ሐማ አይሁድን ለማጥፋት እንደ አስፈቀደ
1ከዚህም ነገር በኋላ ንጉሡ አርጤክስስ የቡጊያዊውን የሐመዳቱን ልጅ ሐማን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከባለሟሎቹም ሁሉ በላይ አስቀመጠው። 2ንጉሡም ስለ እርሱ እንዲሁ አዝዞ ነበርና በንጉሡ በር ያሉት የንጉሡ አገልጋዮች ሁሉ ለሐማ ይሰግዱ ነበር። ነገር ግን መርዶክዮስ ብቻ አይሰግድለትም ነበር። 3በንጉሡም በር ያሉት የንጉሡ አገልጋዮች መርዶክዮስን፥ “የንጉሡን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋለህ?” አሉት። 4ይህንም ዕለት ዕለት ይነግሩት ነበር፤ እርሱ ግን አይሰማቸውም ነበር፤ ለሐማም የንጉሡን ትእዛዝ እንደማይቀበልና መርዶክዮስ አይሁዳዊ እንደ ሆነ ነገሩት። 5ሐማም መርዶክዮስ እንዳልሰገደለት ባየ ጊዜ እጅግ ተቈጣ። 6በአርጤክስስ መንግሥት የነበሩትን የአይሁድን ሕዝብ ሁሉ ያጠፋም ዘንድ ፈለገ። 7ንጉሡ አርጤክስስ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት እንዲህ አደረገ፤ የመርዶክዮስን ወገኖች በአንዲት ቀን ያጠፋቸው ዘንድ በየቀኑና በየወሩ ዕጣ ይጥል ነበር፤ ዕጣውም በአዳር ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ወጣ። 8ሐማም ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ ብሎ ነገረው፥ “አንድ ከዳተኛ ሕዝብ በአሕዛብ መካከል በመንግሥትህ ሀገሮች ሁሉ ተበትነዋል፤ ሕጋቸውም ከሕዝቡ ሁሉ ሕግ የተለየ ነው፤ የንጉሡንም ሕግ አይጠብቁም፤ ንጉሡም ይተዋቸው ዘንድ አይገባውም። 9ንጉሡም ቢፈቅድ እንዲጠፉ ይጻፍ፤ እኔም ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ዐሥር ሺህ መክሊት ብር አገባለሁ።” 10ንጉሡም ቀለበቱን ከእጁ አወለቀ፤ በአይሁድም ላይ የጻፈውን እንዲያትምበት ለሐማ ሰጠው። 11ንጉሡም ሐማን፥ “ብሩ ለአንተ ይሁን፤ ሕዝቡንም እንደ ወደድህ አድርግ” አለው። 12በመጀመሪያውም ወር ከወሩም በዐሥራ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሓፊዎች ተጠሩ፤ ከሕንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ወዳሉ መቶ ሃያ ሰባት ሀገሮች በየሀገሩ ወዳሉ ሹሞችና አለቆች ወደ አሕዛብም ሁሉ ገዢዎች እንደ ቋንቋቸው በንጉሡ በአርጤክስስ ቃል ሐማ እንዳዘዘ ጻፉ። 13በዐሥራ ሁለተኛው ወር በአዳር በዐሥራ ሦስተኛው ቀን የአይሁድን ዘር ሁሉ በአንድ ቀን ያጠፉ ዘንድ፥ ገንዘባቸውንም ይዘርፉ ዘንድ ደብዳቤዎች በመልእክተኞች እጅ ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ሀገሮች ሁሉ ተላኩ።
አይሁድን ለማጥፋት የተላለፈ አዋጅ
14የንጉሡ የአርጤክስስ ደብዳቤዎችም እንዲህ ይላሉ፥ “ከሕንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሃያ ሰባት ሀገሮች ላሉ ለደጃዝማቾችና ለራሶች፥ ለመኳንንትም ትድረስ 15ብዙ አሕዛብን ከገዛሁ በኋላ፥ ሀገሩን ሁሉ ከገዛሁ በኋላ እነዚህን አጥፍቼ፥ ሁሉን አዘጋጅች ለዘለዓለሙ በየዋሀት፥ በጸጥታ እኖር ዘንድ ወደድሁ። መንግሥቴ የተወደደና፥ ጸጥ ያለ እንደ መሆኑ ሁሉን ሠራርቼ ለእኔ የሚታዘዝልኝ ሁሉ ያለ ድንጋጤ ይኖር ዘንድ ነው እንጂ ራሴን ከፍ ከፍ የማደርግ በመንግሥቴ ጽናት አይደለም፤ ደብዳቤዪቱም እስከ ምድር ዳርቻ ትድረስ፤ ከእኔ ዘንድ የሚገኝ፥ በሕዝቡም ዘንድ የሚወደድ ተድላ ደስታን አደርጋለሁ። 16በሚገባ ሁልጊዜ ይህን ማዘጋጀት በምችል ገንዘብ ለአማካሪዎች እሺ ብዬ በልቡናዬ ሳልጸጸት በጎ ነገርን አደርግ ዘንድ መጣሁ። 17ከእኔም በታች ከተሾመ ወደ በጎ ነገር ከመራን፥ ሥርዐቱም ልዩ የሆነ፥ ከአሕዛብም ሁሉ ተለይቶ ለንጉሡ ትእዛዝ ሁልጊዜ የማይታዘዝ፥ ሕጋችንንና ሥርዐታችንንም እንቢ የሚል ሕዝብ በዚህ ዓለም ሁሉ ካሉ አሕዛብ ሁሉ ጋር አንድ እንደ ሆነ ከነገረን ከሐማ በእውነት በሚገባ ተላከ። 18ይህንም ሕዝብ ብቻውን ተለይቶ፥ ሥርዐቱም ከሰው ሥርዐት የተለየ ሆኖ፥ ባዕድም ሆኖና ተለውጦ፥ ከሕጋችንም ወጥቶ አገኘነው። ፈቃዳቸውንም ለመፈጸም ክፉ ሥራ ይሠራሉ፤ መንግሥታችንንም እንደ ኢምንት አደረጓት። 19በሁሉም ላይ በተሾመ፥ ከአባታችን በታች በሆነ በሐማ ደብዳቤዎች ስለጻፍንላችሁ ፈጽማችሁ ሳትራሩላቸው የዚች ዓመት ዐሥራ ሁለተኛው ወር አዳር በባተ በዐሥራ አራተኛው ቀን ሁሉንም በጠላቶቻቸው ሰይፍ ከልጆቻቸውና ከሚስቶቻቸው ጋር ያጠፏቸው ዘንድ እነሆ አዘዝን። 20እንደዚሁም ታናናሹንና ታላላቁን በአንዲት ቀን ወደ መቃብር ታወርዷቸው ዘንድ እነሆ አዘዝን፤ ከዚህም በኋላ ሀገራችን ፈጽማ ከሥራቸው ታርፍ ዘንድ ከእነርሱ የምታስቀሩት አይኑር።” 21በዚያም ቀን ይዘጋጁ ዘንድ የደብዳቤው ቅጅ በየሀገሩ ላሉ አሕዛብ ሁሉ ታወጀ። 22መልእክተኞቹም በንጉሡ ትእዛዝ እየቸኰሉ ሄዱ፤ አዋጁም በሱሳ ከተማ ተነገረ። ንጉሡና ሐማም ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ከተማዪቱ ሱሳ ግን ተደናገጠች።