አስቴር አይሁድን እንደ አዳነች
1በዚያም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የጠላት የሐማን ንብረት ሁሉ ለንግሥቲቱ ለአስቴር ሰጠ። ንጉሡም መርዶክዮስን ጠራው፤ አስቴር በቤቱ እንዳደገች ነግራው ነበርና። 2ንጉሡም ከሐማ ያወለቀውን ቀለበቱን አወጣ፤ ለመርዶክዮስም ሰጠው። አስቴርም በሐማ ንብረት ሁሉ ላይ መርዶክዮስን ሾመችው። 3አስቴርም እንደ ገና ለንጉሡ ነገረችው፤ በእግሩም ላይ ወድቃ የሐማን ክፋትና በአይሁድ ላይ የተተነኰለውን ተንኰል ይሽር ዘንድ ለመነችው። 4ንጉሡም የወርቁን ዘንግ ለአስቴር ዘረጋላት፤ አስቴርም ተነሥታ በንጉሡ ፊት ቆመች። 5እንዲህም አለች፥ “ንጉሥ ሆይ፥ ደስ ቢያሰኝህ በፊትህም ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ በመንግሥትህ ሁሉ ያሉትን አይሁድ ለማጥፋት ሐማ የጻፋቸው ደብዳቤዎች ሁሉ ይገለበጡ ዘንድ ላክ። 6እኔ በሕዝቤ ላይ የሚወርደውን ክፉ ነገር አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ወይስ ከዘመዶች ጥፋት በኋላ እኖር ዘንድ እንዴት እችላለሁ?” 7ንጉሡም ንግሥቲቱን አስቴርን አላት፥ “እነሆ የሐማን ገንዘብ ሁሉ ፈጽሜ ሰጠሁሽ፤ እርሱንም እጆቹን በአይሁድ ላይ ስለዘረጋ በግንድ ላይ ሰቀልሁት፤ እንግዲህ ምን ትፈልጊያለሽ? 8በንጉሡም ስም የተጻፈውንና በንጉሡ ቀለበት የታተመውን እንቢ የሚል የለምና እናንተ ደግሞ ደስ የሚያሰኛችሁን በእኔ ስም ጻፉ፤ በቀለበቴም አትሙ።” 9በዚያም ዓመት ኔሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሃያ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሓፊዎች ተጠሩ፤ ንጉሡም እንዳዘዘው ሁሉ ከሕንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሃያ ሰባቱ ሀገሮች ላሉ ሹሞችና አለቆች፥ አዛውንትም፥ ለእያንዳንዱም ሀገር እንደ ጽሕፈቱ፥ ለእያንዳንዱም ሕዝብ እንደ ቋንቋው፥ ለአይሁድም እንደ ጽሕፈታቸውና እንደ ቋንቋቸው ተጻፈ። 10በንጉሡም በአርጤክስስ ስም ጻፉ፤ በንጉሡም ቀለበት አትመው ደብዳቤውን በመልእክተኞች ላኩ። 11በከተሞች ሁሉ እንደ ሕጋቸው ያደርጉ ዘንድ፥ እርስ በርሳቸውም ይረዳዱ ዘንድ ጠላቶቻቸውንና የሚነሡባቸውን ሁሉ እንደ ወደዱ ይቋቋሙ ዘንድ አዘዛቸው። 12ይህም አዳር በሚባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር በዐሥራ ሦስተኛው ቀን በንጉሡ በአርጤክስስ ሀገሮች ሁሉ በአንድ ቀን እንዲሆን ነው።
አይሁድን ለመታደግ የወጣ የንጉሥ ዐዋጅ
13የዐዋጁም ደብዳቤ ግልባጭ የሚከተለው ነው። 14በቸርነትና ሹመትን ፈጥኖ በመስጠት ከሚጠቅሙአቸው ክብርን ያገኙ ብዙዎች ትዕቢትን አበዙ። 15ክፉ የሚያደርጉትም ለእኛ በሚገዙት ላይ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ጥጋባቸውን መታገሥ ባለመቻላቸው የሚጠቅሙአቸውን ይተናኰሉ ዘንድ ያስባሉ። 16የሰውን ምስጋና የሚክዱ ብቻ አይደሉም፤ ዳግመኛም አዲሶች ባለጸጎች እንደ መሆናቸው በመታበይ ራሳቸውን ከፍ ያደርጋሉ። ሁልጊዜም ሁሉን ከሚመለከት፥ ኀጢአትንም ከሚጠላ ከእግዚአብሔር ፍርድ የሚያመልጡ ይመስላቸዋል። 17ነገር ግን ብዙ ጊዜ የሚገዙልን በመስማማት ይገዙልንና ያገለግሉን ዘንድ የታመናቸው የተዘጋጁ እነዚያ ሰዎች ንጹሕ ደምን በማፍሰስ አንድ ሆኑ፤ 18ሐሰትንም በመምከር በየውሀትና በፀጥታ የምትኖር መንግሥትን አታለው የሚያስጨንቅ መከራን መከሩባቸው። 19ነገር ግን በማሰብ ይቀራል፤ ይኸውም ከእኛ አስቀድሞ ከነበሩ ሰዎች ይልቅ እንድናበልጥ አይደለም፤ ሕጉን እንደ ተቀበልነው እንዲሁ ጸንተን እንኖራለን፤። 20ነገር ግን ከዚህ በኋላ ያለ ሕግ የተደረገውን ነገር እንመረምራለን፤ በሚገባ መፍረድ የማይችሉ፥ የማይገባቸውን ክብር አግኝተዋልና። 21ከዚህም በኋላ መንግሥታችን ያለ ሁከት ጸንታ የምትኖርበትን፥ የሕዝቡም ኑሮ የሚቃናበትን አስበን፥ የተገለጠውንም ሁልጊዜ በየዋህነት እንፈርዳለን። 22መቄዶናዊ የሐመዳቱ ልጅ ሐማ ግን ከእውነት ነገር የወጣና የፋርስ ደም የሌለው እንደ መሆኑ ከእኛ ቸርነት ርቆአል፤ በእኛ ዘንድም ሲኖር ባዕድ ሁኖአል። 23እርሱም በሕዝቡ ላይ ሁሉ ሹመትንና ባለሟልነትን አገኘ። አባታችን እስክንለውና የመንግሥታችንም ዙፋን ሁለተኛ እስክንለው የወደደውን ሹመት አገኘ። 24ዳግመኛም ይህ አልበቃውም፤ ነገር ግን ታብዮ ከመንግሥታችን ያወጣን ዘንድ፥ ሰውነታችንንም ወደ ጥፋት ይወስድ ዘንድ አሰበ። 25በሁሉ የሚጠቅመንንና የሚያድነንን፥ የሚያገለግለንንም መርዶክዮስን፥ ያለ ነቀፋ የመንግሥታችን ተባባሪ የምትሆን አስቴርንም በብዙ ተንኰል፥ ነገርንም በማሳመር ከወገኖቻቸው ሁሉ ጋር ያጠፋቸው ዘንድ ለመነ። 26ስለዚህም ነገር በየዋህነት እንኖራለንና የፋርስን መንግሥት አገኘን፤ እሱ ግን ወደ መቄዶን ያዛውረው ዘንድ አሰበ። 27“እኛ ግን ያጠፋቸው ዘንድ የፈለጋቸውን አይሁድን በክፋት እንዳይደሉ፥ ነገር ግን በእውነተኛ ሕጋቸው እንደሚኖሩ አገኘናቸው። 28በእውነት ለእኛና ከእኛ በፊት ለነበሩ እንደ ልባችን ቅንነት መንግሥትን ያዘጋጀልን የልዑሉና የታላቁ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ናቸው። 29ነገር ግን የሐመዳቱ ልጅ የሆነ የሐማን ትእዛዝ፥ የላከውንም ደብዳቤ ቃል ባትሰሙ መልካም ነገር ታደርጋላችሁ። 30እርሱ ራሱ ይህን ነገር አስቦበታልና፥ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ፈጥኖ ፍዳውን ስለ ከፈለው ከወገኖቹ ሁሉ ጋር በሱሳ ከተማ አደባባይ ተሰቀለ። 31ይህችንም ደብዳቤ በግልጥ ዘርግታችሁ በቦታው ሁሉ አሳዩአት፤ አይሁድንም በሕጋቸው ጸንተው ይኖሩ ዘንድ ተዉአቸው። 32ዐሥራ ሁለተኛው ወር አዳር በባተ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን ከዚያች ጀምሮ እስከዚች ሰዓት ድረስ ቀድሞ በመከራቸው ወራት ከአስጨነቋቸው ራሳቸውን ይከላከሉ ዘንድ ርዱአቸው። 33ሁሉን የሚችል እግዚአብሔርም በጥፋታቸው ፋንታ ለእነዚህ ለተመረጡ ሕዝብ ደስታን አደረገላቸው። 34እናንተም በተጠሩት በበዓሎቻችሁ በታወቀ ቀን እንደዚሁ አድርጉ። 35እነሆ፥ ከዚህ በኋላም ለእኛና ለፋርስ ሰዎች፥ በጎ ነገርን ለሚያደርጉ ሕይወት ይሆንላቸዋል፤ እኛን ይወነጅሉ ዘንድ ለሚወድዱ ግን የጥፋታቸው መታሰቢያ ይሆናል። 36ሀገሩ ሁሉ፥ ወይም ከተማው በሁሉም ቦታ እንዲህ ያላደረገ በጦርና በእሳት በመዓት ይጠፋል፤ ጥፋትም የሚሆነው በሰዎች ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን በአውሬዎችና በዎፎችም ላይ ይሆናል።” 37አይሁድም ጠላቶቻቸውን እንዲበቀሉ በዚያ ቀን ይዘጋጁ ዘንድ የደብዳቤው ቅጂ በግዛቱ ሁሉ በግልጥ ቦታ ተዘርግቶ እንዲታይ ተደረገ። 38ፈረሰኞችም የንጉሡን ትእዛዝ ይፈጽሙ ዘንድ ቸኩለው ወጡ። ዐዋጁም በሱሳ ከተማ ተነገረ። 39መርዶክዮስም ልብሰ መንግሥት ለብሶ፥ የወርቅ አክሊልም ደፍቶ፥ ከሐምራዊ ግምጃ የተሠራ መጐናጸፊያም ተጐናጽፎ ወጣ፤ በሱሳ ከተማ የነበሩትም አይተው ደስ አላቸው። 40ለአይሁድም ብርሃንና ደስታ ሆነ። 41ትእዛዙም በታወጀበት፥ ደብዳቤውም በተገኘበት አውራጃና ከተማ ሁሉ ለአይሁድ ደስታና ተድላ፥ የግብዣም ቀን፥ መልካምም ቀን ሆነ። ከአሕዛብም ብዙዎች አይሁድን ስለ ፈሩ ተገዝረው አይሁድ ሆኑ።