1በዚህ ኢዮቤልዩ በሰባተኛው ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ጠርቶ እንዲህ ብሎ አዘዘው፥ “እኔ አረጀሁ፥ ዘመኔን ጠግቤአለሁና የምሞትበትን ቀን አላውቅም። 2እነሆ፥ እኔ የመቶ ሰባ አምስት ዓመት ሰው ነኝ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን ሳስበው፥ በፍጹም ልቤም የአምላኬን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ መሄድን አቀና ዘንድ ስፈልግ ኖርሁ። ሕያውና ቅዱስ፥ ከሁሉም ይልቅ የታመነና ጻድቅ አምላክ ነውና የፈጣሪዬን ፈቃድ ለማድረግ እጠብቅ ዘንድ ነፍሴ ጣዖትን ጠላች። 3የጽድቅ አምላክ ነውና፥ ሕጉን በሚያፈርሱ ሰዎች ሁሉ፥ ቃል ኪዳኑንም በሚንቁ ሰዎች ፍርድን የሚያደርግ ነውና በእርሱ ዘንድ ዐመፅ፥ ለሰው ፊትም ማድላትና መማለጃ መቀበል የለም። 4“ልጄ ሆይ፥ አንተም ትእዛዙንና ሥርዐቱን፥ ፍርዱንም ጠብቅ። ርኵሳንን፥ የተቀረጹ ጣዖታቱንና፥ ተመትተው የተሠሩትንም ጣዖታት ተከትለህ አትሂድ። የአውሬውንና የእንስሳውን፥ በሰማይ የሚበሩ የወፎችንም ሁሉ ደም አትብላ። 5ብታርድም ተቀባይነት ያለው የሚቃጠል የሰላም መሥዋዕትን ሠዋ፤ ደማቸውንም በመሠዊያው ላይ አፍስስ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ስብ ከስንዴው ጋር ወደ መሠዊያው አቅርብ፤ በዘይት የተለወሰውንም መሥዋዕት ከመጠጡ ቍርባን ጋር ሁሉንም በአንድነት በእግዚአብሔር ፊት ለበጎ መዓዛ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ፥ እንደ ድኅነቱ መሥዋዕት ስብ በሆዱ ውስጥ እንዳለው ስብ በመሠዊያው ላይ ባለው እሳት ታኖረዋለህ። 6በሆድ ዕቃውም ውስጥ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ሁለቱን ኵላሊቱንም፥ በእነርሱ ላይ ያለውንም ስብ ሁሉ፥ በወርቹ ላይ ያለውንም ስብ፥ ግልገል ጉበቱንም፥ ከኵላሊቱ ጋር እንደ ተጠቀለለ፥ 7ይህንም ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለው በጎ መዓዛ አድርገህ ለእግዚአብሔር ለበጎ መዓዛ ለሚቀርበው ከሚቃጠለው የእህል መሥዋዕትና ከመጠጡ ቍርባን ጋር ታቀርባለህ። ሥጋውንም በዚያች ሌሊትና በማግሥቱ ብላ። 8በማግሥቱም እስኪበላ ድረስ ፀሓይ አይግባ፤ እግዚአብሔር አይቀበለውምና ለሦስተኛው ቀን አይትረፍ፤ የተመረጠም አይደለምና፥ ከዚያ በኋላ አይበላም። የሚበሉትም ሁሉ ኀጢአታቸውን ይሸከማሉ። 9በቀደሙ አባቶች መጽሐፍ ውስጥ በሄኖክና በኖኅ ቃል ውስጥ እንዲህ የሚል ጽሕፈት አግኝቻለሁና፥ በመሥዋዕትህም ሁሉ ጨው ትጨምራለህ፤ በእግዚአብሔር ፊት በሚሠዋው መሥዋዕት ሁሉ የጨው ቃል ኪዳን አይቋረጥም። 10“ወደ መሠዊያው እነዚህን እንጨቶች ብቻ ታገባ ዘንድ መሥዋዕት ስለሚሠዋባቸው እንጨቶች ተጠንቀቅ፥ እነዚህም፦ ሰኖባር፥ ቀረጥ፥ ሰገድ፥ ሽነት፥ ወይራ፥ ዋንዛ፥ ዶቅማ፥ ጠዶ፥ ዘይት፥ ባርሰነት፥ ጥድ፥ አርቦቅ፥ ቀጋ፥ ሾላ ናቸው። 11ከእነዚህ እንጨቶች አይነታቸውን መርምረህ በመሠዊያው ላይ ከሚቃጠለው መሥዋዕት በታች አኑር፥ የነቀዘውንና የበሰበሰውን እንጨት ሁሉ አታኑር። ነገር ግን ፈጽሞ ምንም ነውር የሌለባቸውን የጸኑትንና ያማሩትን እንጨቶች፤ የአዲሱንም ተክል እንጨት አኑር። 12መዓዛው ተለይቶታልና፥ እንደ ቀደመው በእርሱ መዓዛ የለምና አሮጌውን እንጨት አታኑር። ነገር ግን መዓዛው ልዩ ነውና፥ መዓዛውም ወደ ሰማይ ያርጋልና ከእነዚህ እንጨቶች በቀር ሌላ አይኑር። 13ይህን ትእዛዝ ጠብቅ፤ ልጄ ሆይ፥ ሥራህን ሁሉ ታቀና ዘንድ ያዘዝሁህን አድርግ። በየጊዜውም ሰውነትህን ንጹሕ አድርግ፤ መሥዋዕት ለመሠዋት ወደ መሠዊያው ሳትወጣ በውኃ ታጠብ፤ ወደ መሥዋዕቱም ሳትቀርብ እጅህንና እግርህን ታጠብ። 14መሥዋዕቱንም ማቅረብ በጨረስህ ጊዜ ተመልሰህ እጅህንና እግርህን ታጠብ። በሰውነታችሁና በልብሳችሁም ላይ ደም ሁሉ አይታይ። 15ልጄ ሆይ፥ ከደም ፈጽመህ ተጠበቅ፤ አፈር አልብሰው፤ ደም ነፍስ ናትና እንግዲህ ወዲህ ደም አትብሉ። ምንም ደም አትብላ፤ ያለ ፍርድ በከንቱ እንዳይፈስስ በሰው ደም ሁሉ ላይ መማለጃ አትቀበል፤ የሚፈስስ ደም ምድርን ያጠፋታልና፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነም በቀር ደም ያለ ሰው ደም አትነጻምና። 16በሰው ደም መማለጃንና እጅ መንሻን አትቀበል። በልዑል አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ደም በደም ይመለሳል። ከክፉ ነገርም ሁሉ ትጠበቅ ዘንድ፥ ከሞትም ሁሉ ያድንህ ዘንድ ጥበቃው ለበጎ ነገር ይሆናል። 17“ልጄ ሆይ፥ የሰው ሁሉ ሥራ ኀጢአትና ክፋት እንደ ሆነ፥ ሥራቸውም ሁሉ የረከሰና የተናቀ፥ የተጠላም እንደ ሆነ፥ ከእነርሱም ጋር ጽድቅ እንደሌለ አያለሁ። 18በመንገዳቸው እንዳትሄድ፥ ፍለጋቸውንም እንዳትከተል ተጠበቅ። በልዑል አምላክ ፊትም እስከ ሞት የሚያደርስ ስሕተትን አትሳት። ከአንተም ፊቱን ይሰውራል፥ ወደ ኀጢአትህም ኀይል ይመልስሃል። ከምድር ይነቅልሃል። ዘርህንም ከሰማይ በታች ያጠፋል፤ ስምህና ዘርህም ከምድር ሁሉ ይጠፋሉ። 19ከሥራቸው ሁሉና ከርኵሰታቸው ሁሉ ራቅ፤ የልዑል አምላክን ሕግም ጠብቅ፤ ፈቃዱንም ፈጽም። ሥራህን ሁሉ አቅና፤ በሥራህ ሁሉ ይባርክሃል። በምድር ሁሉ፥ በምድር ትውልድም ሁሉ የጽድቅ ተክልን ከአንተ ያስነሣል። ከሰማይ በታች በዘመኑ ሁሉ የእኔ ስም፥ የአንተም ስም ይታወቃል። 20“ልጄ ሆይ፥ በሰላም ሂድ፤ የእኔ አምላክ፥ የአንተም አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈጸም ያጽናህ። ልጅህን ሁሉ፥ የልጅ ልጅህንም ለዘለዓለም ትውልድ በምድር ሁሉ ለበረከት ትሆን ዘንድ በጽድቅ በረከት ሁሉ ይባርክ፤” ከእርሱም ዘንድ ደስ እያለው ወጣ።