1እግሩን ዘርግቶ የዘለዓለም እንቅልፍ አንቀላፋ፤ በሞትም ወደ አባቶቹ ተስበሰበ። በዚህም ሁሉ ያዕቆብ በአጠገቡ ተኝቶ ነበር፤ የአባቱ አባት አብርሃምም እንደ ሞተ አላወቀም ነበር። 2ያዕቆብም ከእንቅልፉ ነቃ። እነሆ፥ አብርሃም ቀዘቀዘ፤ እንደ በረድም ሆነ። እርሱም፥ “አባ፥ አባ፥” አለ። የመለሰለትም ቃል አልነበረም፤ አብርሃምም እንደ ሞተ ዐወቀ። 3ከአጠገቡም ተነሥቶ ፈጥኖ ሄደ። ለእናቱ ለርብቃም ነገራት። ርብቃም በሌሊት ወደ ይስሐቅ ሄዳ ነገረችው፤ በአንድነትም ሄዱ። ያዕቆብም ከእነርሱ ጋር ነበረ። በእጁም መብራት ይዞ ነበር። በሄዱም ጊዜ አብርሃምን ሬሳው ተጋድሞ አገኙት። ይስሐቅም በአባቱ ፊት ወድቆ አለቀሰ፤ ሳመውም። 4በአብርሃምም ቤት ጩኸት ተሰማ። ልጁ ይስማኤልም ተነሥቶ ወደ አባቱ ወደ አብርሃም ሄደ፥ ለአባቱ ለአብርሃምም አለቀሰለት። እርሱና የአብርሃም ቤተ ሰብ ሁሉ ትልቅ ልቅሶን አለቀሱ። ልጆቹ ይስሐቅና ይስማኤልም ደርብ ባላት ዋሻ በሚስቱ በሳራ አጠገብ ቀበሩት። ቤተ ሰቦቹም ሁሉ አርባ ቀን አለቀሱለት። 5ይስሐቅና ይስማኤል፥ ልጆቻቸውም ሁሉ የኬጡራም ልጆች በቦታቸው አለቀሱለት። የአብርሃም ልቅሶ ኀዘንም ተፈጸመ። 6እርሱም ሦስት ኢዮቤልዩና አራት ሱባዔ ኖረ፤ ይኸውም መቶ ሰባ አምስት ዓመት ነው፥ በሕይወት የኖረበትም ዘመን ተፈጸመ። አረጀ፤ ዘመኑንም ፈጸመ። የቀደሙ ሰዎች በሕይወት የሚኖሩበት ዘመናቸው ዐሥራ ዘጠኝ ኢዮቤልዮች ነበሩ። 7ከጥፋት ውኃ በኋላ ግን ከኢዮቤልዮች ለማጕደልና ፈጥኖ ለማርጀት፥ ከአብርሃም በቀር በሥራቸው ክፋት ከብዙ መከራ የተነሣ ዘመናቸውን በመሰልቸት ከዐሥራ ዘጠኝ ኢዮቤልዮች ያጐድሉ ጀመር። 8አብርሃም ግን ከእግዚአብሔር ጋር በሥራው ፍጹም ነበረና ዘመኑ ሁሉ በእውነት ደስ ያሰኘው ነበረ። 9እነሆም፥ ከመከራ ብዛት የተነሣ ፈጥኖ እስኪያረጅ ድረስ፥ አራቱን ኢዮቤልዮች በሕይወት አልጨረሰም። ዕድሜንም ጠገበ፥ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ የሚነሡ ልጆች ሁሉ ሁለት ኢዮቤልዩ ሳይጨርሱ ፈጥነው ያረጃሉ። 10ከእርጅናቸውም የተነሣ ዕውቀታቸው የምትለያቸው ትሆናለች፤ ፍጹም ዕውቀታቸውም ትለያቸዋለች። 11በዚያም ወራት ሰው አንድ ኢዮቤልዩና የኢዮቤልዩ እኩሌታ ቢኖር ስለ እርሱ፥ “ብዙ ዘመን ኖረ” ይባላል። 12ነገር ግን የዘመኑ አብዛኛው በሽታ፥ ድካምና መከራ ነው፤ ሰላምም አይኖረውም፤ በመቅሠፍት ላይ መቅሠፍት፥ በቁስል ላይ ቁስል፥ በመከራ ላይ መከራ፥ በክፉ ምስክርነት ላይ ክፉ ምስክርነት፥ በበሽታ ላይ በሽታ ይሆናል። 13እንደዚሁም ክፉ ፍርድ ሁሉ ይሆናል፥ ይህም ከዚህ ደዌ ጋር ነው፥ ጓታ፥ ውርጭ፥ በረድ፥ ዋግ፥ እንቅልፍ፥ ግዳጅ፥ የሆድ በሽታ፥ ድርቅ፥ ሞት፥ ሾተል፥ መማረክ፥ መቅሠፍት ሁሉ፥ መከራውም፥ ይህም ሁሉ በዝሙት ርኵሰትና በመተዳደፍ፥ በሚያስጸይፍ ሥራቸውም ምድርን በምታረክስ በዚህች ክፉ ትውልድ ላይ ይመጣል። 14ያን ጊዜም እንዲህ ይላሉ፥ “የቀደሙ አባቶቻችን ዘመናቸው ብዙ ነበረ፤ እስከ ሺህ ዓመት ድረስ ብዙ ነበር፤ መልካምም ነበር፤። 15እነሆ፥ የእኛ የሕይወታችን ዘመን ግን ሰው ብዙ ዘመን ኖረ ቢባል ሰባ ዓመት ነው፤ እጅግም ቢበዛ ሰማንያ ዓመት ነው። ሁሉም ክፉ ነው፤ በዚያችም ክፉ ትውልድ ዘመን ምንም ሰላም አይኖርም። 16በዚያችም ትውልድ ልጆች አባቶቻቸውን፥ ሽማግሌዎቻቸውንም የሚሳደቡ ይሆናሉ። ስለ ኀጢአትና ስለ ዐመፅ፥ ስለ አንደበታቸውም አነጋገር እነርሱ ስለሚሠሩአቸው ታላላቅ ክፋቶች፥ ትእዛዙንና ሥርዐቱን፥ ሕጉንም ሁሉ ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ፥ በእነርሱና በእርሱ መካከል እግዚአብሔር ያደረገውን ቃል ኪዳን ስለ መተዋቸው ይሳደባሉ። 17ሁሉም ክፉ ሥራን እስከ መሥራት ደርሰው ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አይሉም። አንደበትም ሁሉ በደልን ይናገራል። ሥራቸውም ሁሉ ርኩስ ነው፥ የሚያጸይፍም ነው። መንገዳቸውም ነውር ነው፤ የረከሰም ነው፤ ጥፋትም ነው። 18“እነሆ፥ ምድር ስለ ሥራቸው ሁሉ ትጠፋለች። የወይን ዘር የላቸውም፤ ዘይትም የላቸውም፤ ሥራቸው ሁሉ ክህደት ነውና፥ አራዊትና እንስሳት፥ ወፎችና የባሕር ዓሣዎች ሁሉ ከሰው ልጆች አስቀድመው ሁሉም በአንድነት ይጠፋሉ። 19እነዚህ ከእነዚህ ጋር፥ ወጣቶች ከሽማግሌዎች ጋር፥ ሽማግሌዎችም ከወጣቶች ጋር፥ ድሃ ከባለጸጋ ጋር፥ ታናሹ ከታላቁ ጋር፥ ጦም አዳሪው ከዳኛው ጋር፥ ስለ ሕግና ስለ ቃል ኪዳን ይጣላሉ። 20ትእዛዙንና ቃል ኪዳኑን፥ በዓሉንና የወር መባቻውን፥ ሱባዔውንና ኢዮቤልዩን፥ ፍርዱንም ሁሉ ዘንግተዋልና፤ ከሰንከልካላ መንገዳቸው ይመልሱአቸው ዘንድ ለሰልፍ ሰይፍ ይዘው ይነሣሉ። ሕግን የሚጠብቁ ግን ብዙ ደም በምድር ላይ እስኪፈስስ ድረስ አይመለሱም። እነዚህ በእነዚህ ላይ ይነሣሉ። በጽድቅ መንገድ ያልዳኑ ሰዎች ግን ከክፋታቸው አይመለሱም። 21እያንዳንዱ በቅሚያ ለመበልጸግ የባልንጀራውን ገንዘብ ሁሉ ይወስድ ዘንድ ይነሣሉና፤ በታላቅ ስምም ይጠራሉ። ነገር ግን በእውነት አይደለም፥ በጽድቅም አይደለም፤ በርኵሰታቸውና በጥፋታቸው በነውራቸውም ቅድስተ ቅዱሳኑን ያረክሳሉ። 22“በዚያችም ትውልድ ሥራ ከእግዚአብሔር ጽኑ መቅሠፍት ይሆናል። ለሰይፍና ለቅጣት፥ ለመማረክና ለመቀማት፥ ለጥፋትም ይሰጣቸዋል፤ በእነርሱ ላይ ምሕረትና ይቅርታ የሌላቸውን የአሕዛብ ወገኖች ያስነሣባቸዋል። 23ከሰው ልጆች ሁሉ ይከፉ ዘንድ፥ ክፉዎችና ኀይለኞች ናቸውና ለሽማግሌም ቢሆን፥ ለሕፃንም ቢሆን፥ ለማንም ለማን ፊት አያደሉም፤ በእስራኤልም ላይ ክርክርን፥ በያዕቆብም ላይ በደልን ያደርጋሉ፤ ብዙ ደምም በምድር ላይ ይፈስሳል፤ የሚሰበስብም የለም፤ የሚቀብርም የለም። 24“በዚያም ወራት ጮኸው ይጣራሉ፤ ከኀጢአተኞች ከአሕዛብ እጅ ይድኑ ዘንድ ይጸልያሉ። ነገር ግን የሚያድን የለም። የሕፃናቱም ራስ በሽበት ይነጣል። የሦስቱ ሱባዔ ሕፃንም መቶ ዘመን እንደ ሆነው ሽማግሌ ሆኖ ይታያል። ቁመታቸውም በመከራና በጭንቀት ይጐብጣል። 25በእነዚያም ወራቶች ልጆች ሕጉን ለመመርመር፥ ሥርዐቱንም ለመፈለግ፥ ወደ እውነት መንገድም ለመመለስ ይጀምራሉ። ቀኖችም ይበዙና ይረዝሙ ጀመር፤ የሰው ልጆችም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይበዙ ጀመር፤ ቀናቸውም ወደ ሺህ ዓመት እስኪቀርብ ድረስ ከብዙ ቀናትም እስከ ብዙ ዓመታት እስኪቀርብ ቀን ከቀን ይበዛ ጀመር። 26ሽማግሌ የለም፤ ዕድሜንም የሚጠግብ የለም፤ ሁሉም ሕፃናትና ልጆች ይሆናሉና። ሁሉም ዘመናቸውን ይፈጽማሉ፥ በሰላምና በደስታም ይኖራሉ። 27ባላጋራ አይኖርም፤ ዘመኖቻቸው ሁሉ የበረከትና የፈውስ ዘመኖች ይሆናሉና የሚያጠፋ ክፉ አይኖርም። 28“ያንጊዜም እግዚአብሔር ባሪያዎቹን ያድናል፤ ይነሣሉም፥ በዓለምም ብዙ ሰላምን ያያሉ፤ ጠላቶቻቸውንም አስወጥተው ይሰዳሉ። ጻድቃንም አይተው ያመሰግናሉ። እስከ ዘለዓለም ድረስ ፈጽሞ ደስ ይላቸዋል። በጠላቶቻቸውም የተደረገውን ፍርድ ሁሉና መርገማቸውን ሁሉ ያያሉ። አጥንቶቻቸውም በምድር ያርፋሉ፤ ነፍሶቻቸውም ደስታን ያበዛሉ። 29ፍርድን የሚያደርግ እግዚአብሔርም እንዳለ ያውቃሉ ለሚወዱትም ሁሉ በመቶዎችና በሺሆች ለሚቈጠር ዘመን ይቅርታን ያደርጋል። 30ሙሴ ሆይ፥ አንተም ይህን ነገር ጻፍ፤ እንዲህ ተብሎ የተጻፈ ነውና፤ ለዘለዓለም ትውልድም ሥርዐት ሊሆን በሰማይ ጽላት ይጽፋሉ።