1አብርሃም ከሞተ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ከኬብሮንም ተነሥቶ ሄዶ በዚህ ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ በአንደኛው ዓመት በዐዘቅተ ራእይ አጠገብ ሰባት ዓመት ኖረ። 2በአራተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት በአብርሃም ዘመን ከሆነው ከቀደመው ድርቅ ሌላ በሀገሩ ሁሉ ድርቅ ሆነ። ያዕቆብ የምስር ንፍሮ ቀቀለ፥ ዔሳውም ከምድረ በዳ ርቦት መጣ። 3ወንድሙ ያዕቆብን፥ “ከዚህ ከዳቦውና ከምስሩ ወጥ ስጠኝ” አለው። 4“ብኵርናህን ስጠኝ፤ እኔም ዳቦውን፥ ከዚህም ምስር ወጥ እሰጥሃለሁ” አለው። 5ዔሳውም በልቡ፥ “እኔ በራብ እሞታለሁ፤ ይህ ብኵርና ምን ያደርግልኛል?” አለ፥ ለያዕቆብም፥ “ብኵርናውን ሰጠሁህ” አለው። 6ያዕቆብም፥ “አሁን ማልልኝ” አለው። እርሱም ማለለት። ያዕቆብም ለወንድሙ ለዔሳው ዳቦውንና የምስሩን ወጥ ሰጠው፤ እስኪጠግብ ድረስ በላ፤ ዔሳውም ብኵርናውን አቃለለ። 7ስለዚህም ለበኵርናው ያዕቆብ ዳቦውንና የምስር ወጡን ስለ ሰጠው የዔሳው ስም ኤዶም ተባለ። 8ያዕቆብ ከበረ፤ ዔሳው ግን ከቅድምናው ተዋረደ። 9በሀገርም ድርቅ ሆነ፥ በዚህ ሱባዔ በሁለተኛው ዓመት ይስሐቅ ወደ ግብፅ ይወርድ ዘንድ መጣ፤ ወደ ፍልስጥኤሙ ንጉሥ ወደ አቤሜሌክ ወደ ጌራሮ ሄደ። 10እግዚአብሔርም ተገለጠለት እንዲህም አለው፥ “ወደ ግብፅ አትውረድ፥ እኔ ባልሁህ ሀገር ኑር፥ ወደዚያች ሀገር ሂድ፤ እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ፥ ለአንተና ለዘርህ ይህችን ሀገር መላዋን እሰጥሃለሁና እባርክሃለሁ፤ ለአባትህ ለአብርሃም የማልሁለትንም መሓላ አጸናለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ኮከብ አበዛልሃለሁ፤ ይህችን ሀገር ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ። 11አባትህ የእኔን ነገር ስለ ሰማ ቃሌንና ትእዛዜን ሕጌንና ሥርዐቴን፥ ቃል ኪዳኔንም ስለ ጠበቀ የምድር አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ። 12አሁንም ቃሌንና ትእዛዜን ስማ፤ በዚችም ሀገር ኑር።” ሦስት የዓመት ሱባዔ በጌራሮ ኖረ። አቤሜሌክም ስለ እርሱና ስለ ገንዘቡ ሁሉ፥ “እርሱን፥ ገንዘቡንም የነካ ሁሉ ሞትን ይሙት” ብሎ አዘዘ። 13ይስሐቅም በፍልስጥኤም ከበረ፤ ገንዘብም በዛለት፤ ላሞችና በጎች፥ ግመሎችና አህዮችም በዙለት። ብዙ ጥሪትም ነበረው። በፍልስጥኤም ሀገርም ዘር ዘራ። 14መቶ ዳውላ እህልም አገባ። ይስሐቅም ፈጽሞ ከበረ። የፍልስጥኤም ሰዎችም ቀኑበት። አብርሃም በሕይወት ሳለ የአብርሃም አሽከሮች የቈፈሩትን ጕድጓድ፥ አብርሃም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች አፈር ሞልተው ደፍነውት ነበር። 15አቤሜሌክም ይስሐቅን፥ “ከእኛ ፈጽመህ ከብረሃልና ከእኛ ዘንድ ሂድ” አለው። 16ይስሐቅም በሰባተኛው ሱባዔ በአንደኛው ዓመት ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጌራሮ ቆላ ሄደ። 17የአባቱም የአብርሃም አሽከሮች የቈፈሩአቸውን፥ አባቱ አብርሃም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፍነዋቸው የነበሩትን የውኃ ምንጮች ተመልሰው ቈፈሩ። ስማቸውንም አባቱ አብርሃም ባወጣላቸው ስም ጠራቸው። የይስሐቅም አሽከሮች በፋንጋ ጕድጓዶችን ቈፈሩ፤ በዚያም የጠራ ውኃ አገኙ። 18የጌራሮ እረኞች ከይስሐቅ እረኞች ጋር፥ “ይህ ውኃ የእኛ ነው” እየተባባሉ ተጣሉ። ይስሐቅም፥ “ከእኛ ጋር ተጣልተዋልና፤” ሲል የዚያን ጕድጓድ ስም “ዕፁብ” አለው። ሌላም ጕድጓድ ቈፈሩ፤ በእርሱም ተጣሉ፤ ስሙንም “ጸብእ” አለው። 19ከዚያም ተነሥተው ሄደው ሌላ ጕድጓድ ቈፈሩ፥ በእርሱ ግን አልተጣሉም፤ ስሙንም “ስፉሕ” አለው። 20ይስሐቅም፥ “ዛሬ እግዚአብሔር አሰፋልን፤ በምድርም ከበርን” አለ። ከዚያም በአርባ አራተኛው ኢዮቤልዩ በመጀመሪያው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። 21በዚያችም ሌሊት በመጀመሪያው ወር መባቻ እግዚአብሔር ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፥ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ እኔ ነኝ፤ እኔ ከአንተ ጋር እኖራለሁና አትፍራ፤ አከብርሃለሁ፤ ስለ ወዳጄ ስለ አብርሃም ዘርህን እንደ ባሕር አሸዋ ፈጽሜ አበዛዋለሁ።” 22እርሱም አባቱ አብርሃም ቀድሞ መሠዊያ በሠራበት በዚያ ቦታ መሠዊያ ሠርቶ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ። ለአባቱ ለአብርሃም አምላክም መሥዋዕትን ሠዋ፤ ጕድጓድንም ቈፈረ፤ ጥሩ ውኃንም አገኘ። 23የይስሐቅም ብላቴኖች ሌላ ጕድጓድ ቈoፈሩ፤ ውኃ ግን አላገኙም። ሄደውም ውኃ እንዳላገኙ ለይስሐቅ ነገሩት። 24ይስሐቅም፥ “በዚች ቀን ለፍልስጥኤም ሰዎች ማልሁ፤ ይህም ነገር ለእኛ ሆነ” አለ። ለአቤሜሌክና ለሁለተኛው ለአኮዘት፥ ለጠባቂው ለፋኮልም በዚያ ምሎአልና የዚያን ቦታ ስም “ዐዘቅተ መሐላ” ብሎ ጠራው። 25ይስሐቅም ከእነርሱ ጋር ሰላምን ለማድረግ በዚያች ቀን በግፍ እንደ ማለላቸው ዐወቀ፤ ይስሐቅም በዚያች ቀን የፍልስጥኤምን ሰዎች ረገማቸው። እንዲህም አለ፥ “በመቅሠፍትና በቍጣ ቀን የፍልስጥኤም ሰው ርጉም ነው፤ እግዚአብሔር ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ለይቶ ለሽሙጥና ለመርገም፥ ለመቅሠፍትና ለቍጣ ይስጣቸው፤ ያጠፋቸውም ዘንድ በኀጢአተኞች አሕዛብና በኬጤኤም እጅ ይጣላቸው። 26ለልጆች በዘመናቸው በምድር ላይ የዕለት ጠላትና የቈየ ጠላት ይሆኑባቸዋልና ከጠላት ሰይፍና ከኬጤኤም ያመለጡትን ጻድቃን ወገኖች ከሰማይ በታች በፍርድ ያጥፉአቸው። 27የፍልስጥኤም ዘር ሁሉ ከምድር ተነቃቅሎ ለመጥፋትና ለመራቅ የተዘጋጀ ነውና ለእነርሱ የሚቀርላቸው የለም። በቍጣ ፍርድ ቀንም የሚድን የለም። 28ላልተገረዘ ሁሉ በምድር ላይ የሚቀርለት ምንም ስምና ዘር አይኖረውም፤ እስከ ሰማይም ቢወጣ ከዚያ ይወርዳልና፥ በምድርም ቢጸና፥ ከዚያ ይነቀላልና፤ በአሕዛብም መካከል ቢሰወር ከዚያ ይጠፋልና፤ 29ወደ ሲኦልም ቢወርድ በዚያ ቅጣቱ ይበዛልና፤ በዚያ ምንም ሰላም የለውምና። 30ሰውነቱን ለማጥፋት በሚፈልጉአት ሰዎች እጅ ተማርኮም ቢሄድ በጎዳና መካከል ይገድሉታልና፥ በምድር ሁሉ የሚቀርለት ስምና ዘር የለውም። ወደ ዘለዓለም መርገም ይሄዳልና። 31ከምድር ይጠፋ ዘንድ በፍርድ ቀን ለእርሱ ለማድረግ ስለ እርሱ በሰማይ ጽላት እንደዚህ ተጽፎአል፤ ተቀርጾአልም።”