1አብራም በሕይወት በኖረበት በስድሳኛው ዓመት፥ ይኸውም በአራተኛው ሱባኤ በአራተኛው ዓመት፥ አብራም ሌሊት ተነሥቶ የጣዖታቱን ቤት አቃጠለ። በቤት ያለውንም ዕቃ ሁሉ አቃጠለ። ያወቀ ሰው ግን አልነበረም። 2በሌሊትም ተነሥተው ጣዖቶቻቸውን ከእሳት ውስጥ ያወጡ ዘንድ ወደዱ። 3አራንም ያድናቸው ዘንድ ተወረወረ፤ በላዩም እሳት ነደደበት፤ በእሳትም ተቃጥሎ የከላውዴዎን ዕጣ በምትሆን በዑር በአባቱ በታራ ፊት ሞተ። የከላውዴዎን ዕጣ በምትሆን በዑርም ቀበሩት። 4ታራም የከላውዴዎን ዕጣ ከምትሆን ከዑር ወጣ። እርሱና ልጆቹ ወደ ሊባኖስ ምድርና ወደ ከነዓን ምድር፥ ወደ ካራንም ምድር ይመጡ ዘንድ ወጣ። 5አብራምም ከአባቱ ጋር በካራን ሁለት የዓመቶች ሱባዔ ተቀመጠ። 6በስድስተኛው ሱባዔ በአምስተኛው ዓመት አብራም ተነሣ፤ በሰባተኛው ወር መባቻ ከማታ እስከ ጥዋት ድረስ ከዋክብትን ይቈጥር ዘንድና ስለ ዝናም የዓመቱ ጠባይ ምን እንደሚሆን ያይ ዘንድ በሌሊት ወጥቶ ተቀመጠ። 7ብቻውንም ተቀምጦ ይቈጥር ነበር፥ ቃልም ወደ ልቡ መጣ፤ “የከዋክብት ምልክት ሁሉ፥ የፀሐይና የጨረቃም ምልክት ሁሉ በእግዚአብሔር እጅ ነው። ጥዋትም ማታም ያዘንብ ዘንድ ቢወድ፥ እንዳያዘንብም ቢወድ እኔ ለምን እመራመራለሁ? ሁሉም በእጁ ነው” አለ። 8በዚህችም ሌሊት ጸለየ፥ እንዲህም አለ፥ “አምላኬ አምላኬ ሆይ፥ ልዑል አምላክ፥ አንተ ብቻ ለእኔ አምላክ ነህ፤ አንተ ሁሉን ፈጠርህ፤ የእጅህ ፍጥረት ሁሉ ጸንቶ ይኖራል፤ እኔ አንተንና መንግሥትህን ወደድሁ፤ ከክፉዎች በሰው ልቡና ከሚሠለጥኑ ከመናፍስት እጅ አድነኝ፤ አምላኬ ሆይ፥ አንተን ከመከተል አያስቱኝ፤ እኔንም ዘሬንም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ለዘለዓለም እንዳንስት አድርገን። 9ወደ እነርሱም እመለስ ዘንድ ፊቴን ወደሚሹ ወደ ከላውዴዎን ዑር ልመለስን? ወይስ በዚህ ቦታ ልቀመጥ? ያገለግል ዘንድ በባሪያህ እጅ የቀናውን መንገድ በፊትህ አቅና። አምላኬ ሆይ፥ በልቡናዬ ስሕተት አልሂድ።” 10እርሱም ይህን ተናግሮና ጸልዮ በጨረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል በእኔ እጅ እንዲህ ሲል ወደ እርሱ ተላከ፥ “አንተ ከሀገርህ፥ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤት ወጥተህ እኔ ወደማሳይህ ሀገር ሂድ፤ እጅግም ብዙ ወገን አደርግሃለሁ፤ እባርክህማለሁ፤ ስምህንም ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤ በምድሩም ሁሉ የተባረክህ ትሆናለህ። 11የምድር አሕዛብም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤ የሚመርቁህን እመርቃቸዋለሁ፤ የሚረግሙህንም እረግማቸዋለሁ። ለአንተና ለልጆችህ፥ ለልጅ ልጆችህም፥ ለዘርህም ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ ከአንተም በኋላ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ልጅ ልጅ ዘመን ድረስ አምላክህ እኔ ነኝና አትፍራ።” 12እግዚአብሔር አምላክም እንዲህ አለኝ፥ “ከውድቀት ቀን ጀምሮ ከሰው ልጅ ሁሉ ቋንቋ ተለይቶአልና የተገለጠች ቋንቋን ይሰማና ይናገር ዘንድ አፉንና ጆሮውን ክፈት።” 13እኔም አፉንና ጆሮውን፥ ከንፈሩንም ከፈትሁ፤ በትውልድ ቋንቋው በዕብራይስጥ ቋንቋም ከእርሱ ጋር እናገር ጀመርሁ፤ የአባቶቹንም መጽሐፍ ወሰደ፤ እነዚያም በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፉ ነበሩ። ደግሞም ጻፋቸው፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ ይማራቸው ጀመር። የጸነነውንም ሁሉ እኔ እነግረው ነበር፤ ዝናብም በሚዘንብባቸው በስድስቱ ወሮች ተማራቸው። 14በስድስተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት እንዲህ ሆነ፤ ከአባቱ ጋር ተነጋገረ፤ ከካራን ወደ ከነዓን ሄዶ አይቶአት ወደ እርሱ ይመለስ ዘንድ እንደሚሄድ ነገረው። 15አባቱ ታራም እንዲህ አለው፥ “በሰላም ሂድ፤ የሰላም አምላክም ጎዳናህን ያቅናልህ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን፤ ከክፉ ሁሉ ይጠብቅህ፤ በሚያዩህ ሰዎች ፊት ቸርነትንና ይቅርታን፥ መወደድንም ይስጥህ፤ በአንተም ላይ ክፉ ነገርን ለማድረግ የሰው ልጆች ሁሉ አይሠልጥኑብህ፤ በሰላም ሂድ። 16በእርስዋም ለመኖር ለዐይኖችህ ያማረች ምድርን ብታይ፥ መጥተህ ወደ አንተ ውሰደኝ፤ ለአንተ ልጅ ይሆንህ ዘንድ የወንድምህን የአራን ልጅ ሎጥንም ከአንተ ጋር ውሰደው፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን፤ በሰላም እስክትመለስም ድረስ ወንድምህ ናኮርን በእኔ ዘንድ ተወው፤ ሁላችንም በአንድነት ከአንተ ጋር እንሄዳለን።” 17አብራምም ሚስቱን ሶራንና የወንድሙን የአራን ልጅ ሎጥን ይዞ ከካራን ወደ ከነዓን ሄደ። ወደ ሱርም መጣ፤ እስከ ሰቂሞንም ድረስ ተመላለሰ፤ በረጅም ግራር ሥር አደረ፤ ከኢማት መግቢያ ጀምሮ ረጅም ግራር እስካለበት ድረስ ሀገሪቱ እጅግ ያማረች እንደ ሆነች እነሆ፥ አየ። 18እግዚአብሔርም፥ “ለአንተና ለልጆችህ ይህችን ሀገር እሰጣችኋለሁ” አለው። በዚያም መሠዊያን ሠራ፤ ለተገለጠለት ለእግዚአብሔርም በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መሥዋዕትን አቀረበ። 19ከዚያም ተነሥቶ በምዕራብ አንጻር ወዳለች ወደ ቤቴል ተራራና በምሥራቅ አንጻር ወዳለች ወደ ጋይ ሄደ፤ በዚያም ድንኳኑን ተከለ፤ ባያትም ጊዜ፥ እነሆ፥ ሀገሪቱ ሰፊ ነበረች፤ እጅግም ያማረች ነበረች፤ ሁሉም በእርስዋ ላይ ይበቅላል፤ ወይን፥ በለስ፥ ሮማን፥ ወይራ፥ ግራር፥ ቡጥን፥ ዘይት፥ ዋንዛ፥ ሰኖባር፥ የሊባኖስም ዛፍ፥ የዱርም ዛፍ ሁሉ የሚበቅልባት ናት፤ ውኃውም በተራራው ላይ ነበር። 20የከላውዴዎናውያን ዕጣ ከምትሆን ከዑር አውጥቶ ወደዚህ ተራራ ያመጣውን እግዚአብሔርንም አመሰገነው። 21በሰባተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያው ወር መባቻ እንዲህ ሆነ። በዚያ ተራራ መሠዊያን ሠራ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ፥ “አንተ አምላኬ ሆይ፥ የዘለዓለም አምላክ አንተ ነህ” አለ። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ በሕይወቱም ዘመን ሁሉ እንዳይለየው በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕትን አቀረበ። 22ከዚያም ተነሥቶ ወደ ደቡብ ሄደ፤ እስከ ኬብሮንም ደረሰ። ኬብሮንም ያንጊዜ ተሠርታ ነበር። በዚያም ሁለት ዓመት ተቀመጠ። ሎጥም እስኪገባ ድረስ ወደ ደቡብ ሀገር ሄደ። 23በምድርም ድርቅ ሆነ፤ አብራምም በዚህ ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ወደ ግብፅ ሄደ፤ ሚስቱ ከእርሱ ሳትወሰድ በግብፅ አምስት ዓመት ኖረ። የግብፅ ክፍል የምትሆን ጠናይስም ያንጊዜ ከኬብሮን በኋላ በሰባት ዓመት ተሠርታ ነበር። 24ፈርዖንም የአብራምን ሚስት ሶራን በወሰዳት ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ ስለ አብራም ሚስት ስለ ሶራ እግዚአብሔር ፈርዖንን በደዌ ገረፈ፤ ቤተ ሰቡንም ሁሉ በጽኑ መቅሠፍት ገረፈ። 25አብራምም በገንዘብ፥ በበጎችና በላሞች፥ በአህዮችና በፈረሶች፥ በግመሎችም፥ በወንዶች ባሪያዎችና በሴቶች ባሪያዎች፥ በብርና በወርቅ እጅግ የከበረ ነበረ። የወንድሙ ልጅ ሎጥም በገንዘብ እንደ እርሱ የከበረ ነበረ። 26ፈርዖንም የአብራምን ሚስት ሶራን መለሰ። ከግብፅም ተነሥቶ በቤቴል ምሥራቅና በምዕራብ መካከል ወደ አለው ቀድሞ ድንኳኑን ተክሎበት ወደ ነበረው ወደ ጋይ የመሠዊያ ቦታ ሄደ። 27በሰላም የመለሰው አምላኩ እግዚአብሔርንም አመሰገነው። 28በአርባ አንድ ኢዮቤልዩ፥ በመጀመሪያው ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት እንዲህ ሆነ፤ ወደዚህ ቦታ ተመለሰ፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠል መሥዋዕትን አቀረበ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ፥ “ልዑል አምላክ የምትሆን አንተ እግዚአብሔር ሆይ፥ ለዘለዓለም አምላኬ ነህ” አለ። 29በዚህ ሱባዔ በአራተኛው ዓመት ሎጥ ከእርሱ ተለየ፤ በሰዶምም ኖረ። የሰዶም ሰዎች ግን እጅግ ኀጢአተኞች ነበሩ። የወንድሙም ልጅ ከእርሱ ስለ ተለየ በልቡ አዘነ። ሎጥ በተማረከበት በዚያ ዓመት ልጅ አልነበረውምና። 30ሎጥም ከእርሱ ከተለየ በኋላ በዚህ ሱባዔ በአራተኛው ዓመት እግዚአብሔር አብራምን አለው፥ “በዚያ ትኖር ዘንድ ካለህበት ከዚያ ቦታ ሁነህ ዐይኖችህን ወደ ሰሜንና ሊባ፥ ወደ ባሕርና ምሥራቅ አቅና፤ ይህችን የምታያትን ሀገር ሁሉ ለአንተና ለልጆችህ እስከ ዘለዓለም ድረስ እሰጣችኋለሁና። 31ልጆችህንም እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ፤ ሰው የባሕር አሸዋን መቍጠር ይችል እንደ ሆነ ልጆችህም ይቈጠራሉ፤ ተነሥተህ ቁመቷንና ወርድዋን ዙራት፤ ሁሉንም ተመልከት፤ ለልጆችህ እሰጣታለሁና።” 32አብራምም ወደ ኬብሮን ሄደ፤ በዚያም ተቀመጠ። 33በዚያም ዓመት የኤላም ንጉሥ ኮሎዶጎሞር መጣ፤ የሰናዖርም ንጉሥ አምራፌል፥ የሲላሳር ንጉሥ አሪኦክ፥ የአሕዛብ ንጉሥም ቲርጋል መጡ፤ የገሞራንም ንጉሥ ወጉት። 34የሰዶም ንጉሥ ግን ሸሸ፤ በጨው ባሕር በኩል በሲዲም ሸለቆ ብዙ ሰዎች በጦር ቈስለው ወደቁ፤ ሰዶምንና አዳማን ሴቦኢምንም ማረኩ፤ የአብራምን የወንድሙን ልጅ ሎጥንም ማረኩ፤ ገንዘቡንም ሁሉ ዘረፉ፤ እስከ ዳንም ድረስ ሄደ። ከጦር ያመለጠ አንድ ሰውም መጥቶ የወንድሙ ልጅ ሎጥ እንደ ተማረከ ለአብራም ነገረው። አሽከሮቹንም አስታጠቀ። 35ከቀዳምያት ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐሥራትን እንዲሰጡ በአብርሃምና በልጆቹ ሥርዐት ተሠራ። እግዚአብሔርም ለዘለዓለም ይይዙት ዘንድ በፊቱ ለሚያገለግሉ ለካህናቱ እንዲሰጡአቸው የዘለዓለም ሥርዐትን ሠራ። 36ከሁሉም ከእህሉም፥ ከወይኑም፥ ከዘይቱም፥ ከላሞችም፥ ከበጎችም፥ ከፍየሎችም ለእግዚአብሔር ዐሥራት ይሰጡ ዘንድ ለልጅ ልጅ ለዘለዓለም ሠርቶታልና ለዚህ ሕግ የተወሰነ ዘመን የለውም። 37እርሱም በፊት ደስ ብሎአቸው ሊበሉትና ሊጠጡት ለካህናት ሰጠ። 38የሰዶምም ንጉሥ ወደ እርሱ ደረሰ፤ በፊቱም ሰገደ፥ “ጌታችን አብራም ሆይ ፥ ያዳንኸውን ሰው ስጠን፤ ምርኮው ግን ለአንተ ይሁንልህ” አለው። 39አብራምም፥ “እኔ አብራምን አበለጸግሁት የምትል እንዳትሆን፥ ጐልማሶች ከበሉት በቀር ከአንተ ገንዘብ ሁሉ የክር ፈትልና የጫማ ጠፍር እንዳልወስድ ገናና ወደ ሆነ አምላኬ እኔ እጆችን አነሣለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ ጋር የሄዱ ሰዎች አውናንና ኤሴኬል፥ መምሬም እነርሱ ፈንታቸውን ይውሰዱ” አለው።