ሐማ እንደ ተሰቀለ
1ንጉሡና ሐማም ከንግሥቲቱ ከአስቴር ጋር ይጋበዙ ዘንድ ገቡ። 2በሁለተኛውም ቀን ንጉሡ በወይኑ ጠጅ ግብዣ ሳለ አስቴርን፥ “ንግሥት አስቴር ሆይ! ምን ሁነሻል? የምትለምኚኝ ምንድን ነው? የምትሺውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል” አላት። 3ንግሥቲቱም አስቴር መልሳ አለች፥ “ንጉሥ ሆይ! በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ ሕይወቴ በልመናዬ፥ ሕዝቤም በመሻቴ ይሰጠኝ። 4እኔና ሕዝቤ ለመጥፋት፥ ለመገደልና ለመደምሰስም ተሸጠናልና። እኛና ልጆቻችን ባሪያዎችህ ልንሆን ተሸጠን ቢሆን ኑሮ ዝም ባልሁ ነበር፤ ጠላት ወደ ንጉሡ አደባባይ መግባት አይገባውም ነበርና።” 5ንጉሡም፥ “ይህን ያደርግ ዘንድ የደፈረ ማን ነው?” ብሎ ተናገራት። 6አስቴርም፥ “ያ ጠላትና ባላጋራ ሰው ይህ ክፉው ሐማ ነው” አለች። ሐማም በሰማ ጊዜ በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት ደነገጠ። 7ንጉሡም የወይን ጠጅ ከመጠጣቱ ተነሣ፤ ወደ አታክልት ቦታ ውስጥም ሄደ። ሐማም ክፉ ነገር እንደ ደረሰበት አይቶአልና ንግሥቲቱን ይለማመጥ ጀመር። 8ንጉሡም ከአታክልቱ ቦታ ተመለሰ፤ ሐማም ንግሥቲቱን እየተለማመጠ በአልጋው ላይ ወድቆ ነበር። ንጉሡም ደግሞ፥ “በቤቴ ሚስቴን ይጋፋታልን?” አለ። ሐማም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ፊቱ ጠቈረ። 9በንጉሡም ፊት ካሉት ጃንደረቦች አንዱ ቡጋታን፦ “እነሆ ሐማ ለንጉሡ በጎ ለተናገረው ለመርዶክዮስ ያዘጋጀው ርዝመቱ አምሳ ክንድ የሆነ ግንድ በሐማ ቤት ተተክሎአል” አለ። ንጉሡም በእርሱ ላይ ስቀሉት አለ። 10ሐማንም ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ ሰቀሉት፤ በዚያም ጊዜ የንጉሡ ቍጣ በረደ።