አስቴር ንግሥት እንደ ሆነች
1ከዚህም ነገር በኋላ የንጉሡ የአርጤክስስ ቍጣ በበረደ ጊዜ ምን እንዳለችውና እንዴት እንደፈረደባት አስታውሶ አስጢንን ረሳት። 2ንጉሡንም የሚያገለገሉ ብላቴኖች እንዲህ አሉት፥ “መልከ መልካም የሆኑ ደናግል ለንጉሡ ይፈለጉለት። 3ንጉሡም በመንግሥቱ ሀገሮች ሁሉ አለቆችንና መሳፍንትን ይሹም፤ መልከ መልካም ደናግል ልጆችንም ይምረጡለት፤ ወደ ሱሳ ከተማ ወደ ሴቶች ቤትም ያምጡአቸው፤ ሴቶችን ለሚጠብቅ ለንጉሡ ጃንደረባም ይስጡአቸው፤ ቅባትና የሚያስፈልጋቸውንም ይስጧቸው። 4ከእነርሱም ንጉሡን ደስ የምታሰኝ ቆንጆ በአስጢን ስፍራ ከእርሱ ጋር ትንገሥ።” ይህም ነገር ንጉሡን ደስ አሰኘው፤ እንዲሁም አደረገ። 5አንድ አይሁዳዊ የቂስ ልጅ የሰሜኢ ልጅ የኢያዕር ልጅ መርዶክዮስ የሚባል ከብንያም ወገን በሱሳ ከተማ ነበረ። 6እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ከማረካቸው ምርኮኞች ወገን ነበረ። 7ያሳደጋትም ልጅ ነበረችው፤ እርስዋም የአጎቱ የአሚናዳብ ልጅ ነበረች፤ ስምዋም አስቴር ይባል ነበር። ከወላጆችዋም በወጣች ጊዜ ልጅ ትሆነው ዘንድ አሳድጎአት ነበር፤ ያችም ልጅ መልከ መልካም ነበረች። 8የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በተሰማ ጊዜ ብዙ ቆነጃጅት ወደ ሱሳ ከተማ ወደ ጋይ እጅ ተሰበሰቡ፤ አስቴርም ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ሴቶች ጠባቂው ወደ ጋይ ተወሰደች። 9ልጅቱም ደስ አሰኘችው፤ በእርሱም ዘንድ ሞገስን አገኘች፤ ቅባቷንም፥ ድርሻዋንም ከንጉሡ ቤት ልታገኝ የሚገባትን ሰባት ደንገጥሮች ፈጥኖ ሰጣት፥ እርስዋንና ደንገጥሮችዋንም በሴቶች ቤት በተመረጠ ስፍራ አኖረ። 10መርዶክዮስ እንዳትናገር አዝዞአት ነበርና አስቴር ሕዝብዋንና ወገንዋን አልተናገረችም። 11መርዶክዮስም የአስቴርን ደኅንነትና የሚሆንላትን ያውቅ ዘንድ ዕለት ዕለት በሴቶች ቤት ወለል ትይዩ ይመላለስ ነበር። 12የመንጻታቸውም ወራት ስድስት ወር ያህል በከርቤ ዘይት፥ ስድስት ወርም በጣፋጭ ሽቱና በልዩ ልዩም በሚያነጻ ነገር ይፈጸም ነበርና እንደ ሴቶች ወግ ዐሥራ ሁለት ወር እንዲሁ ከተደረገላት በኋላ ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ለመግባት የአንዳንዲቱ ቆንጆ ተራ በደረሰ ጊዜ፥ 13በዚህ ወግ ቆንጆዪቱ ወደ ንጉሡ ትገባ ነበር፤ ከሴቶች ቤት ወደ ንጉሡ ቤት ለመውሰድ የምትሻውን ሁሉ ይሰጡአት ነበር። 14ማታም ትገባ ነበር፤ ሲነጋም ተመልሳ ወደ ሁለተኛው የሴቶች ቤት ቁባቶችን ወደሚጠብቅ ወደ ንጉሡ ጃንደረባ ወደ ጋይ ትመጣ ነበር፤ ንጉሡም ያልፈለጋት እንደ ሆነ፥ በስምዋም ያልተጠራች እንደ ሆነ ከዚያ ወዲያ ወደ ንጉሡ አትገባም ነበር። 15ወደ ንጉሡም ትገባ ዘንድ የመርዶክዮስ አጎት የአሚናዳብ ልጅ የአስቴር ተራ በደረሰ ጊዜ የሴቶች ጠባቂ የንጉሡ ጃንደረባ ጋይ ከሚለው በቀር ምንም አልፈለገችም ነበር፤ አስቴርም በሚያዩአት ሁሉ ዐይን ሞገስን አግኝታ ነበር። 16አርጤክስስም በነገሠ በሰባተኛው ዓመት አዳር በሚባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር አስቴር ወደ ንጉሡ ቤት ገባች። 17ንጉሡም ከሴቶች ሁሉ ይልቅ አስቴርን ወደደ፤ በዐይኑም ከደናግል ሁሉ ይልቅ ሞገስንና መወደድን አገኘች፤ የንግሥትነትንም ዘውድ በራስዋ ላይ አደረገ። 18ንጉሡም ለባለሟሎቹና ለአገልጋዮቹ ሁሉ ሰባት ቀን ያህል ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ የአስቴርንም ሰርግ ከፍ አደረገው፤ ለሀገሮቹም ሁሉ ይቅርታ አደረገ።
መርዶክዮስ ንጉሡን ከአሴሩበት እንደ አዳነ
19መርዶክዮስም በንጉሡ በር ያገለግል ነበር። 20አስቴርም እግዚአብሔርን እንድትፈራ ከእርሱ ጋር እንዳደገችበት ጊዜ ታደርግ ዘንድ መርዶክዮስ አዝዞአት ነበርና መርዶክዮስ እንዳዘዛት ወገንዋንና ሕዝብዋን አልተናገረችም። አስቴርም የአኗኗርዋን ሥርዐት አልለወጠችም። 21በዚያም ወራት መርዶክዮስ ከፍ ከፍ ስላለ ደጁን ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱ ተቈጡ፤ ንጉሡን አርጤክስስንም ይገድሉት ዘንድ ፈለጉ። 22ነገሩም ለመርዶክዮስ ተገለጠ፤ እርሱም ለንግሥቲቱ ለአስቴር ነገራት፤ አስቴርም በመርዶክዮስ ስም ለንጉሡ ነገረች። 23ንጉሡም ሁለቱን ባለሟሎቹን በመረመራቸው ጊዜ አመኑ፤ ሰቀላቸውም። ከዚህም በኋላ ንጉሡ ይህን ነገር ስለ መርዶክዮስ ክብር የመንግሥቱ ታሪክ በተጻፈበት መጽሐፍ ይጽፉት ዘንድ አዘዘ።