1በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር እንቅልፍን ከንጉሡ አጠፋ፤ የዘመኑንም ታሪክ መጽሐፍ ያመጣና ያነብለት ዘንድ ጸሓፊውን አዘዘ። 2ደጁንም ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱ ንጉሥ አርጤክስስን ይገድሉ ዘንድ እንደ ፈለጉና መርዶክዮስም ሰምቶ እንደ ነገረው ተጽፎ ተገኘ። 3ንጉሡም “ስለዚህ ነገር ለመርዶክዮስ ምን ክብርና ደግነት አደረግንለት?” አለ። ንጉሡንም የሚያገለግሉ ብላቴኖች “ለመርዶክዮስ ምንም አላደረግህለትም” አሉት። 4ንጉሡም የመርዶክዮስን ደግነት ሲናገር እነሆ ሐማ ወደ አደባባይ ደረሰ። ንጉሡም፥ “በአደባባይ ማን አለ?” አለ። ሐማም ባዘጋጀው ግንድ ላይ መርዶክዮስን ለማሰቀል ለንጉሡ ይናገር ዘንድ ወደ ውስጥ ገባ። 5የንጉሡም ብላቴኖች፥ “እነሆ ሐማ በአደባባይ ቆሞአል” አሉት። ንጉሡም “ጥሩት” አለ። 6ንጉሡም ለሐማ አለው፥ “እኔ ላከብረው ለምወድደው ሰው ምን ላድርግለት?” ሐማም በልቡ፥ “ንጉሡ ከእኔ ይልቅ ማንን ያከብር ዘንድ ይወድዳል?” አለ። 7ንጉሡንም እንዲህ አለው፥ “ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግ። 8የንጉሡ ብላቴኖች ንጉሡ የሚለብሰውን የክብር ልብስ፥ ንጉሡም የሚቀመጥበትን ፈረስ ያምጡለት። 9ልብሱንና ፈረሱንም ከንጉሡ አዛውንት በዋነኛው እጅ ያስረክቡት፤ ንጉሡም ያከብረው ዘንድ የሚወድደውን ሰው ያልብሱት፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጠው በከተማዪቱ አደባባይ ያሳልፉት፤ በፊቱም ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ተብሎ ዐዋጅ ይነገር።” 10ንጉሡም ሐማን፥ “መልካም ብለሃል፤ እንደ ተናገርኸውም ልብሱንና ፈረሱን ውሰድ፤ በንጉሡም በር ለሚቀመጠው ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስ እንዲሁ አድርግለት፤ ከተናገርኸው ሁሉ ምንም አታስቀር” አለው። 11ሐማም ልብሱንና ፈረሱን ወሰደ፤ መርዶክዮስንም አለበሰው፤ በፈረሱም ላይ አስቀመጠው፤ በከተማዪቱም አደባባይ በፊቱ አሳለፈው። በፊቱም “ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል” ብሎ ዐዋጅ ነገረ። 12ከዚህም በኋላ መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ ዐደባባይ ተመለሰ። ሐማ ግን አዝኖና ራሱንም ተከናንቦ ወደ ቤቱ ሄደ። 13ሐማም ለሚስቱ ለዞሳራና ለወዳጆቹ ሁሉ ያገኘውን ሁሉ አጫወታቸው። ወዳጆቹና ሚስቱM “በፊቱ መውደቅ የጀመርህለት መርዶክዮስ ከአይሁድ ወገን የሆነ እንደ ሆነ በፊቱ ፈጽመህ ትወድቃለህ እንጂ አታሸንፈውም፤ ሕያው እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነውና” አሉት። 14እነርሱም ሲናገሩት ሳሉ እነሆ የንጉሡ ጃንደረቦች መጡ፤ አስቴርም ወዳዘጋጀችው ግብዣ ይመጣ ዘንድ ሐማን አስቸኰሉት።