1ንጉሡም አርጤክስስ በመንግሥቱ በምድርና በባሕር ላይ ግብር ጣለ። 2የኀይሉና የብርታቱ፥ የሀብቱና የመንግሥቱ ክብር እነሆ በፋርስና በሜዶን ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ለመታሰቢያ ተጻፈ። 3አይሁዳዊውም መርዶክዮስ ለንጉሡ ለአርጤክስስ በማዕረግ ሁለተኛ ነበረ፤ በመንግሥቱም ታላቅ ሰው ነበረ፤ በአይሁድም የከበረ ነበረ፤ በወንድሞችም ዘንድ የተወደደ፥ ለሕዝቡም ሁሉ መልካምን የሚያደርግ ነበረ። 4መርዶክዮስም፥ “ይህ ነገር በእግዚአብሔር ፈቃድ ተደረገ። 5የዚያ ሕልም ጊዜው አላለፈምና ስለዚህ ነገር ያየሁት የሕልሜን ነገር አሰብሁ” አለ። 6ፀሐይና ብርሃን የወጣባት፥ ብዙው ውኃም የተገኘባት ወንዝ የሆነች ያች ትንሿ የውኃ ምንጭ ንጉሥ ያገባት፥ ንግሥትም ያደረጋት አስቴር ናት። 7እነዚያ ሁለቱ ዘንዶዎችም ሐማና እኔ ነን። 8የአይሁድንም ስም ያጠፉ ዘንድ የተሰበሰቡት አሕዛብ ናቸው። 9ወደ እግዚአብሔርም የጮኹ፥ ከመከራውም የዳኑ ወገኖች እስራኤል ናቸው።” እግዚአብሔርም ወገኖቹን ከመከራው አዳናቸው፤ እግዚአብሔርም ከመከራው ሁሉ አዳነን፤ እግዚአብሔርም በሕዝቡ ዘንድ እንደዚህ ያልተደረገ ታላቅ ድንቅና ብዙ ታምራትን አደረገ። 10ስለዚህም ነገር ሁለት ዕጣ አደረገ፤ አንዱ ለእግዚአብሔር ወገኖች ነው፤ ሁለተኛውም ለአሕዛብ ነው፤ 11እነዚያም ሁለት ዕጣዎች በቍርጥ ፍርድ ቀንና ሰዓት በእግዚአብሔር ፈቃድ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ደረሱ። 12እግዚአብሔርም ወገኖቹን አሰባቸው፤ ርስቱንም አነጻ። 13እነዚያም ቀኖች አዳር የተባለው ወር በባተ በዐሥራ አራተኛውና በዐሥራ አምስተኛው ቀን በእግዚአብሔር ፊት በደስታ ተሰብስበው በትውልዳቸው በእስራኤል ዘንድ ለዘለዓለሙ የሚያከብሩአቸው ሆኑ።