1በዚህ ኢዮቤልዩ በሰባተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያው ወር እንዲህ ሆነ። በዚህ ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን እግዚአብሔር እንደሚወደው ስለ አብርሃም በሰማይ ቃሎች ተሰሙ፤ በሚናገረው ነገር ሁሉ የታመነ እንደ ሆነ በመከራውም ሁሉ የታመነ ነውና። 2መኰንን መስቴማ መጥቶ በአምላክ ፊት ቆሞ እንዲህ አለ፥ “እነሆ፥ አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ይወደዋል፥ ከሁሉም ይልቅ እርሱ ደስ ያሰኘዋል፤ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት አድርጎ ያቀርበው ዘንድ ንገረው። 3ይህን ነገር ቢያደርግ አንተ ታያለህ፤ በምትፈትነው ሁሉ እርሱ የታመነ እንደ ሆነ ታውቃለህ።” እግዚአብሔር ግን አብርሃም በነገረው መከራ ሁሉ የታመነ እንደ ሆነ ያውቃል፤ በሀገሩ በድርቅ ፈትኖታልና፤ በነገሥታቱም ገንዘብ ፈትኖታልና፤ ዳግመኛም በሚስቱ መቀማት ፈትኖታልና፤ በመገረዝም ፈትኖታልና፤ በሰደዳቸው ጊዜ በልጁ በይስማኤልና በባሪያው በአጋር ፈትኖታልና፥ በፈተነው መከራ ሁሉ የታመነ ሆኖ ተገኝቶአልና፥ ሰውነቱም ቸል አላለችምና። 4የታመነ ነውና፥ እግዚአብሔርንም ይወዳልና፥ ሥራውን አላቈየም። 5እግዚአብሔርም አብርሃምን፥ “አብርሃም፥ አብርሃም፥ አብርሃም” ብሎ ጠራው፥ አብርሃምም፥ “አቤት፥ አለሁ” አለ። እርሱም፥ “የምትወደውን ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ከፍ ወዳለች ተራራ ሂድ፤ እኔ ከምነግርህ ከተራሮች ወደ አንዲቱ ተራራ አውጣው” አለው። 6ከዚያም በነግህ ገሠገሠ፤ አህያውንም ጭኖ፥ ሁለቱንም ብላቴኖቹን፥ ልጁ ይስሐቅንም፥ ከእርሱ ጋር ይዞ፥ ለመሥዋዕት የሚሆን እንጨትንም ፈልጦ አሸክሞ ሦስት ቀን እግዚአብሔር ወዳዘዘው ቦታ ሄደ። 7ቦታውንም በሩቁ ሆኖ አየ፤ ውኃ ወዳለበት ጕድጓድም ደረሰ፤ ብላቴኖቹን፥ “አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቈዩኝ፤ ልጄና እኔ ሄደን፥ ሰግደን ወደ እናንተ እንመለሳለን” አላቸው። 8የመሥዋዕቱንም እንጨት ለልጁ ለይስሐቅ አሸክሞ፥ ወቅለምቱንና እሳቱን በእጁ ይዞ፥ እስከዚያ ቦታ ድረስ ሁለቱ ሁሉ በአንድነት ሄዱ። 9ይስሐቅም አባቱን፥ “አባቴ” አለው፥ እርሱም፥ “ልጄ፥ እነሆኝ፥ አለሁ” አለው። “እነሆ፥ እሳቱና ወቅለምቱ፥ እንጨቱም አለ፤ አባቴ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው በግ ወዴት ነው?” አለው። 10እርሱም፥ “ልጄ ሆይ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ያውቃል” አለው። ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ቦታ ቀረበ፤ መሠዊያም ሠራ፤ እንጨቱንም በመሠዊያው ላይ አደረገ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ላይ ባለ እንጨት ላይ አስተኛው። ልጁን ይስሐቅንም ይሠዋው ዘንድ ወቅለምቱን ለማንሣት እጁን ዘረጋ። 11እኔም በፊቱ ቆምሁ ፤ በመኰንን መስቴማም ፊት ቆምሁ። 12እግዚአብሔርም፥ “እርሱ እግዚአብሔርን የሚፈራ እንደ ሆነ ዐውቄአለሁና በይስሐቅ ላይ እጁን እንዳያወርድ፥ በእርሱም ምንም ክፉ ነገር እንዳያደርግ ንገረው” አለ። 13በሰማይም ሆኜ፥ “አብርሃም፥ አብርሃም” ብዬ ጠራሁት። እርሱም ደንግጦ፥ “እነሆ፥ እኔ አለሁ” አለኝ። “በሕፃኑ ላይ እጅህን አታውርድ፤ አንተ እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ ዛሬ ዐውቄአለሁና፤ ከእኔም ለበኵር ልጅህ አልራራህምና በእርሱ ላይ ምንም አታድርግ” አልሁት፤ መኰንን መስቴማም አፈረ። 14አብርሃምም ዐይኖቹን አቅንቶ አየ። እነሆ፥ ቀንዱን በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ አንድ በግ ሲወርድለት አየ። አብርሃምም ሄዶ ያን የበግ አውራ አምጥቶ ስለ ልጁ ፋንታ ለሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበው። 15አብርሃምም ያን ቦታ፥ “እግዚአብሔርን ያየሁበት” ይባል ዘንድ፥ “እግዚአብሔር የታየበት ቦታ” አለው፤ ተራራውም ደብረ ጽዮን ነው። 16እግዚአብሔርም አብርሃምን በሰማይ ሆኖ ዳግመኛ በስሙ ጠራው፤ በእግዚአብሔር ስም እንነግረው ዘንድ እንደ ታየነው፤ እግዚአብሔር “በራሴ ማልሁ አለ” አልነው። 17“ይህን ነገር አድርገሃልና፥ ለምትወድደው ለበኵር ልጅህ ከእኔ አልራራህለትምና ፈጽሜ እንድባርክህ፥ በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋና እንደ ሰማይ ኮከብ ዘርህን ፈጽሜ እንዳበዛው፥ 18ልጆችህም የጠላቶቻቸውን ሀገር እንዲወርሱ፥ ቃሌን ስለ ሰማህ ፋንታ በዚህ ዓለም ያሉ አሕዛብንም ሁሉ እንዲወርሱ እኔ ባዘዝሁህ ሁሉ አንተ ለእኔ የታመንህ እንደ ሆንህ ለሁሉ ነገርሁ፤ በሰላም ሂድ” አለው። 19አብርሃምም ወደ ብላቴኖቹ ሄደ። ከዚያም ተነሥተው በአንድነት ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ። አብርሃምም በመሐላ የውኃ ጕድጓድ አደረ። ያችንም በዓል በሄደባቸውና በሰላም በተመላለሰባቸው በሰባቱ ቀኖች መጠን በዘመኑ ሁሉ ሰባት ቀን የደስታ በዓል አደረጋት። የእግዚአብሔርም በዓል አላት። 20ሰባት ቀን በደስታ ይህችን በዓል ለማድረግ በልጆቹና በእስራኤል ላይ እንደ ታዘዘ በሰማይ ጽላት እንዲህ ተሠርቶአል፤ ተጽፎአልም። 21በአርባ ሁለተኛው ኢዮቤልዩ በመጀመሪያው ሱባዔ በአንደኛው ዓመት አብርሃም ተመልሶ በኬብሮን አንጻር ሁለት የዓመት ሱባዔ ኖረ። ይህችውም ቃርያታርባቅ ናት። 22በዚህ ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት የሳራ የሕይወት ዘመን ተፈጸመ፤ በኬብሮንም ሞተች። 23አብርሃምም አልቅሶ ይቀብራት ዘንድ ሄደ። ልቡናው ይታገሥ እንደ ሆነ እንዲሁም በአፉ በተናገረው ነገር ቸል አይል እንደ ሆነ ፈተንነው። በዚህም የታገሠ ሆኖ ተገኘ፤ በውስጡ ሬሳውን ሊቀብር የመቃብር ቦታ ይሰጡት ዘንድ ከኬጢ ልጆች ጋር በልቡና ትዕግሥት ተናግሮአልና አልተበሳጨም። 24እግዚአብሔርም በሚያዩት ሰዎች ሁሉ ፊት ባለምዋልነትን ሰጠው፤ ከኬጢ ልጆችም በየዋሃት ለመነ፤ በግራሩ አንጻር ያለች ባለ ደርብ ዋሻን ሰጡት። ይህችውም ኬብሮን ናት። በአርባ ብርም ሸጡለት። 25እነርሱም፥ “ያለ ዋጋ እንስጥህ” ብለው ለመኑት፥ እርሱ ግን የቦታውን ዋጋ ብሩን ፈጽሞ ሰጥቶአልና ከእነርሱ ያለ ዋጋ አልወሰደም፤ ዳግመኛም ሰገደላቸው። 26ከዚህ በኋላ ደርብ ባላት ዋሻ ሬሳዋን ቀበረ። ሳራም በሕይወት የኖረችበት መላ ዘመንዋ መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ሆነ፤ እነዚህም ሁለት ኢዮቤልዩ አራት ሱባዔና አንድ ዓመት ናቸው። ሳራም በሕይወት የኖረችባቸው የዘመኖችዋ ቀን ይህ ነው። 27አብርሃምም በተፈተነበት የታመነና ልቡናው የታገሠ ሆኖ የተገኘበት ይህ መከራ ዐሥር ነው፤ ለእርሱ ይሰጣት ዘንድ፥ ከእርሱም በኋላ ለልጁ ይሰጣት ዘንድ እግዚአብሔር ስለ ከነዓን የነገረውን ነገር እንቢ አላለም፤ በዚያም ሬሳውን ይቀብር ዘንድ ቦታን ለመነ። የታመነና የሚታገሥ ሆኖ ተገኝቶአልና በሰማይ ጽላት የእግዚአብሔር ወዳጅ ተብሎ ተጻፈ። 28በአራተኛው ዓመት ለልጁ ለይስሐቅ ሚስትን አጋባው፥ ስምዋም ርብቃ ይባላል፤ ይህችውም የአብርሃም ወንድም የናኮር ልጅ የባቱኤል ልጅና የላባ እኅት ናት። የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት የሚልካ ልጅ ባቱኤልም ርብቃንና ላባን ወለዳቸው። 29አብርሃምም ከሳራ አስቀድሞ አጋር በሞተች ጊዜ በቤቱ ከተወለዱ ልጆች ወገን የምትሆን ሦስተኛ ሚስትን አገባ፤ ስምዋም ኬጡራ ይባላል፤ እርስዋም ዘንበሬንና ዮከሳንን፥ ማዳይንና ምድያንን፥ ኢያዝቦቅንና ስሂያን እነዚህን ስድስቱን ወለደችለት። 30በሁለተኛው ሱባዔ ዘመን በስድስተኛው ሱባዔ በሁለተኛው ዓመት ርብቃ ለይስሐቅ ሁለት ልጆች፥ ያዕቆብንና ዔሳውን ወለደችለት። 31ያዕቆብም ፍጹም ቅን ነበረ፥ ዔሳው ግን ጨካኝ አርበኛና ጠጕራም ነበረ፤ ያዕቆብም በቤት ይውል ነበር። እነዚህም ጐልማሶች አደጉ። 32ያዕቆብ መጻፍን ተማረ፤ ዔሳው ግን አርበኛና አዳኝ ነበረና አልተማረም። ሰልፍንና ክፉ ሥራንም ሁሉ ተማረ፤ አብርሃምም ያዕቆብን ይወድ ነበር፤ ይስሐቅ ግን ዔሳውን ይወድ ነበር። 33አብርሃም የዔሳውን ሥራ አየ፤ ነገር ግን በያዕቆብ ስምና ልጅ እንዲጠራለት ዐወቀ። 34ርብቃንም ጠርቶ እርስዋ ከዔሳው ይልቅ ያዕቆብን ፈጽማ እንድትወደው አይቶአልና የያዕቆብን ነገር አዘዛት። 35“ልጄ ሆይ፥ ያዕቆብን ልጄን ጠብቂ፤ እርሱ ስለ እኔ ፋንታ በሰዎች ልጆች መካከል ለበረከት ይሆናልና፤ ለሴምም ዘር መመኪያ ይሆናልና፤ በምድር ገጽ ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ለሕዝቡ ጠበቃ ሊሆንለት እግዚአብሔር እርሱን እንዲመርጥ አውቃለሁና። 36እነሆ፥ ልጄ ይስሐቅ ከያዕቆብ ይልቅ ዔሳውን ይወድዳል፤ አንቺ ደግ ሰው ያዕቆብን ስትወጂው እኔ አይቻለሁ፤ ዳግመኛም ለእርሱ ደግ ነገር ማድረግን ጨምሪለት። 37ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም እስከሚነሣ ትውልድ ሁሉ ድረስ በምድር ላይ እርሱ ለበረከት ይሆነኛልና ዓይኖችሽ ወደ ተወዳጁ ይሁኑ። ከልጆች ሁሉ ይልቅ እርሱን ፈጽሜ ወድጃለሁና፥ ለዘለዓለም ይከብራልና ዘሩም ምድርን ሁሉ የሚሞላ ይሆናልና እጆችሽ ይጽኑ። ልብሽም በልጅሽ በያዕቆብ ደስ ይበለው፤ ሰው የባሕር አሸዋ መቍጠር ይችል እንደ ሆነ እንደዚሁም የእርሱ ዘር ይቈጠራል። 38እግዚአብሔር እኔንና ዘሬን የባረካቸው በረከቶች ሁሉ በዘመኑ ሁሉ ለያዕቆብና ለዘሩ ይሁኑ፤ በዘሩም ስሜ ይከብራል፤ የአባቶች የሴምና የኖኅ፥ የሄኖክና የመላልኤል፥ የሄኖስና የሴት የአዳምም ስም ይባረካል፤ እነርሱም ሰማይን ለመመሥረት፥ ምድርንም ለማጽናት፥ በጠፈር ላይ ያሉ ብርሃናትንም ለማደስ ይሆናሉ” አላት። 39ያዕቆብንም ጠርቶ በእናቱ በርብቃ ፊት ሳመው፤ መረቀውም፤ እንዲህም አለው፥ “ልቡናዬ የወደደችህ ልጄ ተወዳጁ ያዕቆብ ሆይ፥ ከጠፈር በላይ ያለ አምላክ ይባርክህ። 40አዳምንና ሄኖክን፥ ኖኅንና ሴምን የባረከባቸውን በረከቶችን ሁሉ ይስጥህ። የነገረኝን ሁሉና እሰጥሃለሁ ያለኝንም ሁሉ፥ በምድር ላይ እንደ ሰማይ ዘመን በአንተና በዘርህ ላይ እስከ ዘለዓለም ድረስ ያጽናልህ። 41ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ አምላክህ እግዚአብሔርን ከመከተል ያርቁህ ዘንድ የሰይጣን መናፍስት በአንተና በዘርህ ላይ አይሠልጥኑብህ። 42እግዚአብሔር አምላክ አባት ይሁንህ፥ አንተም ልጅ ሁነው። ለሕዝቡም በዘመኑ ሁሉ አለቃ ሁን፥ ልጄ በሰላም ሂድ።” 43ሁለቱም በአንድነት ከአብርሃም ዘንድ ወጡ፤ ርብቃም ያዕቆብን በፍጹም ልቡናዋ፥ በፍጹም ነፍስዋም ከዔሳው ይልቅ እጅግ ወደደችው፤ ይስሐቅም ከያዕቆብ ይልቅ ዔሳውን ይወድደው ነበር። 44በአርባ ሁለተኛው ኢዮቤልዩ፥ በሰባተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት አብርሃም ይስማኤልንና ዐሥራ ሁለቱን ልጆቹን፥ ይስሐቅንና ሁለቱን ልጆቹን፥ ስድስቱን የኬጡራ ልጆችንና ልጆቻቸውንም ጠራ። 45የእግዚአብሔርን ሕግ ይጠብቁ ዘንድ፥ ጽድቅንም ይሠሩ ዘንድ፥ በሰልፉም ሁሉ እንደ እርሱ ሊሆኑ እያንዳንዱ ባልንጀራውን ይወድ ዘንድ፥ እያንዳንዳቸውም በእያንዳንዳቸው ላይ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ አዘዛቸው። 46በምድርም ላይ ፍርድንና ጽድቅን ለማድረግ ከእነርሱ ጋር በገባው ቃል ኪዳን ልጆቻቸውን ይገርዙ ዘንድ፥ ከዝሙትና ከርኵሰት ሁሉ እንጠበቅ ዘንድ፥ ከመካከላችንም ርኵሰትንና ዝሙትን እናርቅ ዘንድ፥ እግዚአብሔር ካዘዘን ሥርዐት ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም እንዳይተላለፉ አዘዛቸው። 47ሴት ሁላ፥ ወይም ድንግልና ያላት ልጅ ብትሰስንባችሁ በእሳት አቃጥሉአት፤ ዐይናቸው ባየውና ልባቸው ባሰበውም አይሰስኑ። የከነዓን ዘሮች ከምድር ይጠፋሉና ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስትን አያግቡ። 48የረዓይትን ፍርድና የሰዶምን ፍርድ፥ ስለ ክፋታቸው ስለ ዝሙትና ርኵሰት እንደ ተፈረደባቸው፥ በዝሙትም እርስ በርሳቸው በሠሩት ጥፋት እንደ ሞቱ ነገራቸው። 49እናንተም ከዝሙትና ከርኵሰት ሁሉ፥ በኀጢአትም ከመተዳደፍ ሁሉ ተጠበቁ። ስማችንን ለመርገም እንዳትሰጡ፥ ኑሮአችሁንም ሁሉ ለትምክሕት እንዳታደርጉ፥ ልጆቻችሁንም ሁሉ በሰይፍ ለመጥፋት እንዳታደርጉ ተጠበቁ። እንደ ሰዶምም የተረገማችሁ ትሆናላችሁ። ልጆቻችሁም ሁሉ እንደ ገሞራ ልጆች ይሆናሉ። 50ልጆች፥ እኔ አዳኝባችኋለሁ፤ የሰማይን አምላክ ውደዱት፥ ትእዛዙንም ሁሉ ጠብቁ፤ ጣዖታቸውንና ኀጢአታቸውን ተከትላችሁ አትሂዱ። ተመትተው የተሠሩ ጣዖታትንና ቅርፆችን ለእናንተ አትሥሩ፤ ከንቱ ናቸውና፤ ምንም ምን እስትንፋስ የላቸውም፤ የሰው እጅ ሥራ ናቸውና። የሚታመኑባቸውም ሁሉ ከንቱ ናቸውና አታምልኩአቸው፤ አትስገዱላቸውም። 51እናንተ ግን ልዑል አምላክን አምልኩ፥ ሁልጊዜ ስገዱለት፥ ሁልጊዜም የእርሱን ፊት ተስፋ አድርጉ፤ በእናንተ ደስ ይለው ዘንድ፤ ምሕረቱንም ይሰጣችሁ ዘንድ፥ የበልጉንና የመከሩንም ዝናም ያወርድላችሁ ዘንድ፥ ሥራችሁንም ሁሉ፥ በምድርም የሠራችሁትን ሁሉ ይባርክላችሁ ዘንድ፥ ፍርድንና ጽድቅንም፥ ቅንነትንም በፊቱ አድርጉ። 52እህልህንና ውኃህን ይባርክልሃል፤ የአብራክህን ዘር፥ የምድርህንም ዘር፥ የላሞችህን መንጋና የበጎችህን መንጋ ይባርክልሃል። በምድርም ለበረከት ትሆናለህ። 53የምድርም አሕዛብ ሁሉ ይወዱአችኋል። እኔ እንደ ተናገርሁት የተባረኩ ይሆኑ ዘንድ ልጆቻቸሁን በስሜ ይባርካሉ። 54ለልጁ ለይስማኤልና ለኬጡራ ልጆችም ስጦታን ሰጥቶ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ አሰናበታቸው። ሁሉን ግን ለልጁ ለይስሐቅ ሰጠው። 55ይስማኤልና ልጆቹም፥ የኬጡራ ልጆችም የልጅ ልጆቻቸውም በአንድነት ሄዱ። ከፋራን ጀምሮ በምድረ በዳ አንጻር በምሥራቅ በኩል እስከ ባቢሎን መግቢያ ድረስ በሀገሩ ሁሉ ኖሩ፤ እነዚህም ከእነዚህ ጋር አንድ ሆኑ። ስማቸውም ዓረብና ይስማኤላውያን ተብሎ ተጠራ።