1አንተም የእስራኤልን ልጆች በዘመናቸው፥ በየዓመቱ ሁሉ በዓመት አንድ ቀን በጊዜው ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ እዘዛቸው። 2የሚወደደው መታሰቢያ ከእግዚአብሔር ፊት ይመጣል። በሁሉ እንደ ታዘዘ በጊዜው በዓልን ባደረጉ ጊዜ በዚያ ዘመን ፈጽሞ ለማጥፋት መቅሠፍት አይመጣባቸውም። 3ከእንግዲህም ወዲህ መበላቱ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውጭ አይሁን፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ትይዩና በእስራኤል ወገኖች ሁሉ ፊት በጊዜው ያድርጉት። የመጣዉ ሰው ሁሉ ከሃያ ዐመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለ በአምላካችሁ ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር ፊት በዕለቱ ይብላው፥ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ይበሉት ዘንድ እንደዚህ ተጽፎአልና፥ ተሠርቶአልምና፤ 4የእስራኤል ልጆች ይዘዋት ወደሚኖሩ ወደ ከነዓን ከገቡ በኋላ፥ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም እስኪሠራ ድረስ ሠራዊቶቻቸው ከያዙአቸው ሀገሮች በአንዱ ቦታ በምድር መካከል የእግዚአብሔርን ድንኳን ይተክላሉ። 5መጥተውም በእግዚአብሔር ድንኳን መካከል የፋሲካን በዓል የሚያደርጉ ይሁኑ። በዓመት በዓመትም በእግዚአብሔር ፊት ይረዱት። 6በወረሱአት ሀገር ላይ በእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ በተሠራባት ቀን ወደዚያ ሄደው ፀሐይ ሲገባ ከቀኑ በሦስተኛው ክፍል በማታ ጊዜ የፋሲካውን በግ ይረዱ፤ ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ይርጩት፤ ስቡንም በመሠዊያው ላይ ባለ በእሳቱ ላይ ያኑሩት። ሥጋውንም በእግዚአብሔር ፊት በቤተ መቅደስ ዐደባባይ በእሳት ጠብሰው ይብሉት። 7በእግዚአብሔር ድንኳን ነው እንጂ፥ ያም ባይሆን ስሙ በሚጠራበት በቤቱ ፊት ነው እንጂ በከተማቸውና በአውራጃቸው ሁሉ ፋሲካን ማድረግ አይችሉም፤ እግዚአብሔርንም ከመከተል ወጥተው አይሳቱ። 8አንተም ሙሴ፥ ዓመቱን በዓመት፥ ቀኑንም በቀን ታደርገው ዘንድ እንደ ታዘዘልህ የፋሲካውን ሥርዐት ይጠብቁ ዘንድ፥ በዐሉን ሊያደርጉ ሰባት ቀን ቂጣ ይበሉ ዘንድ፥ ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ ባሕሩን ተሻግራችሁ ወደ ሱር ምድረ በዳ እስክትደርሱ ድረስ ይህችን በዓል በመቸኮል አድርጋችኋታልና በባሕርም ዳርቻ ላይ ፈጽማችኋታልና መሥዋዕት በሚሠዋባቸው በእነዚህ በሰባቱ ቀኖች በአምላካችሁ መሠዊያ ላይ ዕለት ዕለት ቍርባኑን ወደ እግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። 9ከዚህም ሥርዐት በኋላ በሱባዔ የሚቈጠረውን ቀን በሲና ምድረ በዳ ነገርሁህ። ይህችውም ምድረ በዳ በሲናና በኤሎም መካከል ያለች ናት። የምድር ሰንበታትንም በደብረ ሲና ነገርሁህ። በዓመቶች ሱባዔ ውስጥ በኢዮቤልዩ የሚቈጠሩ ዓመቶችንም ነገርሁህ። ዓመቱን ግን ወደምትይዙአት ምድር እስክትገቡ ድረስ አልነገርንህም። በእርስዋም ላይ በመኖራቸው ምድር ዕረፍትን ታድርጋለች። የኢዮቤልዩንም ዓመት ያውቃሉ። 10ስለዚህ ነገር በዓመቶች የሚቈጠረውን ሱባዔ ሠራሁልህ። አዳም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከዚህች ቀን ድረስ ያለው ዘመን አርባ ዘጠኝ ኢዮቤልዮታትና አንድ ሱባዔ ከሁለት ዓመት ነው። በምዕራብ በኩል ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ምድረ ርስት ማዶ እስኪገቡ ድረስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለማወቅ ገና አርባ ዘመን ቀርቶአል። እስራኤል ከዝሙት፥ ከበደል፥ ከርኵሰት፥ ከመተዳደፍ፥ ከኀጢአት፥ ከስሕተትም ሁሉ እስኪነጻ ድረስ ብዙ ኢዮቤልዮታት ያልፋሉ። 11በምድርዋም ሁሉ ተዘልሎ ይኖራል፤ ከእንግዲህም ለእርሱ ማንም ባላጋራ አይኖርም። ምንም ክፉ ነገር አይኖርም። ምድርም ከዚያች ቀን ጀምሮ እስከ ዘመኑ ፍጻሜ ድረስ ትነጻለች። 12የሰንበታትንም ሥርዐት እነሆ፥ ጻፍሁልህ። የሥርዐቱንም ፍርድ ጻፍሁልህ። በስድስቱም ቀኖች ሥራህን ሥራ። 13ሰባተኛዪቱ ቀን ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከመፍጠር ያረፈባት ቀን ናትና፥ እናንተና ልጆቻችሁ፥ ወንዶች ባሪያዎቻችሁና ሴቶች ባሪያዎቻችሁም፥ ከብቶቻችሁም ሁሉ፥ በአንተ ዘንድ የሚኖር መጻተኛም ቢሆን ሥራውን ሁሉ አትሥሩባት። በዚያችም ቀን ማንኛውንም ሥራ የሚሠራባት ሰው ይሙት። ይህችን ቀን የሚሽራት ሰው ሁሉ፥ ከሚስቱም ጋር የሚገናኝባት ሰው፥ ገሥግሦም ሄዶ ሥራን ይሠራ ዘንድ ነገርን የሚነጋገርባት ሰው ሞትን ይሙት። 14የሚሸጥባትና የሚለውጥባትም ሰው ሁሉ፥ ውኃንም የሚቀዳ ሰው፥ በስድስተኛዪቱም ቀን ያላዘጋጀ፥ ከድንኳኑ፥ ወይም ከቤቱ ያወጣ ዘንድ የሚሸከመውን ሸክም ሁሉ የሚያነሣ ሰው ይሙት። 15በስድስተኛው ቀን ያዘጋጃችሁትን በልታችሁና ጠጥታችሁ ለማክበር በዚህች ቀን ከሥራው ሁሉ ዕረፉባት እንጂ፥ በዓል የምታደርጉባትን ቀን የሰጣችሁን አምላካችሁን እግዚአብሔርንም አመስግኑባት እንጂ በሰንበት ቀን ምንም ሥራን አትሥሩ። የተቀደሰች ቀን ናት፤ በዘመናቸው በቀኑ ሁሉ ይህች ቀን ለእስራኤል ሁሉ የተቀደሰች የመንግሥት ቀን ናት። 16በዚህች የበዓል ቀን በልተውና ጠጥተው ሊጠግቡባት፥ በእግዚአብሔር ፊት በየቀኑና በየሱባዔው ዕጣንን ከማጠን፥ ቍርባንንም ከማቅረብ፥ መሥዋዕትንም ከመሠዋት በቀር ሰው ከሚሠራው ሥራ ሁሉ ሊያርፍባት እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠው ታላቅ ክብር ናትና አክብሩአት። 17በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሰንበት ቀን ይህ ሥራ ብቻ ይሠራ። የእስራኤልን ልጆች ኀጢአት ያስተሰርዩ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለው መባን ለመታሰቢያ ዕለት ዕለት ያቅርቡ። እንደ ታዘዘም ለዘለዓለሙ ዕለት ዕለት ይቀበላቸዋል። 18ሥራን የሚሠራባት ሰው ሁሉ፥ መንገድንም የሚሄድባት ሰው፥ የሚያርስባትና የሚቈፍርባትም ሰው፥ በቤቱም ቢሆን፥ በሁሉም ቦታ ቢሆን፥ እሳት የሚያነድባት ሰው፥ በእንስሳውም ላይ የሚጭን ሰው፥ በመርከብም በባሕር የሚሄድ ሰው፥ 19ማናቸውንም መትቶ የሚገድል ሰው ሁሉ፥ እንስሳንና ወፍንም የሚያርድባት ሰው፥ አውሬም ቢሆን ወፍም ቢሆን ዓሣም ቢሆን የሚያጠምድ ሰው፥ የሚጾምባትም ሰው፥ በሰንበት ቀን ጠብ የሚያነሣ፥ ከዚህ ሥርዐትም ወጥቶ ይህን ሁሉ ሥራ በሰንበት ቀን የሚሠራ ሰው ይሙት። 20የበዓሉንና የቀኑን ሥርዐት በየዘመኑ አከፋፈል እጽፍልህ ዘንድ በእጄ በሰጠኝ በሰማይ ጽላት እንደ ተጻፈ፥ ምድር ዕረፍት እንድታደርግ እንደ ታዘዘ፥ የእስራኤል ልጆች በዓልን የሚያደርጉ ይሆኑ ዘንድ ሥራን የሚሠራባት ሰው ሁሉ ይሙት።