መጽሐፈ አስቴር 4
መርዶክዮስ የአስቴርን ርዳታ እንደ ጠየቀ
1መርዶክዮስም የተደረገውን ሁሉ በዐወቀ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለበሰ፤ በራሱም ላይ ዐመድ ነሰነሰ፤ ወደ ከተማዪቱም መካከል ወጣ። “ያለ በደል ሕዝብን ታጠፋላችሁን?” እያለም ታላቅና የመረረ ጩኸት ጮኸ። 2ማቅም ለብሶ፥ ዐመድ ነስንሶ በንጉሡ በር መግባት አይገባም ነበርና ከንጉሡ በር ደርሶ ቆመ። 3የንጉሡም ትእዛዝና ዐዋጅ በደረሰበት ሀገር ሁሉ በአይሁድ ላይ ታላቅ ኀዘን፥ ልቅሶና ዋይታም ሆነ፤ ብዙዎችም ማቅና ዐመድ ለራሳቸው አነጠፉ። 4የአስቴርም ደንገጥሮችዋና ጃንደረቦችዋ መጥተው ነገሩአት፤ ንግሥቲቱም እጅግ አዘነች፤ ማቁንም ይለውጥ ዘንድ የሚለብሰውን ልብስ ለመርዶክዮስ ላከችለት፤ እርሱ ግን ማቁን አልተውም አለ። 5አስቴርም ያገለግላት ዘንድ ንጉሡ ያቆመውን አክራትዮስን ጠራች፤ እርሱም ከጃንደረቦቹ አንዱ ነበረ፤ እርስዋም ይህ ነገር ምንና ምን እንደ ሆነ ያስታውቃት ዘንድ ወደ መርዶክዮስ እንዲሄድ ላከችው። 6አክራትዮስም በንጉሡ በር ፊት ወደ ነበረችው ወደ ከተማዪቱ አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ወጣ። 7መርዶክዮስም የተደረገውን ሁሉ፥ አይሁድንም ለማጥፋት ሐማ በንጉሡ ግምጃ ቤት ይመዝን ዘንድ የተናገረውን የብሩን ቍጥር ነገረው። 8ለአስቴርም እንዲያሳያት ለመጥፋታቸው በሱሳ የተነገረውን የዐዋጁን ጽሕፈት ቅጅ ሰጠው፤ ወደ ንጉሡም ገብታ ስለ ሕዝብዋ ትለምነውና ትማልደው ዘንድ እንዲነግራት፥ “በእጄ እንዳደግሽ የችግርሽን ጊዜ አስቢ፤ ከንጉሡ በታች የተሾመው ሐማ ይገድሉን ዘንድ አዝዞአልና ወደ ጌታ ወደ እግዚአብሔር ለምኝ፤ ለንጉሡም ነግረሽ ከሞት አድኝን በላት” አለው። 9አክራትዮስም ገብቶ የመርዶክዮስን ቃል ለአስቴር ነገራት። 10አስቴርም አክራትዮስን ተናገረችው፤ ለመርዶክዮስም እንዲህ የሚል መልእክት ሰጠችው። 11“የንጉሡ አገልጋዮችና በሀገሮችም የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን ሳይጠራ ወደ ንጉሡ ወደ ውስጠኛው ወለል የሚገባ ሁሉ በሕይወት ይኖር ዘንድ ንጉሡ የወርቁን ዘንግ ካልዘረጋለት በቀር እርሱ ይሞት ዘንድ ሕግ እንዳለ ያውቃሉ፤ እኔ ግን ወደ ንጉሡ ለመግባት ይህን ሠላሳውን ቀን አልተጠራሁም።” 12አክራትዮስም የአስቴርን ቃል ለመርዶክዮስ ነገረው። 13መርዶክዮስም አክራትዮስን አለው፥ “ሂድና ለአስቴር እንዲህ በላት፦ አንቺ በንጉሥ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ተለይች ብቻዬን እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። 14በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ረድኤትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፤ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” 15አስቴርም እንዲህ ብሎ ለመርዶክዮስ እንዲመልስ አዘዘችው፦ 16“ሂደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ ሰብስብ፤ ለእኔም ጹሙ፤ ሦስት ቀን ሌሊቱንና ቀኑን አትብሉ፤ አትጠጡም፤ እኔና ደንገጥሮች ደግሞ እንዲሁ እንጾማለን፤ ምንም እንኳ ያለ ሕግ ቢሆን ወደ ንጉሡ እገባለሁ፤ ብጠፋም እጠፋለሁ።” 17መርዶክዮስም ሄዶ አስቴር እንዳዘዘችው ሁሉ አደረገ።
የመርዶክዮስ ጸሎት
18እግዚአብሔር ያደረገውን ሁሉ እያሰበ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። 19እንዲህም አለ፥ “አቤቱ! አቤቱ! ሁሉን የምትገዛ፥ በሥልጣንህ ሁሉን የፈጠርህ ንጉሥ! እስራኤልን ታድናቸው ዘንድ ብትወድ የሚከራከርህ የለም፤ 20ሰማይንና ምድርን፥ ከሰማይ በታች ያለ ድንቅ ፍጥረትንም ሁሉ አንተ ፈጥረሃልና፥ 21አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ አቤቱ ለዚህ ትዕቢተኛ ሐማ ያልሰገድሁ በመናቅ እንዳይደለ፥ በትዕቢትም እንዳይደለ፥ ራሴንም ከፍ ከፍ በማድረግ እንዳይደለ አንተ ታውቃለህ። 23የእግዚአብሔርን ክብር የሰው ክብር እንዳላደርግ፥ ከአንተም ከጌታዬ በቀር ለማንም እንዳልሰግድ፥ ይህን ነገር አደረግሁት እንጂ፥ እስራኤልስ የሚድኑ ከሆነ እግሩን እስም ዘንድ በወደድሁ ነበር፤ ይህንም ሥራ በትዕቢት አላደረግሁትም። 25ያጠፉን ዘንድ በጠላትነት ተነሥተውብናልና፥ መጀመሪያ ርስትህንም ያጠፉ ዘንድ ወድደዋልና አሁንም አቤቱ የአብርሃም አምላክ ንጉሥ እግዚአብሔር ሆይ! ወገኖችህን አድን። 26ከግብፅ ሀገር ያዳንኻቸው ርስትህን ቸል አትበል። 27ልመናችንንም ሰምተህ ወገኖችህን ይቅር በል፤ አቤቱ በሕይወት ሳለን ስምህን እናመሰግን ዘንድ ኀዘናችንን ወደ ደስታ መልሰው፤ ተስፋ የሚያደርጉህንም ሰዎች አለኝታቸውን አታጥፋ።” 28በፊታቸው ሞት ደርሶባቸዋልና እስራኤል ሁሉ ጮኹ፤ ቃላቸውንም አሰምተው በኀይላቸው ተናገሩ። 29አስቴርም ሞትን ወደ መፍራት ደርሳለችና ሰውነትዋን ለእግዚአብሔር አደራ ሰጠች። 30የደስታ ልብስዋን አውልቃ የኀዘን ልብስዋን ለበሰች፤ በደስታ ሽቱም ፋንታ በራስዋ ላይ ዐመድና ትቢያን ነሰነሰች። ሰውነትዋንም ፈጽማ አሳዘነች። በፀጕርዋ ሰርሜዶ ፋንታም ትቢያ ጨመረች።
የአስቴር ጸሎት
31ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብላ ለመነች፥ “አቤቱ! ረዳት አንተ ብቻ ነህ፤ ሞት ወደ እኔ ቀርቦአል፤ ረዳት የሌለኝ ብቸኛ የሆንሁ እኔን ርዳኝ። 33አቤቱ! እኔም ከልጅነቴ ጀምሬ ከአባቶች ወገኖች ዘንድ አንተ ከአሕዛብ ሁሉ ለይተህ እስራኤልን ገንዘብ እንዳደረግሃቸው፥ ለዘለዓለሙም ርስት ይሆኑህ ዘንድ አባቶቻችንን ከዘመዶቻቸው ለይተህ እንደተቀበልሃቸው ሰማሁ፤ አሁንም እንደ ተናገርህ ሁሉን አደረግህላቸው። 34በፊትህ በደልን፤ በጠላቶቻችንም እጅ ጣልኸን። የአሕዛብን ጣዖቶች አመስግነናልና። አቤቱ አንተ ጻድቅ ነህ። 36አሁንም እጃቸውን ወደ ጣዖቶቻቸው ያነሡ አሕዛብ በጽኑ አገዛዝ ገዙን እንጂ አልተዉንም። 37በቃልህ የሠራኸውን ሥርዐት ያስወግዱ ዘንድ፥ ርስትህንም ያጠፉ ዘንድ፥ የሚያመሰግኑህንም ሰዎች አፍ ይዘጉ ዘንድ፥ የቤተ መቅደስንም ሥርዐትና መሠዊያህን ያጠፉ ዘንድ፥ 38ለከንቱ ጣዖት ለማድላት የአሕዛብንም አፍ ይከፍቱ ዘንድ፥ ሥጋዊ ንጉሥንም ለዘለዓለሙ ያመሰግኑ ዘንድ በጽኑ አገዛዝ ገዙን። 39ባጸናኸው ሕግ ያሉትን አሳልፈህ አትስጣቸው፤ በመከራችንም አይሳቁብን። ነገር ግን ምክራቸውን በራሳቸው መልስ፤ በእኛም ላይ በጠላትነት የተነሣውን አዋርደው። 40አቤቱ አስበን፤ በመከራችንም ጊዜ ተገለጥልን፤ አለቆችን ሁሉ ያጸናህ የአማልክት ንጉሥ ሆይ! እኔንም አጽናኝ። 41በአንበሳው ፊት በአንደበቴ በጎ ነገርን አድርግ፤ የሚዋጋንንም ይጣላው ዘንድ፥ የእርሱንና ከእርሱ ጋር የሚተባበሩትንም ጥፋት ይናገር ዘንድ ልቡናውን መልሰ። 42እኛን ግን በእጅህ አድነን፤ አቤቱ ከአንተ በቀር ማንም ሌላ ረዳት የሌለኝ ብቸኛ የሆንሁ እኔንም ርዳኝ። አቤቱ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ የኀጢአተኞችን ክብራቸውን እንድጠላ፥ ያልተገረዙትንና የሌሎችን ሁሉ ምንጣፍ እንደምጠላ አንተ መርምረህ ታውቃለህ። 44አንተ መከራዬን ታውቃለህ፤ በከበርሁበትም ወራት የምታይበት በራሴ ላይ ያለ ጌጥ ደስ እንደማያሰኘኝ፥ እንደ ደም ጨርቅም እንደምጸየፈው፥ በምከብርበትና በማርፍበትም ወራት እንደማላጌጥበት አንተ ታውቀዋለህ። 45እኔ ባሪያህ የሐማን ማዕድ አልበላሁም፤ የንጉሡም መጠጥ ደስ አያሰኘኝም፤ ከወይናቸውም አልጠጣሁም። 46አቤቱ! የአብርሃም አምላክ! ከገባሁ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔ ባሪያህ በአንተ እንጂ በእነርሱ ደስ አልተሰኘሁም። 47አቤቱ ሁሉን የምትችል፥ ተስፋ የቈረጡትን ጸሎት ስማ፤ በእኛ ክፉ ነገር ከሚያደርጉ እጅም አድነን፤ እኔንም ከምፈራው አድነኝ።”