መጽሐፈ አስቴር 1
የመርዶክዮስ ሕልም
1ታላቁ ንጉሥ አርጤክስስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት በኒሳን መባቻ የኢያዕር የሰሜኢ የቂስ ልጅ ከብንያም የተወለደ አይሁዳዊው መርዶክዮስ ሕልም አየ፤ 2እርሱም በሱሳ ከተማ ይኖር ነበር፤ ታላቅ ሰውም ነበረ፤ በንጉሡ ቤት አደባባይም ያገለግል ነበር። 3እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከይሁዳው ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ከኢየሩሳሌም ከማረካቸው ምርኮኞች አንዱ ነበረ። 4ሕልሙም ይህ ነበረ፦ እነሆ ቃል፥ የምድር መነዋወጥና ሁከት፥ ነጐድጓድም ተሰማ፤ በምድርም ላይ ችኮላ ሆነ። 5እነሆም ለጠብ የተዘጋጁ ሁለት ታላላቅ ዘንዶዎች መጡ፤ ቃላቸውም ታላቅ ሆነ። 6በቃላቸውም አሕዛብ ሁሉ ጻድቃን ሕዝብን ይዋጉ ዘንድ ለሰልፍ ተዘጋጁ። 7እነሆም ጭጋግና ጨለማ፥ ኀዘንና መከራ፥ ጭንቅና ታላቅ ሁከት በምድር ላይ የሚደረግበት ቀን ሆነ፤ 8ጻድቃን ሕዝቦች ሁሉ ክፋታቸውን እየፈሩ ታወኩ። ለጥፋትም ተዘጋጁ፤ 9ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፤ ከጩኸታቸውም የተነሣ ከትንሽ ምንጭ ብዙ ውኃ እንዳለበት እንደ ትልቅ ወንዝ ሆነ፤ 10ብርሃንና ፀሐይ ወጣ፤ የተዋረዱም ሰዎች ከፍ ከፍ አሉ፤ የከበሩ ሰዎችንም አጠፉአቸው። 11መርዶክዮስም ይህን ሕልም እግዚአብሔርም ያደርግ ዘንድ የቈረጠውን ነገር አይቶ ነቃ፤ ይህንም ነገር በልቡ ጠበቀ፤ እስከ ሌሊትም ድረስ በሁሉም አቅጣጫ ያስተውለው ዘንድ ወደደ።
መርዶክዮስ የንጉሡን ሕይወት እንደ አዳነ
12መርዶክዮስም ሀገሩንና አደባባይዋን ከሚጠብቁ ከንጉሡ ባለሟሎች ከሁለቱ ከታራና ከገበታ ጋር በአደባባይ ይቀመጥ ነበረ። 13ያሰቡት ምክራቸውንም ሰማ፤ ንጉሡን አርጤክስስን ይገድሉት ዘንድ ሴራን እንደ አዘጋጁ ዐወቀ፤ ተረዳም፤ ለንጉሡም የእነርሱን ነገር ነገረው። 14ንጉሡም ሁለቱን ባለሟሎቹን መረመራቸው፤ ኀጢአታቸውንም አምነው በሞት ተቀጡ። 15ንጉሡም ይህን ነገር በታሪክ ማስታወሻው ጻፈው፤ መርዶክዮስም ይህን ነገር ጻፈው። 16ንጉሡም መርዶክዮስን በንጉሡ ግቢ ያገለግል ዘንድ አዘዘው፤ ስለዚህም ነገር ድርጎ አወጣለት። 17የአግ ወገን የሆነ የሐመዳቱ ልጅ ሐማ ግን የከበረ ነበረ፤ በንጉሡም ፊት ይቆም ነበር፤ የንጉሡ ባለሟሎች የሆኑ እነዚያ ሰዎች ስለ ሞቱ በወገኖቹና በመርዶክዮስ ክፉ ነገርን ያደርግ ዘንድ ይፈልግ ነበር።
ንግሥት አስጢን የንጉሡን ትእዛዝ እንደ ተላለፈች
18በአርጤክስስም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ ይህም አርጤክስስ ከሕንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሃያ ሰባት ሀገሮች ነገሠ። 19በዚያም ዘመን ንጉሥ አርጤክስስ በሱሳ ከተማ በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳለ፥ 20በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለባለሟሎቹና ለአገልጋዮቹ፥ ለቀሩትም ለፋርስና ለሜዶን ታላላቆች ሁሉ፥ ለሠራዊቱም አለቆች ሁሉ ግብዣ አደረገ። 21ከዚህም በኋላ የከበረውን የመንግሥቱን ሀብት፥ የታላቁንም የግርማዊነቱን ክብር መቶ ሰማንያ ቀን ያህል አሳያቸው። 22የሰርጉም ቀኖች በተፈጸሙ ጊዜ ንጉሡ በከተማ ለተገኙት ሕዝብ ሁሉ በንጉሡ ቤት አደባባይ ስድስት ቀን ግብዣ አደረገ። 23በቤቱም ነጭ፥ አረንጓዴና ሰማያዊ መጋረጃዎች ከጥሩ በፍታና ከሐምራዊ ግምጃ በተሠራ ገመድ በብር ቀለበትና በዕብነ በረድ አዕማድ ላይ ተዘርግተው ነበር፤ አልጋዎቹም ከወርቅና ከብር ተሠርተው በቀይና በነጭ፥ በብጫና በጥቁር ዕብነ በረድ ወለል ላይ ነበሩ። 24የወርቅና የብር ጽዋዎች ነበሩ፤ ዋጋው ሠላሳ ሺህ የሚሆን የከበረ የዕንቍ ጽዋዕም ነበረ። ወይኑም ብዙ ነበር፤ ንጉሡም የሚጠጣው ወይን መዓዛ እጅግ መልካም ነበር። 25በዓሉ ንጉሡ እንደ ፈቀደ ነበረ እንጂ እንደ ቀደመው ወግ አልነበረም። የእርሱንና የሰዎችን ፈቃድ ያደርጉ ዘንድ የቤቱን አዛዦች አዝዞ ነበርና። 26ንግሥቲቱም አስጢን በንጉሡ በአርጤክስስ ቤተ መንግሥት ለሴቶች ግብዣ አደረገች። 27በሰባተኛውም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ ደስ ባለው ጊዜ በፊቱ የሚያገለግሉትን ሰባቱን ጃንደረቦች ሐማን፥ ባዛንን፥ ታራን፥ ባራዚንን፥ ዘቶልታን፥ አባታዛን፥ ታራባን 28ንግሥቲቱ አስጢን መልከ መልካም ነበረችና ውበቷ ለአሕዛብ አለቆች እንዲታይ ዘውድ ጭነው ወደ ንጉሡ ፊት ያመጡአትና ያነግሡአት ዘንድ አዘዛቸው። 29ነገር ግን ንግሥቲቱ አስጢን በጃንደረቦች እጅ በላከው በንጉሡ ትእዛዝ ትመጣ ዘንድ እንቢ አለች፤ ንጉሡም አዝኖ እጅግ ተቈጣ። 30እርሱም አስጢን ያለችውን ለወዳጆቹ ነገራቸው፤ እንግዲህ እንደ ሕጉና እንደ ፍርዱም አድርጉ አላቸው፤ 31በመንግሥቱም ቀዳሚዎች ሆነው የሚቀመጡ የንጉሡ ባለሟሎች የፋርስና የሜዶን መሳፍንት አርቄስዮስ፥ ሰርስትዮስ፥ ሚሊሲአር ወደ እርሱ መጡ፤ 32ንጉሡም በጃንደረቦች እጅ ያዘዘውን ስላላደረገች በንግሥቲቱ በአስጢን ላይ ምን እንደሚያደርጉ እንደ ሕጉ ነገሩት። 33ሜኬዎስም ለንጉሡና ለአለቆቹ እንዲህ አላቸው፥ “ንግሥት አስጢን ንጉሡን ብቻ የበደለች አይደለችም፤ አለቆቹንና የንጉሡን ሹሞች ሁሉ እንጂ።” 34እርሱም ንጉሡን እንቢ እንዳለችው የንግሥቲቱን ቃል ነገራቸው። “ዛሬ ይህች ንጉሡን አርጤክስስን እንሲ ካለችው፦ 35ዛሬም የፋርስና የሜዶን መኳንንት ሚስቶች ንግሥቲቱ ለንጉሡ የመለሰችለትን ሰምተው እነርሱም ደፍረው ባሎቻቸውን ይንቃሉ። 36ንጉሡም ቢፈቅድ ንግሥቲቱ አስጢን ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ፊት ከእንግዲህ ወዲያ እንዳትገባ የንጉሡ ትእዛዝ ከእርሱ ይውጣ፤ እንዳይለወጥም በፋርስና በሜዶን ሕግ ይጻፍ፤ ንጉሡም ንግሥትነቷን ከእርስዋ ለተሻለችው ለሌላዪቱ ሴት ይስጥ። 37ንጉሡም የሠራው ሕግ በመንግሥቱ ሁሉ በሰፊው ይነገር፤ ያንጊዜ ሴቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ባለጸጋም ቢሆን ድሃም ቢሆን ያከብራሉ።” 38ይህም ምክር ንጉሡንና አዛውንቶቹን ደስ አሰኛቸው፤ ንጉሡም እንደ ሜኬዎስ ቃል አደረገ። 39ንጉሡም ሚስቶች ባሎቻቸውን ይፈሩአቸው ዘንድ በመንግሥቱ ወደ አሉ ሀገሮች ሁሉ በዚሁ ቃል ላከ።