ ልቡናዬን በእነርሱ ላይ አሳረፍኩ። 6ስለዚህም እንዳልበድል፥ በመንገዴም ሁሉ በሕይወቴ ዘመን እንዳልጠፋ በሰውነቴ ተጠበቅሁ፤ ስለ መዳራትና ስለ ዝሙት አባቴ አብርሃም አብዝቶ አዝዞኛልና፥ ከዚህም ሁሉ ጋር ይህን አዝዞኛልና። ወንድሜ የሁለቱን ሚስቶቹን እኅት አንዲቱን አግባ እያለ ሲከራከረኝና ሲናገረኝ ሃያ ሁለት ዓመቱ ነው። 7“እኔም ወንድሜ እንዳደረገው አደርግ ዘንድ አልወድም፤ ባለ ዘመኔ ሁሉ ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሁሉ ሚስት እንዳላገባ፥ ወንድሜ ክፉ ሥራ እንደ ሠራ እኔም ክፉ ሥራ እንዳልሠራ በፊትሽ እምላለሁ። እናቴ፥ አትፍሪ፤ ፈቃድሽን እንደማደርግ፥ በቅንነትም እንደምሄድ፥ መንገዴንም ለዘለዓለም እንደማላጠፋ እመኚ።” 8ከዚህም በኋላ አንገቷን ወደ ሰማይ አቀናች፤ እጆችዋንም ዘረጋች፤ አፍዋንም ከፍታ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ልዑል አምላክን አመሰገነችው፤ ፍጹም ምስጋናንም አቀረበችለት። 9እንዲህም አለች፥ “ንጹሕ ልጅና ቅዱስ ዘርን ያዕቆብን የሰጠኝ አምላኬ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ስሙም ለዘለዓለም ይባረክ። የአንተ ነውና በዘለዓለም ትውልድ ሁሉ እስከ ብዙ ዘመን ድረስ ልጁ ለአንተ ይሁን። 10አቤቱ፥ ባርከው። እመርቀውም ዘንድ በአንደበቴ የጽድቅ በረከትን አኑር።” 11ያንጊዜም መንፈስ ቅዱስ ወርዶ በአንደበቷ አናገራት፤ ሁለቱን እጆችዋንም በያዕቆብ ራስ ላይ አኖረች። እንዲህም አለች፥ “የጽድቅ ጌታ፥ የዓለማት አምላክ አንተ የተመሰገንህ ነህ። 12ልጄ ሆይ ከሰው ልጅ ሁሉ ለይቶ አንተን ይባርክ። የጽድቅን መንገድ ይስጥህ፤ ለዘርህም ጽድቅን ይግለጥለት፤ በሕይወትህ ሳለህም ልጆችህን ያብዛልህ፤ በዓመቱም ወሮች ቍጥር ዐሥራ ሁለት ይሁኑ። ልጆቻቸውም ይብዙ፤ ከሰማይ ከዋክብት ይልቅ ይብዙ፤ ቍጥራቸውም ከባሕር አሸዋ ይብዛ። ለአብርሃም ይሰጣት ዘንድ፥ ከእርሱም በኋላ በዘመኑ ሁሉ ለዘሩ ይሰጣቸው ዘንድ እንደ ተናገረ ያችን የተወደደች ምድር ይስጣቸው። 13ለዘለዓለም እጅ አድርገው ይዘዋት ይኑሩ። ልጄ ሆይ፥ በሕይወት ሳለሁ የተባረከ ልጅን ልይ፤ ዘርህ ሁሉ የተባረከና፥ የተቀደሰ ዘር ይሁን፤ በሕይወቷ ሳለች የእናትህን ልቡና እንዳሳረፍህ የእናትህ ማኅፀን እንዲህ ትመርቅህ፤ ማኅፀኔና ጡቴ አንተን ይመርቁ፤ አፌና አንደበቴም ፈጽመው አንተን ያመስግኑ፤ ፈጽመህ ብዛ፤ በዓለሙም ሁሉ ምላ። ዘርህም በሰማይና በምድር ስፋት በዓለሙ ሁሉ ፍጹም ይሁን፤ ዘርህንም ደስ ይበለው። 14በታላቅ ሰላም ቀንም ሰላም ይሁንለት። ስምህና ዘርህ እስከ ብዙ ዘመን ድረስ ይኑር፤ ልዑል አምላክም አምላካቸው ይሁን፤ የጽድቅ አምላክም ከእነርሱ ጋር ይኑር። መቅደሱም በዓለሙ ሁሉ በእነርሱ ይሠራ። የሚመርቅህ የተመረቀ ይሁን፤ በሐሰት የምትረግምህ ሰውነት ሁሉ የተረገመች ትሁን፤” 15እርሷም ሳመችው፤ እንዲህም አለችው፥ “የእናትህ ልቡና እንደሚወድህ፥ ማኅፀንዋም በአንተ ደስ እንደሚለው፥ እንደሚመርቅህም የዓለሙ ሁሉ ጌታ አንተን ይውደድህ።” ከዚያ በኋላ ከመመረቅ ዝም አለች። 16በዚህ ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት ይስሐቅ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ እንዲህ አለው፥ “ልጄ ሆይ፥ እኔ አረጀሁ፤ እነሆ፥ ዐይኖች ለማየት ፈዝዘዋል፤ የምሞትባትን ቀን አላውቅም። 17አሁንም የምታድንበትን ጦርህንና ጎራንጎሬህን፥ ቀስትህንም ይዘህ ወደ ምድረ በዳ ውጣ። አደንም አድነህና አጥምደህ አምጣልኝ፤ ልጄ! ሰውነቴ የምትወድደውን መብል አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ፤ ሳልሞትም ሰውነቴ ትመርቅህ” አለው። ርብቃም ይስሐቅ ለዔሳው ሲነግረው ነገሩን ትሰማ ነበር። 18ዔሳውም አጥምዶ ይይዝና ለአባቱ ያመጣ ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ገሥግሦ ሄደ። 19ርብቃም ልጅዋን ያዕቆብን ጠርታ እንዲህ አለችው፥ “አባትህ ይስሐቅ፦ አደን አድነህ አምጥተህ የምበላውን አዘጋጅልኝ፤ በልች ሳልሞት በእግዚአብሔር ፊት ልመርቅህ ብሎ ከወንድምህ ከዔሳው ጋር ሲነጋገር ሰማሁት። 20አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እኔ የማዝዝህን ነገር ስማ፤ ወደ መንጋህ ሄደህ የአማሩ ሁለት የፍየል ጠቦቶችን አምጣልኝ፤ እንደሚወድደውም አድርጌ ለአባትህ ምግብ ላዘጋጃቸው፤ ሳይሞትም በእግዚአብሔር ፊት ይመርቅህ ዘንድ፥ ለአባትህ አቅርበህለት ይብላ፤ የተመረቅህም ትሆናለህ።” 21ያዕቆብም እናቱ ርብቃን እንዲህ አላት፥ “አባቴ ስለሚበላውና ደስ ስለሚያሰኘው ሁሉ አልሸልግም። ነገር ግን እናቴ! ቃሌን እንዳያስተውለው እፈራለሁ። ይዳስሰኝም ዘንድ ይወድ ይሆናል። እኔ ጠጕር እንደሌለኝ፥ ወንድሜ ዔሳውም ጠጕራም እንደ ሆነ አንቺ ታውቂያለሽ፤ በፊቱ የምንቀውና ያላዘዘኝን የምሠራ ይመስለዋል፤ ይቈጣኛል፤ በረከትን ያይደለ ርግማንን በእኔ ላይ አመጣለሁ።” 22እናቱ ርብቃም፥ “ልጄ ሆይ፥ ነገሬን ስማ እንጂ መርገምህ በእኔ ይሁን” አለችው፤ ያዕቆብም የእናቱን የርብቃን ቃል ሰማ፤ ሄዶም ያማሩና የሰቡ ሁለት የፍየል ጠቦቶችን አመጣ፤ ወደ እናቱም አቀረባቸው፤ እናቱም ይስሐቅ እንደሚወደው አድርጋ አዘጋጀቻቸው። 23ርብቃም የሚወደድ ከእርስዋ ዘንድ በቤቷ ያለውን የታላቁን ልጅዋን የዔሳውን ልብስ አምጥታ ለታናሹ ልጅዋ ለያዕቆብ አለበሰችው፤ የፍየሉን ጠቦት፤ ቍርበቶችንም በእጁ ላይ አኖረች፤ በሰውነቱና በአንገቱ ላይ አለበሰችው። ያዘጋጀቻቸውን ዳቦውንና ወጡንም ለልጅዋ ለያዕቆብ ሰጠችው። 24ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ገብቶ፥ “እኔ ልጅህ እንዳልኸኝ አደረግሁልህ፥ ተነሥተህ ተቀመጥ፤ አባቴ ሆይ፥ ሰውነትህ ትመርቀኝ ዘንድ አጥምጄ ከአመጣሁልህ ብላ” አለው። 25ይስሐቅም ልጁን፥ “ልጄ ሆይ! እንዲህ ፈጥነህ ያመጣህበት ምክንያት ምንድን ነው?” አለው። ያዕቆብም፥ “አምላክህ በፊቴ ያስገኘልኝን አመጣሁ” አለው። 26ይስሐቅም፥ “አንተ ልጄ ዔሳው እንደ ሆንህ፥ እንዳይደለህም ቅረበኝ፤ ልዳስህ” አለው። 27ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ቀረበ፤ ዳሰሰውም። “ቃልህስ የያዕቆብን ቃል ይመስላል፤ እጆችህ ግን የዔሳውን እጆች ይመስላሉ” አለው፤ 28ከእግዚአብሔር ታዝዞ ልቡናው ወደ ያዕቆብ የሚመለስበት ጊዜ ነውና አላወቀውም። 29ይመርቀውም ዘንድ እጆቹ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ናቸውና ይስሐቅ አላወቀም። 30“አንተ ልጄ ዔሳው ነህን?” አለው፤ እሱም፥ “አዎ፥ እኔ ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው። “ሰውነቴ ትመርቅህ ዘንድ ልጄ አድነህ ካመጣኸው አቅርብልኝ ልብላ” አለው። 31መብሉንም አቀረበለትና በላ። ወይንንም አቀረበለትና ጠጣ። 32አባቱ ይስሐቅም፥ “ልጄ ሆይ! ቀርበህ ሳመኝ” አለው። 33ቀርቦም ሳመው። ደስ የሚያሰኝ የልብሱን መዓዛ አሸተተ። መረቀውም። እንዲህም አለ፥ “እነሆ፥ የልጄ የልብሱ መዓዛ እግዚአብሔር እንደ ባረከው እንደ መስክ መዓዛ ነው። እግዚአብሔር ይስጥህ፤ ከሰማይ ጠልና ከምድር ጠል ያብዛህ፤ ስንዴውንና ዘይቱን ያብዛልህ። 34አሕዛብ ይገዙልህ፤ ሕዝቡም ይስገዱልህ፤ ለወንድምህም ጌታ ሁነው፤ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ። እግዚአብሔር እኔን የባረከባቸው፥ አባቴ አብርሃምንም የባረከባቸው በረከቶች ሁሉ ለአንተ ይሁኑህ፤ እስከ ዘለዓለምም ድረስ ለልጆችህ ይሁኑ። የሚረግምህ የተረገመ ነው፥ የሚመርቅህም የተመረቀ ነው” አለው። 35ይስሐቅ ልጁን ያዕቆብን መርቆት ከጨረሰ በኋላ እንዲህ ሆነ። 36ከወጣም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ያዕቆብም ከአባቱ ከይስሐቅ ዘንድ ወጥቶ ተሸሸገ። ወንድሙ ዔሳው ግን ከአደኑ ደረሰ፤ እርሱም መብልን አዘጋጅቶ ለአባቱ አቀረበ፤ አባቱንም፥ “አባቴ ሆይ፥ ሰውነትህ ትመርቀኝ ዘንድ አደን አድኜ ከአመጣሁልህ ተነሥ ብላ” አለው። 37አባቱ ይስሐቅም፥ “አንተ ማን ነህ?” አለው። “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ እንዳዘዝኸኝ አደረግሁ” አለው። 38ይስሐቅም እጅግ ፈጽሞ ተደነቀ፥ “አደን አድኖ አምጥቶልኝ አንተ ሳትመጣ ከሁሉ በልች የመረቅሁት ይህ ማን ነው? የተመረቀ ይሁን፤ ዘሩም እስከ ዘለዓለም ድረስ የተመረቀ ይሁን” አለው። 39ዔሳውም የአባቱን የይስሐቅን ነገር በሰማ ጊዜ እንዲህ ሆነ። በታላቅ ቃል እጅግ ምርር ብሎ ጮኸ፤ አባቱን፥ “አባቴ ሆይ፥ እኔንም መርቀኝ” አለው። 40“ወንድምህ በተንኰል መጥቶ በረከትህን ወሰደብህ፤” አለው። 41“ያዕቆብ ተብሎ በተጠራበት ስሙ እንዳሰነካከለኝ ዛሬ ዐወቅሁ። እነሆ፥ ይህ ሁለተኛው ነው። ቀድሞ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ ዛሬም በረከቴን ወሰደብኝ፤ አባቴ፥ ምርቃትን አላስቀረህልኝምን?” አለ። 42ይስሐቅም ለዔሳው እንዲህ ብሎ መለሰለት፥ “እነሆ፥ ለአንተ ጌታ አድርጌ ሾምሁት፤ ወንድሞቹንም ሁሉ ተገዢ ይሆኑት ዘንድ ሰጠሁት። ወይኑንና ስንዴውን፥ ዘይቱንም በማብዛት አፀናሁት። ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ለአንተ ምን ላድርግልህ?” 43ዔሳውም አባቱ ይስሐቅን፥ “አባቴ፥ በረከትህ አንዲት ብቻ ናትን? አባቴ ሆይ፥ እኔንም ባርከኝ” አለው። ዔሳውም ቃሉን አሰምቶ አለቀሰ። 44ይስሐቅም መለሰለት እንዲህም አለው፥ “እነሆ፥ ኑሮህ ከምድር ጠል፥ በላይም ከሰማይ ጠል ይሁን፥ በሰይፍህም ኑር፤ ለወንድምህ ተገዛ። 45እምቢ ብትል ግን፥ ቀንበሩንም ከአንገትህ ብታርቅ ያንጊዜ ለሞት የሚያበቃ በደልን ሁሉ ትበድላለህ። ዘርህም ሁሉ ከሰማይ በታች ይጠፋል።” 46ዔሳውም አባቱ ስለ መረቀው ምርቃት ያዕቆብን ይጣላው ነበር። በልቡም እንዲህ አለ፥ “የአባቴ የልቅሶው ቀን አሁን ይደርሳል፤ ወንድሜ ያዕቆብን እገድለዋለሁ።” የታላቁ ልጅዋ የዔሳውም ነገር ለርብቃ በሕልም ተነገራት። 47ርብቃም ልካ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብን ጠራችው፤ እንዲህም አለችው፥ “እነሆ፥ ወንድምህ ዔሳው ይገድልህ ዘንድ ቂም ይዞአል፤ አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ስማ፤ ተነሥተህ ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ወደ ካራን ሽሽ፤ የወንድምህ ቍጣ እስኪመለስ ድረስ ጥቂት ቀን ከእርሱ ጋር ተቀመጥ። ከአንተ ቍጣውን ይተዋል፤ ያደረግኸውንም ይረሳዋል፤ እኔም ልኬ በዚያ እቀበልሃለሁ።” 48ያዕቆብም፥ “አልፈራም፤ ይገድለኝ ዘንድ ቢወድድም እገድለዋለሁ” አለ። 49“ሁለታችሁን ልጆችን ሁሉ በአንዲት ቀን አጥቼ የወላድ መካን እንዳልሆን ሂድ” አለችው። 50ያዕቆብም እናቱን ርብቃን እንዲህ አላት፥ “አባቴ እንደ አረጀ እነሆ፥ አንቺ ታውቂያለሽ፤ ዐይኖቹም ፈዝዘዋልና አያይም። 51ከእናንተ ተለይቼ ትቼው ብሄድ በፊቱ ክፉ ይሆናል፤ አባቴም ተቈጥቶ ይረግመኛልና አልሄድም፤ ቢያሰናብተኝ ግን ያንጊዜ እሄዳለሁ፤” አላት። 52ርብቃም ያዕቆብን፥ “እኔ ገብች እነግረዋለሁ፤ ያሰናብትሃልም” አለችው። 53ርብቃም ወደ ይስሐቅ ገብታ ይስሐቅን እንዲህ አለችው፥ “ዔሳው ለእርሱ ሚስት አድርጎ ከአገባቸው ከሁለቱ ከኬጢ ልጆች የተነሣ ኑሮዬን ጠላሁ፤ ያዕቆብ እንደነዚህ ከአሉ ከሀገሪቱ ሴቶች ልጆች ለእርሱ ሚስት ከአገባ የከነዓን ሴቶች ልጆች ክፉዎች ናቸውና እንደ ምን እኖራለሁ?” 54ይስሐቅም ልጁን ያዕቆብን ጠርቶ መረቀው፤ መከረውም፥ “ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሁሉ ሚስት አታግባ፥ ተነሥተህ ወደ መስጴጦምያ ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድ፤ 55ከዚያም ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች ሚስት አግባ። የሰማይ አምላክ ይባርክህ። ፈጽሞም ያብዛህ። የአሕዛብ ጌታ ሁን። ተሰድደህ ትኖርባት የነበረች ሀገርን፥ እግዚአብሔርም ለአብርሃም የሰጣትን ምድር ሁላ ትወርሳት ዘንድ የአባቴን የአብርሃምን በረከት ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ ይስጥህ። ልጄ ሆይ፥ በሰላም ሂድ” አለው፥ 56ይስሐቅም ያዕቆብን አሰናበተው። ወደ ያዕቆብ እናት ወደ ርብቃ ወንድም ወደ ሶርያዊው ሰው ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ላባ ዘንድ ወደ መስጴጦምያ ሄደ። 57ያዕቆብ ወደ መስጴጦምያ ለመሄድ ከተነሣ በኋላ እንዲህ ሆነ። ልጅዋ ከሄደ በኋላ የርብቃ ልብዋ አዝኖ ታለቅስ ነበር። 58ይስሐቅም ርብቃን፥ “እኅቴ ሆይ ስለ ልጂሽ ስለ ያዕቆብ አታልቅሺ። በሰላም ሄዶ በሰላም ይመለሳልና፤ ልዑል አምላክም ከክፉ ሁሉ ይጠብቀዋልና፤ ከእርሱም ጋር ይኖራል፤ በዘመኑም ሁሉ አይለየውም፤ ወደ እኛ በሰላም እስኪመለስ ድረስ በሄደበት ሁሉ ጎዳናው እንዲቀናለት አውቃለሁና። 59በሰላም እናየዋለን፤ እኅቴ ሆይ፥ ስለ እርሱ አትፍሪ። እርሱ በመንገዱ የቀና ነውና፥ ፍጹምም ነውና፤ የታመነ ሰውም ነውና፤ አይወድቅምና አታልቅሺ” አላት። ይስሐቅም ስለ ልጅዋ ስለ ያዕቆብ ርብቃን ያረጋጋት ነበር። እርሱንም መረቀው።