1ከዚህ ነገር በኋላ በዚህ ሱባዔ በአራተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር መባቻ፥ “አብራም፥ አትፍራ፤ ጠበቃህ እኔ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ይበዛል፥” ሲል የእግዚአብሔር ቃል በሕልም ወደ አብራም መጣ። 2እርሱም እንዲህ አለ፥ “አቤቱ፥ ምን ትሰጠኛለህ? እኔ ልጅ ሳልወልድ እሄዳለሁ፤ የደማስቆ ሰው የሚሆን የአማቲየል 3እርሱም፥ “ከአብራክህ የሚወለድ ልጅ እርሱ ይወርስሃል እንጂ ይህ አይወርስህም” አለው። 4ወደ ውጭም አውጥቶ፥ “ወደ ሰማይ ተመልከት፤ መቍጠር ይቻልህ እንደ ሆነ ከዋክብትን ቍጠር” አለው። ሰማይን አየ፤ ከዋክብትንም ተመለከተ፤ እርሱም፥ “ዘርህ እንደዚህ ይሆናል” አለው። እግዚአብሔርንም አመነው፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት። 5“ለዘለዓለም ይዘሃት ልትኖር 6እርሱም፥ “አቤቱ አቤቱ፥ እንደምወርሳት በምን አውቃለሁ?” አለ። 7እርሱም፥ “የሦስት ዓመት ወይፈን፥ የሦስት ዓመት ፍየል፥ የሦስት ዓመት በግ፥ ዋኖስና ርግብንም አምጣልኝ” አለው። 8ይህንም ሁሉ በወር እኩሌታ አመጣ። እርሱ ግን የኬብሮን አቅራቢያ በምትሆን በመምሬ ባለ ግራር ሥር ተቀምጦ ነበር። 9በዚያም መሠዊያን ሠራ፥ ይህንም ሁሉ ሠዋ፤ በመሠዊያውም ላይ ደማቸውን አፈሰሰ፤ ከሁለት ከሁለትም አደረጋቸው፤ በየመልካቸውም በአንጻራቸው አኖራቸው፤ አዕዋፍን ግን ጨርሶ አልቈረጣቸውም። ወፎችም ወደ መሥዋዕቱ ይወርዱ ነበር። 10አብራም ግን ይከለክላቸው ነበር፤ ወፎችም ይበሉአቸው ዘንድ አልተወም ነበር። 11ፀሐይም በገባ ጊዜ እንዲህ ሆነ፥ በአብራም እንቅልፍ መጣበት ፤ እነሆም፥ የሚያስፈራ ጽኑ ጨለማ በላዩ ወደቀበት። 12ለአብራምም እንዲህ ተብሎ ተነገረ፥ “ዘርህ በአሕዛብ ሀገር ስደተኞች እንደሚሆኑ፥ አራት መቶ ዓመትም እንደሚገዙአቸውና መከራ እንደሚያጸኑባቸው ፈጽመህ ዕወቅ፤ የሚገዙአቸውንም ወገኖች እኔ እፈርድባቸዋለሁ። 13ከዚህ በኋላ ከብዙ ገንዘብ ጋር ከዚያ ይወጣሉ። አንተም ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ በበጎ እርግናም ትቀበራለህ። 14በአራተኛው ትውልድ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ እስከ ዛሬ ድረስ የአሞራውያን ኀጢአት አልተፈጸመምና።” 15ከእንቅልፉም ነቅቶ ተነሣ፤ ፀሐይም ገባ፤ እሳትም ይነድ ጀመር፤ እነሆ፥ ምድጃው እየጤሰ የእሳቱ ነበልባል በመሠዊያው መካከል አለፈ። 16በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ከአብራም ጋር እንዲህ ሲል ቃል ኪዳን አደረገ፥ “ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ፤ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ፥ ይህችን ሀገር ለልጆችህ እሰጣለሁ፤ የቄኔዎስንና የቄኔዜዎስን፥ የቀድሞኔዎስን፥ የፌርዜዎስንና የራፋይምን፥ የፌኮሬዎስን፥ የኤዌዎስንና የአሞሬዎስን፥ የከናኔዎስንና የጌርጌሴዎስን፥ የኢያቡሴዎስንም ሀገር እሰጥሀለሁ።” 17አብራምም ሄዶ መሠዊያውን አዘጋጀ፤ አዕዋፍንና መሥዋዕታቸውን፥ ወይናቸውንም አቀረበ፤ እሳትም በላው። 18በዚያችም ወር ከኖኅ ጋር ቃል ኪዳን እንደ አደረግን በዚችም ዕለት ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን አደረግን። 19አብራምም ይህችን በዓልና ሥርዐቷንም እስከ ዘለዓለም ድረስ ለራሱ አጸናት፤ አብራምም ደስ አለው፤ ይህንም ነገር ሁሉ ለሚስቱ ለሶራ ነገራት፤ ልጅ እንደሚወለድለትም አመነ። እርስዋ ግን ልጅ አትወልድም ነበር፤ ሶራም ባልዋን አብራምን መከረችው፦ 20አብራምም የሚስቱ የሶራን ቃል ሰማ፥ “እንዳልሽ አድርጊ” አላት። ሶራም ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን አምጥታ ሚስት ትሆነው ዘንድ ለባልዋ ለአብርሃም ሰጠቻት። 21ወደ እርስዋም ገባ፥ ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች። በዚህ ሱባዔ በአምስተኛው ዓመት ስሙን ይስማኤል ብሎ ጠራው። በዚያም ዓመት የአብራም ዕድሜ ሰማንያ ስድስት ዓመት ነበር። 22በዚህ ኢዮቤልዩ በአራተኛው ሱባዔ በአምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በወሩ እኩሌታ መጀመሪያ ስለ ደረሰው የስንዴ አዝመራ አብራም በዓልን አደረገ። 23በመሠዊያውም ላይ የእህሉን መጀመሪያ አዲስ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ወይፈኑንና የበጉን ሙክት፥ በጉንም በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ። መሥዋዕታቸውንና ወይናቸውንም ከነጭ ዕጣን ጋር አቀረበ። 24እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፥ “ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ። በፊቴ የምትወደድ ሁን፤ ፍጹምም ሁን፤ በእኔና በአንተ መካከልም ቃል ኪዳን እሰጣለሁ፤ እጅግም አከብርሃለሁ።” 25አብራምም በግንባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “እነሆ፥ ሥርዐቴ ከአንተ ጋር ነው፤ ለብዙ አሕዛብም አባት አደርግሃለሁ። 26እንግዲህ ወዲህ ስምህ አብራም አይባል፤ የብዙ ሕዝብ አባት አድርጌሃለሁና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ስምህ አብርሃም ይባል። አንተንም በአሕዛብ መካከል ፈጽሜ አከብርሃለሁ፤ ነገሥታቱም ከአንተ ይወለዳሉ። 27በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በልጆችህ መካከል በወገናቸው የዘለዓለም ሥርዐት ልትሆን፥ ቃል ኪዳኔን አጸናለሁ፤ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ ለዘለዓለም በምትገዛት፥ ተሰደህ በሄድህባት በከነዓን ቃል ኪዳኔን አጸናለሁ፤ አምላካቸውም እሆናቸዋለሁ።” 28እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፥ “አንተ ቃል ኪዳኔን ጠብቅ፤ ከአንተም በኋላ ልጆችህ ይጠብቁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ሁሉ ትገዝራላችሁ፤ የሰውነታችሁንም ሸንኮፍ ሁሉ ትገዝራላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከልም ለልጅ ልጅ ለዘለዓለም የኪዳኔ ምልክት ይሆናል። 29በስምንተኛውም ቀን ወንድ ልጅን ሁሉ በየወገናችሁ ትገዝራላችሁ። በቤት የተወለደው፥ ከአሕዛብም ልጆች ሁሉ በወርቅ የገዛችሁት፥ ከዘርህም ያይደለ ቢሆን ይገዘሩ፤ በቤትህ የተወለደም፥ በወርቅህም የገዛኸው ቢሆን ይገዘሩ። 30ለዘለዓለም ሥርዐቴ ሊሆን ቃል ኪዳኔ በሰውነታችሁ ጸንቶ ይኖራል። ግዙር ያልሆነ ወንድ ልጃችሁ ሁሉ፥ በስምንተኛዪቱም ቀን የሰውነቱን ሰንኮፍ ያልተገዘረ ሁሉ ቃል ኪዳኔን አፍርሶአልና ያ ሰው ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ።” 31እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፥ “ሚስትህ ሶራ ስምዋ ሳራ ነውና ከእንግዲህ ወዲያ ስምዋ ሶራ ተብሎ አይጠራ፤ እባርካታለሁ፤ ከእርስዋም ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ታላቅ ወገንም ይሆናል፤ የአሕዛብ ነገሥታትም ከእርሱ ይወለዳሉ።” 32አብርሃምም በግንባሩ ወደቀ። ደስ ብሎትም በልቡ እንዲህ አለ፥ “በመቶ ዘመኔ ልጅ እወልዳለሁን? ዘጠና ዓመት የሆናት ሳራስ ልጅ ትወልዳለችን?” 33አብርሃምም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፥ “ይስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር።” 34እግዚአብሔርም አለው፥ “ይሁን፥ ሳራም ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ቃል ኪዳኔንም የዘለዓለም ቃል ኪዳን ሊሆን ከእርሱ ጋር አጸናለሁ፤ ከእርሱም በኋላ ለልጆቹ አጸናለሁ። 35ስለ ይስማኤልም ሰማሁህ፤ እነሆ፥ እባርከዋለሁ፥ አገነዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ ዐሥራ ሁለት መሳፍንትንም ይወልዳል፤ በታላቅም ሕዝብ ላይ እሾመዋለሁ። 36ቃል ኪዳኔን ግን በዚህ ወራት በሁለተኛው ዓመት ሳራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አጸናለሁ።” ከእርሱም ጋር ይህን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃም ካለበት ወጣ። 37አብርሃምም እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፤ ልጁ ይስማኤልንና በቤት የተወለደውን ሁሉ፥ በወርቁ የገዛውንም፥ በቤቱም ያለ ወንድ ልጅን ሁሉ ወስዶ የሰውነታቸውን ሰንኮፍ ገረዘ። 38በዚህችም ቀን አብርሃም ተገረዘ፤ ቤተ ሰቦቹም፥ በወርቅ የገዛቸውም ሁሉ፥ ከአሕዛብም የተወለዱ ሁሉ ከእርሱ ጋር ተገረዙ። ይህም ሕግ ለልጅ ልጅ ሁሉ የዘለዓለም ነው። 39ይህ የዘለዓለም ሥርዐት ነውና፥ በሰማይ ጽላትም ተጽፎአልና ቀን ማሳጠር የለም፤ ከስምንቱ ቀንም አንዲት ቀን መተላለፍ የለም። 40እስከ ስምንት ቀንም ድረስ የሰውነቱን ሰንኮፍ ያልተገረዘ ሰው ሁሉ ከጥፋት ልጆች ወገን ነውና እግዚአብሔር ለአብርሃም ከገባው ቃል ኪዳን ልጆች ወገን አይደለም። 41ለእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ምልክት የለውም፤ የአምላካችን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ስላፈረሰ ከምድር ለመጥፋትና ለመደምሰስ፥ ከምድርም ለመነቀል የተገባ ነውና። መላእክተ ገጽ ሁሉና የምስጋና መላእክት ሁሉ ከተፈጠሩበት ቀን ጀምሮ ተፈጥሮአቸው እንዲህ ነውና። 42በመላእክተ ገጽና በምስጋና መላእክት አንጻር ከእርሱ ጋርና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ይሆኑ ዘንድ እስራኤልን ቀደሰው። 43አንተም የእስራኤልን ልጆች እዘዝ፤ የዚህን ቃል ኪዳኔንም ምልክት ይጠብቁ፤ ለልጆቻቸውም የዘለዓለም ሥርዐት ይሁን፤ ለዘለዓለም በእስራኤል ልጆች ሁሉ ላይ ይጠብቁት ዘንድ ለቃል ኪዳን ሥርዐት ሠርቶአልና ከምድር እንዳይጠፉ ይሁኑ። ይስማኤልንና ልጆቹን፥ ወንድሞቹንና ዔሳውንም እግዚአብሔር ወደ እርሱ አላቀረባቸውም፤ ምንም የአብርሃም ልጆች ቢሆኑና ቢወድዳቸውም እነርሱን አልመረጠም። 44ሕዝብ ይሆኑት ዘንድ እስራኤልን ለይቶ መረጠ። ብዙ አሕዛብና፥ ብዙ ሕዝብ ሁሉ የእርሱ ናቸውና፥ ሁሉም ለእርሱ ይገባልና ከሰው ልጆች ሁሉ ለይቶ ሰበሰበው። ነገር ግን ከእርሱ በኋላ ያስቱአቸው ዘንድ መናፍስትን በሁሉ ላይ አሠለጠነ። 45በእስራኤል ላይ ግን ገዢአቸው እርሱ ብቻ ነውና፥ መልአክም ቢሆን መንፈስም ቢሆን ማንንም አላሠለጠነም። እርሱም ይጠብቃቸዋል። ከመላእክትና ከመናፍስት እጅ፥ ከሥልጣናትም ሁሉ እጅ ይጠብቃቸው ዘንድ ይመራመራቸዋል። እነርሱ ልጆቹ ይሆኑት ዘንድ እርሱም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ አምላክ ይሆናቸው ዘንድ ይባርካቸዋል። 46አሁንም የእስራኤል ልጆች ይህችን ሥርዐት ሐሰት እንደሚያደርጉ እኔ እነግርሃለሁ። በሰውነታቸው ከመገረዛቸው የተነሣ ልጆቻቸውን ሳይገርዙ ይቀራሉና፤ የቤልሆርም ልጆች ሁሉ ልጆቻቸውን እንደ ተወለዱ ሳይገርዙ ይተዋሉ። 47ቃል ኪዳኑን አፍርሰዋልና፥ ከቃሉም ወጥተዋልና ያች ጽኑ መዓት ከእግዚአብሔር ታዝዛ በእስራኤል ልጆች ትደረጋለች። የዚህንም ምልክት ሥርዐቱን እንዳልፈጸሙ ከምድር ፈጽሞ ለመጥፋት ሰውነታቸውን እንደ አሕዛብ አድርገዋልና ተበሳጭተው ተሳደቡ። 48በዚችም ምድር ለሚሠራው ስሕተት፥ ኀጢአትም ሁሉ ፈጽሞ ይሰረይ ዘንድ እንግዲህ ወዲህ የኀጢአት ስርየትና ይቅርታ የላቸውም። 49በአራተኛው ወር መባቻ በመምሬ ባለው በግራሩ ሥር ለአብርሃም ተገለጥንለት፤ ከእርሱም ጋር ተነጋገርን። ከሚስቱ ከሳራም ልጅ እንደሚሰጠው ነገርነው፤ ሳራም ይህን ነገር ከአብርሃም ጋር እንደ ተነጋገርን ሰምታለችና ሳቀች። እኛም ዘለፍናት፤ እርስዋም ፈርታ ስለ ተነገረው ነገር እንደ ሳቀች አስተባበለች። 50የልጅዋንም ስም ስሙ ይስሐቅ ተብሎ በሰማይ ጽላት እንደ ተሠራና እንደ ተጻፈ ነገርናት። ያንጊዜም ወደ እርስዋ በተመለስን ጊዜ እርስዋ ወንድ ልጅን ፀነሰች። 51በዚያም ወር እግዚአብሔር በገሞራና በሰዶም፥ በሰቡኢምና በዮርዳኖስ አውራጃ ሁሉ ፍርዱን አደረገ። በእሳትና በድኝ አቃጠላቸው፤ እጅግ ክፉዎችና ኀጢአተኞች እንደ ሆኑ በሰውነታቸውም እየሴሰኑ እንደሚረክሱ፥ በምድር ላይም ርኵሰትን እንደሚሠሩ፥ እነሆ፥ ሥራቸውን ሁሉ እንደ ነገርሁህ እስከዚህች ቀን ድረስ አጠፋቸው። 52እንደዚሁም እግዚአብሔር እንደ ሰዶም ርኵሰት በሠሩባቸው ቦታዎች ሁሉ እንደ ሰዶም ፍርድ ያደርጋል። 53እግዚአብሔርም አብርሃምን አስቦታልና ሎጥን አዳነው፤ ከጥፋትም መካከል አወጣው። ከአዳም ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ በምድር ላይ ያልተደረገ ኀጢአትን እርሱ ከልጆቹ ጋር በምድር አደረገ፤ አባት ከልጁ ጋር ተኝቶአልና። 54ያጠፋቸውና ይነቅላቸው፥ ቅጣታቸውንም እንደ ሰዶም ቅጣት ያደርግ ዘንድ፥ በፍርድ ቀንም በምድር የሰውን ዘር ሁሉ እንዳያስቀርለት፥ እነሆ፥ ታዘዘ። በልጆቹም ሁሉ ላይ በሰማይ ጽላት ተቀረፀ። 55በዚህም ወር አብርሃም ከኬብሮን ተጕዞ ሄዶ በጌራሮን ተራሮች ባሉ በቃዴስና በሱር መካከል ተቀመጠ። 56በአምስተኛው ወር እኩሌታም ከዚያ ተጕዞ በመሐላ ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ።