1በስድስተኛው ወር እኩሌታም እግዚአብሔር ሳራን ጐበኛት፤ እንዳለውም አደረገላት። ፀንሳም ወንድ ልጅን ወለደች። በሦስተኛውም ወር፥ በወሩ እኩሌታ እግዚአብሔር ለአብርሃም በነገረው ቀን በመጀመሪያው መኸር በዓል ይስሐቅ ተወለደ። 2አብርሃምም ልጁን በስምንተኛዪቱ ቀን ገረዘው፤ እርሱም ለዘለዓለም ሥርዐት ሊሆን እንደ ተሠራ በገባው ቃል ኪዳን አስቀድሞ ተገረዘ። 3በአራተኛው ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት ወደ አብርሃም ወደ መሐላ ጕድጓድ መጣን። ወደ እርስዋም እንመለስ ዘንድ ለሳራ እንደ ነገርናት ተገለጥንለት፤ እርስዋም ወንድ ልጅን ፀነሰች። 4በሰባተኛው ወር ተመለስን፤ ሳራንም በፊታችን ፀንሳ አገኘናት፤ ሳራንም ባረክናት። ዳግመኛም ሰባት ልጅ እስኪወልድና ሳይሞት እስኪያይ ድረስ እንደማይሞት የታዘዘለትን ሁሉ ነገርናት። 5በይስሐቅም ስምና ልጅ ይጠራለታል። የልጅ ልጆቹም ሁሉ ሕዝብ ይሆናሉ፤ ከአሕዛብም ጋር ይቈጠራሉ። 6ከይስሐቅም ልጆች አንዱ ለቅዱስ ዘርዕ ይሆናል፤ የልዑል ዕድል ፋንታም ይሆናልና ከአሕዛብ ጋር አይቈጠርም። 7ዘሩም ሁሉ ከሕዝቡ ሁሉ ተለይቶ ለእግዚአብሔር የክብር ሕዝብ ይሆን ዘንድ፥ ለመንግሥትና ለክህነት፥ ለቅዱስ ሕዝብም ይሆን ዘንድ እርሱ ወደሚያመልከው አምላክ 8መንገዳችንንም ሄድን፤ የነገርነውንም ሁሉ ለሳራ ነገርናት፤ ሁለቱም ሁሉ በአንድነት እጅግ ብዙ ደስ አላቸው። 9ላዳነውና በተሰደደበት ምድር ደስ ላሰኘው ለእግዚአብሔር በዚያ መሠዊያን ሠራ። 10በዚህም ወር በመሐላው ጕድጓድ መሠዊያ አቅራቢያ ሰባት ቀን የደስታ በዓል አደረገ። 11በዚህችም በዓል ለእርሱና ለአገልጋዮቹ ዳስ ሠራ፤ እርሱም አስቀድሞ በምድር የዳስ በዓልን አደረገ። 12በዚህም በሰባቱ ቀን ሁልቀን በየዕለቱ ሁለት ላሞች፥ ሁለት የበግ ሙክቶችና ሰባት በጎች፥ ስለ ኀጢአትም አንድ የፍየል ጠቦት፥ ስለ ልጆቹና ስለ እርሱ ያስተሰርይበት ዘንድ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ያቀርብ ነበር። 13ለድኅነት መሥዋዕትም ሰባት የበግ ሙክት፥ ሰባት የፍየል ጠቦት፥ ሰባት በጎች፥ ሰባት የፍየል ሙክት አቀረበ። መሥዋዕታቸውንና ወይናቸውንም በስባቸው ሁሉ ላይ አቀረበ። ለበጎ መዓዛም የተመረጠ ዕጣንን በመሠዊያው ላይ ጥዋት ጥዋት ያጥን ነበር። 14በሰርክም ሽቱን ያጥን ነበር። ነጭ ዕጣንን፥ ቀንዓትን፥ ልባንጃን፥ ናርዶስን፥ ከርቤና ሰንቡልን፥ ቀበርቾንም እነዚህን ሰባቱን ሁሉ ያጥን ነበር፤ የተወቀጠውንና የተመረጠውን፥ የተስተካከለውንና የተቀላቀለውን፥ ንጹሑንም ያቀርብ ነበር። 15እርሱም በፍጹም ልቡ፥ በፍጹም ነፍሱም ደስ እያለው በቤቱ ካሉት ሁሉ ጋር ሰባት ቀን ይህን በዓል አደረገ፤ ከእርሱም ጋር ባዕድ ወይም ያልተገረዘ ሰው ማንም አልነበረም። 16ለዘለዓለም ትውልድ የጽድቅ ተክል ከእርሱ እንደሚሆን ስላወቀና ስለ ተረዳ ለፈቃዱ ፈጥሮታልና የፈጠረውን አምላኩን አመሰገነው። ሁሉን እንዳደረገ እንደ እርሱም ይሆን ዘንድ ከእርሱ ቅዱስ ዘር ይሆናል። 17ይህችንም በዐል ባረካት፥ ደስም አለው፤ ስምዋንም የእግዚአብሔር በዓል ብሎ ጠራት። ልዑል አምላክም ደስ ብሎት የሚቀበላት የእግዚአብሔር በዓል አላት። 18ለዘለዓለም ባረክነው፤ ከእርሱ በኋላም ዘሩን ሁሉ እንደ ሰማይ ጽላት ምስክር ያቺን በዓል በጊዜዋ አድርጎአልና በምድር ትውልድ ሁሉ ባረክነው። 19ስለዚህም በዘመናትና በዓመታት ሁሉ በትውልዳቸው የዘለዓለም ሕግ ሊሆን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለው የዳስ በዓልን በደስታ ሰባት ቀን የሚያደርጉ ይሆኑ ዘንድ ለእስራኤል በሰማይ ጽላት ተጻፈ። 20በዓሉን ያደርጉት ዘንድ፥ በጥላም ይቀመጡ ዘንድ፥ በራሳቸውም አክሊል ይደፉ ዘንድ፥ ከወንዙም የአኻያውን ቅጠል ቅርንጫፍ ይይዙ ዘንድ፥ በእስራኤል የዘለዓለም ሥርዐት ሆኖ ተጽፎአልና ለዚህ ሥርዐት የተወሰነ ዘመን የለውም። 21አብርሃምም ለጋውን የሰሌን ጫፍ፥ ያማረ የእንጨቱንም ፍሬ ይዞ በየቀኑ በዘንባባው ሰባት ጊዜ መሠዊያውን ይዞር ነበር። 22ጥዋት ጥዋትም ሁሉን የፈጠረ አምላኩን በደስታ ያመሰግን ነበር። 23በዚህ ኢዮቤልዩ በአምስተኛው ሱባዔ በአንደኛው ዓመት ይስሐቅ ጡት ጣለ። 24አብርሃምም ልጁ ይስሐቅ ጡት በጣለባት ቀን በሦስተኛው ወር ታላቅ በዓል አደረገ። የግብፃዊቷ የአጋር ልጅ ይስማኤልም በአባቱ በአብርሃም ፊት በቦታው ተቀምጦ ነበር። 25አብርሃምም ደስ አለው። ሁለቱን ልጆቹን አይቶአልና፥ ልጅንም ሳይወልድ አልሞተምና። 26ሎጥ ከእርሱ በተለየባት ቀን የተናገረውንም ነገር አሰበ። ምድርን ይወርሳት ዘንድ በምድር እግዚአብሔር ዘርን ሰጥቶታልና ደስ አለው። የሁሉን ፈጣሪም በአፉ አመሰገነው። 27ሳራም ይስማኤልን ሲጫወትና ሲዘፍን አየችው፤ አብርሃምንም እጅግ ደስ ብሎት አየች። ይስማኤልንም ባየችው ጊዜ ቀንታ አብርሃምን፥ “የዚህች የባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ርስት አይወርስምና ይህችን ባሪያ ከልጅዋ ጋር አስወጥተህ ስደዳት” አለችው። 28ከእርሱ ለይቶ ይሰዳቸው ዘንድ ስለ ባሪያውና ስለ ልጁ በአብርሃም ፊት ኀዘን ሆነ። 29እግዚአብሔርም አብርሃምን፥ “ስለ ሕፃኑና ስለ ብላቴናዪቱ በፊትህ ኀዘን አይሁን፥ በይስሐቅ ስምና ዘር ይጠራልሃልና፥ ሳራ የነገረችህን ነገር ሁሉ ስማና አድርግ። ስለዚያች ባሪያ ልጅ ግን አትዘን፤ ከልጆችህ ወገን ነውና ታላቅ ወገን አደርገዋለሁ” አለው። 30አብርሃምም በጥዋት ገሥግሦ ሄዶ ውኃ ያለበትን ረዋትና ዳቦውን አምጥቶ ለአጋር አሸከማት፤ ልጁንም አሳዝሎ ሸኛት፤ በቤርሳቤህ ምድረ በዳም እየተቅበዘበዘች ሄደች። 31ውኃውም ከረዋቷ አለቀ፤ ልጁም ተጠማ፤ መሄድም ተሳነው፤ ሕፃኑም ወደቀ፤ እናቱም አነሣችው፤ ሄዳም በአንዲት የዘይት እንጨት ሥር አኖረችው፥ “የልጄንም ሞት አላይም” ብላለችና ጦር ወርውረው የሚያደርሱበት አንድ ምዕራፍ ያህል ርቃ ሄዳ ፊት ለፊት ተቀመጠች፤ በዚያም ተቀምጣ አለቀሰች። 32ከቅዱሳን መላእክት አንዱ መልአክ፥ “አንቺ አጋር፥ ለምን ታለቅሻለሽ? እግዚአብሔር ቃልሽን ሰምቶአልና፥ ሕፃኑንም አይቶታልና ተነሥተሽ ሕፃኑን አንሥተሽ በእጅሽ ያዢው” አላት። 33ዐይኖችዋንም ገልጣ የውኃ ጕድጓድ አየች፤ ሄዳም ረዋቷን ውኃ ሞላች፤ ልጅዋንም አጠጣች፤ ተነሥታም ወደ ፋራን ምድረ በዳ ሄደች። 34ሕፃኑም አድጎ አዳኝ ሆነ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። እናቱም ከግብፅ ሴቶች ሚስት አጋባችው፤ ወንድ ልጅንም ወለደችለት። “በለመንሁት ጊዜ እግዚአብሔር ለእኔ ቅርቤ ነው” ብላለችና ስሙን ናቢኦት አለችው።