አስቴር ንጉሡንና ሐማን ግብዣ እንደ ጠራች
1ከዚህም በኋላ በሦስተኛው ቀን ጸሎቷን በጨረስች ጊዜ የኀዝን ልብስዋን አወለቀች፤ የክብር ልብስዋንም ለበሰች፤ 2የም ታስፈራም ሆነች፤ ሁሉን የሚመለከት አዳኝ እግዚአብሔርንም ጠራችው። 3ሁለቱን ደንገጥሮችዋንም አስከትላ ሄደች፤ ትወዳታለችና ላንዲቱ ትራራላት ነበር፤ ሁለተኛዪቱም ልብስዋን ተሸክማ ትከተላት ነበር። እርስዋ ግን በጌጡ ሁሉ ፈጽማ አጊጣ ነበር፤ ወደ ወዳጆችዋ እንደምትሄድም ፊቷ የሚያበራ ሆነ፤ ልብዋ ግን ሞትን ከመፍራት የተነሣ አዝኖ ነበር። 6በሩን ሁሉ ገብታ ወደ ንጉሡ ደረሰች፤ እርሱ ግን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ነበር። 7ዋጋው ብዙ የሆነ፥ ሁለንተናውም በዕንቍና በወርቅ ያጌጠ የክብር ልብሱን ለብሶ ነበር፤ ፈጽሞም ያስፈራ ነበር። ፊቱም ከክብሩ ጋር ተመልሶ በቍጣ አያት፤ ንግሥቲቱም ፈራች፤ ጠወለገችም፤ ለመውደቅም ተፍገመገመች፤ በፊቷ የምትሄድ የብላቴናዋንም ራስ ተደገፈች። 8እግዚአብሔርም የንጉሡን ልቡና ወደ የዋህነት መለሰው፤ ታገሣትም፤ ከዙፋኑም ተንሥቶ ስቦ በአጠገቡ አስቀመጣት፤ በበጎ ቃልም ያባብላት ጀመር፤ እንዲህም አላት፥ “አስቴር ሆይ! ምን ሆንሽ? እኔ ወንድምሽ ነኝ፤ እንደማትሞች እመኚ፤ የአገራችን ሕግ ልዩ ነውና፤” 11የወርቁንም ዘንግ አንሥቶ በአንገቷ ላይ አኖረው፤ እቅፍ አድርጎ ይዞም “ንገሪኝ” አላት። 13እርስዋም አለች፥ “አንተ ድንቅ ነህና፥ ፊትህም ሞገስን የተመላ ነውና ክብርህን ከመፍራት የተነሣ ጌታዬ እንደ መልአከ እግዚአብሔር ሆነህ ባየሁህ ጊዜ ልቡናዬ ደንገጠብኝ።” 15ስትናገርም ተዝለፍልፋ ወደቀች። ንጉሡም ደነገጠ፤ ሰዎቹም ሁሉ ደነገጡ፤ ያጽናኗትም ጀመር። 17ንጉሡም፥ “አስቴር ሆይ! ምን ትፈልጊያለሽ? ምንስ ትለምኛለሽ? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ጠይቂ፤ ሁሉም ይሰጥሻል” አላት። 18አስቴርም፥ “የግብዣ ቀን አለኝ፤ ንጉሡ ቢፈቅድ ወደ አዘጋጀሁለት ግብዣ ከሐማ ጋር ዛሬ ይምጣ” አለች። 19ንጉሡም፥ “አስቴር እንዳለች ይደረግ ዘንድ ሐማን በፍጥነት ጥሩት” አለ። ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ። 20ንጉሡም በግብዣ ሳለ አስቴርን፥ “አስቴር ሆይ! የምትሺው ምንድን ነው? ጠይቂ፤ የምትጠይቂው ሁሉ ይደረግልሻል” አላት። 21አስቴርም መልሳ፥ “ልመናዬና የምሻው ነገር ይህ ነው፤ 22በንጉሡ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ ንጉሡና ሐማ ወደማዘጋጅላቸው ግብዣ ነገ ይምጡ፤ ያንም ነገ አደርገዋለሁ” አለች።
ሐማ መርዶክዮስን ለመስቀል እንዳሰበ
23ሐማም እጅግ ደስ ብሎት ከንጉሡ ዘንድ ወጣ፤ ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስን በአደባባዩ ባየው ጊዜ እጅግ ተቈጣ። 24ሐማ ግን ወደ ቤቱ ሄደ፤ ወዳጆቹንና ሚስቱን ዞሳራን ጠራ። 25ንጉሡም ያደረገለትን ሀብቱንና ክብሩን ሁሉ፥ በግዛቱም ላይ ከፍ ከፍ እንዳደረገው አጫወታቸው። 26ሐማም፥ “ንግሥቲቱ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ከእኔ በቀር ከንጉሡ ጋር ማንንም አልጠራችም፤ ደግሞ ነገ ከንጉሡ ጋር ወደ እርስዋ ተጠርቻለሁ። 27ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ከአየሁ ይህ ሁሉ ለእኔ ምንም ደስ አያሰኘኝም” አለ። 28ሚስቱም ዞሳራና ወዳጆቹም ሁሉ፥ “ቁመቱ አምሳ ክንድ የሆነ ግንድ ይቈረጥ፤ ነገም መርዶክዮስ ይሰቀልበት ዘንድ ለንጉሡ ተናገር፤ ደስ ብሎህም ከንጉሡ ጋር ወደ ግብዣው ግባ” አሉት። ይህም ነገር ሐማን ደስ አሰኘው፤ ግንዱንም አዘጋጀ።