1በአርባ አራተኛው ኢዮቤልዩ፥ በመጀመሪያው ሱባዔ አብርሃም በሞተበት በሁለተኛው ዓመት እንዲህ ሆነ፤ በመጀመሪያው የአዝመራ በዓል የዚችን ሱባዔ በዓል ያደርጉ ዘንድ ይስሐቅና ይስማኤል ከቤርሳቤህ ወደ አባታቸው ወደ አብርሃም መጡ። 2አብርሃምም ሁለቱ ልጆቹ መጥተዋልና ደስ አለው። በቤርሳቤህ ያለ የይስሐቅ ገንዘቡ ብዙ ነበረና፤ ይስሐቅም ገንዘቡን ጐብኝቶ ወደ አባቱ ይመለስ ነበር። 3በዚህም ወራት ይስማኤል አባቱን ያይ ዘንድ መጣ። ሁሉም በአንድነት መጡ። 4ይስሐቅም የሚቃጠል መሥዋዕትን ሠዋ፤ አባቱ በኬብሮን በሠራው መሠዊያም ላይ አቀረበ። የድኅነት መሥዋዕትንም ሠዋ፤ በወንድሙ በይስማኤል ፊትም የደስታ ፍሪዳን አረደ። 5ርብቃም ከአዲሱ ስንዴ ትኩስ ዳቦ ጋገረች፤ በልቶም ሳይሞት የሁሉን ፈጣሪ እንዲያመሰግን ከመጀመሪያው የምድር ፍሬ ለአባቱ ለአብርሃም ያገባ ዘንድ ለልጅዋ ለያዕቆብ ሰጠችው። 6ይስሐቅም አብርሃም ይበላና ይጠጣ ዘንድ ያማረውን የድኅነት መሥዋዕት በያዕቆብ እጅ ሰደደለት። በልቶና ጠጥቶም ምድርንና ሰማይን፥ የምድርን ስፋትም ሁሉ የፈጠረ ልዑል አምላክን አመሰገነው። ይበሉና ይጠጡ ዘንድ፥ ፈጣሪያቸውንም ያመሰግኑ ዘንድ ለሰው ልጆች ሰጣቸው። 7አብርሃምም እንዲህ አለ፥ “ይህችን ቀን አሳይተኸኛልና እነሆ፥ እኔ ለአንተ እገዛለሁ። እነሆም፥ እኔ የመቶ ሰባ አምስት ዓመት ሰው ነኝ፤ አርጅቻለሁም፤ ዘመኔም ተፈጽሞአል፤ ዘመኖችም ሁሉ ሰላም ሆኑልኝ፤ የጠላት ሰይፍም ድል አልነሣኝም። 8በሰጠኸኝም ሁሉና፥ በልጆች በሕይወት በኖርሁበት ዘመን ሁሉ እስከዚች ቀን ድረስ፥ አምላኬ ሆይ፥ በዚህ ዓለም ከአሕዛብ ሁሉ ተለይቶ ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም በምድር ላይ እስከሚነሣው ትውልድ ዘመን ሁሉ ድረስ የተመረጠ ሕዝብና ርስት ይሆንህ ዘንድ፥ ይቅርታህ ለባሪያህና ለልጆቹ ይሁን።” 9ያዕቆብንም ጠርቶ እንዲህ አለው፥ “ልጄ ያዕቆብ ሆይ፥ ሁሉን የፈጠረ አምላክ ይባርክህ፤ በፊቱም ጽድቅንና ፈቃዱን ለማድረግ ያበርታህ። እንደ ፈቃዱም በዘመኑ ሁሉ የርስቱ ሕዝብ ትሆኑት ዘንድ አንተንና ዘርህን ይምረጥ። 10አንተም ልጄ ያዕቆብ፥ ቀርበህ ሳመኝ፤” ቀርቦም ሳመው። 11እንዲህም አለ፥ “አንተም ልጄ ያዕቆብ፥ የተባረክህ ነህ። ልጆችህም ሁሉ ለልዑል እግዚአብሔር ለዘለዓለም የተባረኩ ናቸው። ጻድቅ ዘርንም ይስጥህ፤ ከልጆችህም በምድር ሁሉ መካከል ይቀድስ። አሕዛብ ይገዙልህ፤ አሕዛብም ሁሉ በዘርህ ፊት ይስገዱ፤ በሰውም ፊት አርበኛ ሁን፤ በሴት ልጆችም ሁሉ መካከል ሠልጥነህ ኑር። 12ያንጊዜ ቅዱስ ሕዝብ ለመሆን መንገዶችህና የልጆችህ መንገዶች እውነተኛ ይሆናሉ። ልዑል አምላክ እኔን የባረከባቸውን፥ ኖኅንና አዳምንም የባረከባቸውን በረከቶች ሁሉ ይስጥህ። በልጅ ልጅ ዘመን ሁሉ እስከ ዘለዓለም ድረስ ዘርህን ለመቀደስ በአንተ ላይ ይረፉ። 13ባለማወቅ ከሠራኸው ኀጢአትህ ሁሉ ስርየትን ታገኝ ዘንድ ከኀጢአትና ከርኵሰት ሁሉ ያንጻህ፤ ያበርታህም፤ ሀገሩን ሁሉ ትወርስ ዘንድ ይባርክህ። ለዘለዓለም ለርስቱ ሕዝብ ትሆነው ዘንድ ቃል ኪዳኑን ከአንተ ጋር ያጽና። 14በምድር ዘመን ሁሉ ለአንተም ለዘርህም በእውነትና በጽድቅ አምላክ ይሁንህ። 15“አንተም ልጄ ያዕቆብ፥ ቃሌን አስብ፤ የአባትህን የአብርሃምንም ትእዛዝ ጠብቅ፤ ከአሕዛብም ተለይ፤ ከእነርሱም ጋር አትብላ፥ እንደ ሥራቸውም አትሥራ። ሥራቸው የረከሰ ነውና፥ አካሄዳቸውም ሁሉ የረከሰና የተናቀ ነውና፤ መሥዋዕታቸውም የሚያጸይፍ ነውና ባልንጀራ አትሁናቸው። 16ለሬሳዎች ፍሪዳ ያርዳሉ፤ ለአጋንንትም ይሰግዳሉ፤ በመቃብርም ይበላሉ፥ ሥራቸውም ሁሉ ከንቱና ብላሽ ነው። ለማሰብም ልብ የላቸውም። ዐይናቸውም የሚያይ አይደለም። ሥራቸው ምንድን ነው? 17እንጨቱን፦ ፈጣሪዬ አንተ ነህ፥ ድንጋዩንም፦ ጌታዬ አንተ ነህ፥ የምታድነኝም አንተ ነህ እያሉ እነርሱ እንዴት ይስታሉ? ልብም የላቸውም። 18“አንተ ልጄ ያዕቆብ፥ ልዑል አምላክ ይርዳህ፤ የሰማይ አምላክም ይባርክህ፤ ከርኵሰታቸውና ከስሕተታቸው ሁሉ ያርቅህ። 19ልጄ ያዕቆብ፥ ከከነዓን ሴቶች ልጆች ዘር ሚስት እንዳታገባ ተጠበቅ። ዘሩ ሁሉ ከምድር ለጥፋት ነውና፥ በካም በደል ከነዓን ስትዋልና። ልጁና የልጅ ልጁ ሁሉ ከምድር ይደመሰሳልና፤ በፍርድ ቀንም ከእነርሱ የሚድን የለምና። 20ጣዖት ለሚያመልኩና ለተጠሉ ሰዎች ሁሉ በሕያዋን ምድር ምንም ተስፋ የላቸውምና፥ ወደ ሲኦልም ይወርዳሉና፥ ወደ ፍርድ ቦታም ይሄዳሉና፥ በምድርም ላይ ምንም መታሰቢያ የላቸውምና የሰዶም ልጆች ከምድር እንደ ተወሰዱ እንዲሁ ጣዖት የሚያመልኩ ሁሉ ይወሰዳሉ። 21“ልጄ ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፤ የአብርሃም ልጅ ሆይ፥ አትደንግጥ፤ ልዑል አምላክ ከጥፋት ይጠብቅህ፤ ከስሕተትም ሥራ ሁሉ እርሱ ያድንህ። 22ይህንም ቤት በምድር ላይ ስሜን በእርሱ አኖር ዘንድ ለእኔ ሠራሁ፤ ለአንተና ለዘርህም ለዘለዓለም ተሰጠች። የአብርሃምም ቤት ትባላለች። 23ቤቴን ትሠራለህና፥ ስሜንም በአምላክ ፊት እስከ ዘለዓለም ታጸናለህ፥ ዘርህም፥ ስምህም በምድር ትውልድ ሁሉ ጸንቶ ይኖራል፤” ይህንም አዝዞና መርቆ ጨረሰ። 24ሁለቱም ሁሉ በአንድ አልጋ በአንድነት ተኙ። ያዕቆብም በአባቱ አባት በአብርሃም አጠገብ ተኛ። ሰባት ጊዜም ሳመው፤ ሩኅሩኅ ልቡናውም በእርሱ ደስ አለው። በፍጹም ልቡናውም ባረከው። 25እንዲህም አለ፥ “ለዘለዓለም ልወርሳትና ለዘለዓለም ይባረክ ዘንድ ቅዱስ ልጅን ልወልድ ያችን ሀገር ትሰጠኝ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ያወጣኸኝ የሁሉ አምላክና የሁሉ ፈጣሪ ልዑል አምላክ ሆይ፥ 26በፍጹም ልቤና በይቅርታዬ በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ያዕቆብን ባርከው። ይቅርታህና ብዙ ቸርነትህ በዘመኑ ሁሉ በእርሱና በዘሩ ይሁን። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ አትለየው፤ ቸልም አትበለው። 27ይጠብቁት ዘንድ፥ ትባርከውም ዘንድ፥ ለርስትህ የሚሆን ሕዝብን ትቀድሰው ዘንድ፥ በእርሱና በዘሩ ላይ ዐይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ። ከዛሬም ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በበረከትህ ሁሉ ባርከው። 28ቃል ኪዳንህንና ይቅርታህን ከእርሱ ጋር፥ ከዘሩም ጋር፥ በምድር ትውልድ ሁሉ በፍጹም ፈቃድህ አድስ።” ሁለቱንም ሁሉ የያዕቆብን ጣቶች በዐይኖቹ ላይ አኖረ፤ የአማልክት አምላክን አመሰገነው፥ ፊቱንም ሸፈነ።