አይሁድ ጠላቶቻቸውን እንደ ተበቀሉ
1አዳር በሚባለውም በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በዐሥራ ሦስተኛው ቀን ንጉሡ የጻፈው ደብዳቤ ደረሰ። 2በዚያችም ቀን የአይሁድ ጠላቶች ጠፉ። ስለፈሩአቸውም አይሁድን የሚቃወም ሰው አልነበረም። 3መርዶክዮስን መፍራትም በላያቸው ስለ ወደቀ በየሀገሩ የነበሩ አዛውንትና ሹሞች፥ አለቆችም፥ የንጉሡም ጸሓፊዎች ሁሉ አይሁድን አከበሩ። 4መርዶክዮስ በመንግሥቱ ሁሉ ይከበር ዘንድ የንጉሡ ደብዳቤ ያስገድድ ነበርና፤ 5አይሁድም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በሰይፍ እየመቱ ገደሉአቸው፤ አጠፉአቸውም፤ በሚጠሉአቸውም ላይ እንደ ወደዱ አደረጉባቸው። 6አይሁድም በሱሳ ከተማ አምስት መቶ ያህል ሰዎችን ገደሉ፤ አጠፉም። 7ፈርሰኔስ፥ ደልፎን፥ ፋስጋ፤ 8ፋርዳታ፥ በርያ፥ ሰርበካ፤ 9መርመሲማ፥ ሩፋዮስ፥ አርሳዮስ፥ ዛቡታዮስ የሚባሉትን፥ 10የቡጊያዊው የሐመዳቱን ልጅ የአይሁድን ጠላት የሐማን ዐሥሩን ልጆች ገደሉ፤ በዚያም ቀን ገንዘባቸውን ሁሉ ዘረፉ። 11በሱሳ ከተማ የተገደሉት ሰዎች ቍጥርም ወደ ንጉሡ ተላለፈ። 12ንጉሡም ንግሥቲቱን አስቴርን፥ “አይሁድ በሱሳ ከተማ አምስት መቶ ሰዎችን ገደሉ፤ አጠፉአቸውም፤ በቀሩትስ በንጉሡ ሀገሮች እንዴት አድርገው ይሆን? እንግዲህስ ይደረግልሽ ዘንድ የምትፈልጊው ምንድን ነው?” አላት። 13አስቴርም፥ “አይሁድ ነገ ደግሞ እንዲሁ እንዲያደርጉ፥ ዐሥሩንም የሐማ ልጆች በግንድ ላይ እንዲሰቅሉ ይፈቀድላቸው፤” አለች። 14ንጉሡም ይህ ይደረግ ዘንድ ፈቀደ፤ በከተማ ለሚኖሩ አይሁድም የሐማን ልጆች አስከሬን ይሰቅሉ ዘንድ አዘዘ። 15አይሁድም አዳር በሚባለው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በሱሳ ተሰብስበው ሦስት መቶ ያህል ሰዎችን ገደሉ፤ ነገር ግን ንብረታቸውን አልዘረፉም። 16የቀሩትም በንጉሡ ሀገር ያሉ አይሁድ ተሰብስበው እርስ በርሳቸው ተረዳዱ፤ ከጠላቶቻቸውም ዐረፉ፤ ከሚጠሉአቸውም አዳር በሚባለው ወር በዐሥራ ሦስተኛው ቀን ዐሥራ አምስት ሺህ ገደሉ፤ ነገር ግን የዘረፉት የለም። 17በዚያም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ዐረፉ፤ ያችንም ቀን ከግብዣና ከደስታም ጋር የዕረፍት ቀን አደረጓት። 18በሱሳ ከተማ የነበሩት አይሁድ ግን በዐሥራ አራተኛው ቀን ተሰብስበው ዐረፉ፤ በዐሥራ አምስተኛውም ቀን በዓልና ደስታ አደረጉ። 19ስለዚህ በገጠር መንደሮች ተበታትነው የሚኖሩ አይሁድ አዳር በሚባለው ወር ዐሥራ አራተኛውን ቀን የደስታና የመጠጥ፥ የመልካምም ቀን፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበት ቀን ያደርጉታል።
የፉሪም በዓል
20መርዶክዮስም ይህን ነገር በመጽሐፍ ጻፈው፤ በንጉሡም በአርጤክስስ ሀገሮች ሁሉ፥ በሩቅም በቅርብም ላሉት ሁሉ ላከው። 21በየዓመቱም አዳር በሚባለው ወር ዐሥራ አራተኛውንና ዐሥራ አምስተኛውን ቀን የደስታ ቀኖች አድርገው ይጠብቋቸው ዘንድ፥ 22በእነዚያ ወራት አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍትን አግኝተዋልና፥ አዳር የተባለውም ወር ከኀዘን ወደ ደስታ፥ ከልቅሶም ወደ መልካም ቀን የተለወጠበት የግብዣና የደስታም ቀን፥ ለወዳጆቻቸውና ለድኆችም ስጦታ የሚልኩበት ቀን ነውና። 23አይሁድም መርዶክዮስ እንደ ጻፈላቸው ተቀበሉት፤ 24መቄዶንያዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማም አይሁድን በተንኰል ያጠፋ ዘንድ ተዋግቶአቸው ነበር፤ ዐዋጅም ዐውጆ ነበር፤ ዕጣም ጥሎ ነበር። 25እንዲሁም ወደ ንጉሡ ገብቶ መርዶክዮስን ይሰቅለው ዘንድ ጠይቆ ነበር፤ ነገር ግን በአይሁድ ላይ የተተነኰለው ክፉ ተንኰል በራሱ ላይ ተመለሰ። እርሱም ልጆቹም ተሰቀሉ። 26ስለዚህም እነዚህ ቀኖች ዕጣ ስለ ተጣለባቸው ፉሪም ተባሉ። በዚችም ደብዳቤ ስለ ተጻፈው ቃል ሁሉ፥ በውስጥዋም ስለ ተገኘውና ስላገኙአቸውም ነገሮች ሁሉ በቋንቋቸው ፉሪም ይሏቸዋል። 27አይሁድም ለራሳቸው፥ ለዘራቸውና ከእነርሱ ጋር አንድ ለሚሆኑ ሁሉ ከዚህ ሥርዐት እንዳይወጡ የተጻፈውን ተቀበሉ። እነዚህም ቀኖች በየትውልዳቸውና በየወገናቸው፥ በየሀገራቸውም፥ በየከተማቸውም ለዘለዓለም የታሰቡና የተከበሩ ይሆናሉ። 28እነዚህም የፉሪም ቀኖች ሁልጊዜ ይከበራሉ፤ መታሰቢያቸውም በትውልድ ሁሉ አይደመሰስም። 29የአሚናዳብም ልጅ ንግሥቲቱ አስቴርና አይሁዳዊው መርዶክዮስ ያደረጉትን ሁሉ ጻፉ። የፉሪምንም ደብዳቤ አጸኑ። 30ደብዳቤዎቹንም በአርጤክስስ መንግሥት በመቶ ሃያ ሰባቱ ሀገሮች ወዳሉ አይሁድ ሁሉ በሰላምና በእውነት ቃል ላኩ። 31እነዚህንም የፉሪም ቀኖች መርዶክዮስና ንግሥቲቱ አስቴር ለራሳቸው የጾም ቀን አደረጓቸው፤ በሕይወታቸውና በምክራቸውም ማሉ። 32አስቴርም ይህን ነገር በትእዛዝ አጸናችው፤ ለመታሰቢያም ተጻፈ።