1ሁለተኛ ጊዜ ሄኖክ ያየው ራእይ፤ የአዳም ልጅ፥ የሴት ልጅ፥ የሄኖስ ልጅ፥ የቃይናን ልጅ፥ የመላልኤል ልጅ፥ የያሬድ ልጅ ሄኖክ ያየው የጥበብ ራእይ ይህ ነው። 2በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች እናገረው ዘንድ የጀመርሁት የጥበብ ነገር መጀመሪያ ይህ ነው። 3የቀድሞ ሰዎች፥ ስሙ፤ በኋላም የተነሣችሁ ሰዎች፥ በመናፍስት ጌታ ፊት የምናገረው የቅዱሱን ነገር አስተውሉ። 4እነዚህ “መጀመሪያው ይሻላል” ይላሉ፤ እኛም በኋላ የተነሣን ሰዎች የጥበብ መጀመሪያን አንከለክልም። 5እኔ እንዳሰብሁት የዘለዓለም የሕይወት እድል ከእርሱ የተሰጠኝ የመናፍስት ጌታ እንደ ወደደ የያዝሁት ጥበብ ከመናፍስት ጌታ ፊት እስከ ዛሬ ድረስ አልተሰጠኝም ነበር። 6ሦስት ምሳሌዎችም ተገለጡልኝ። 7እኔም በምድር ለሚኖሩ ሰዎች እነግራቸው ጀመር። 8መጀመሪያው ምሳሌ ይህ ነው፥ የጻድቃን ማኅበር በተገለጠ ጊዜ፥ ኃጥኣንም በኀጢአታቸው በተፈረደባቸው ጊዜ፥ ከምድር ፊትም በታወኩ ጊዜ፥ 9በመናፍስት ጌታ ዘንድ ሥራቸው በጸናላቸው በተመረጡ ጻድቃን ፊት ጻድቁ በተገለጠ ጊዜ፥ 10በምድር ላይ ለሚኖሩ ለጻድቃንና ለተመረጡ በተገለጠ ጊዜ፥ 11የኀጢአተኞች ማደሪያ ወዴት ነው? የመናፍስት ጌታን የካዱት ሰዎችስ ማረፊያቸው የት ነው? 12ጥንቱን ባልተወለዱ በተሻላቸው ነበር፤ የጻድቃንም የተሰወሩ ክብሮቻቸው በተገለጡ ጊዜ በኃጥአን ይፈረድባቸዋል፤ ከጻድቃንና ከተመረጡት ሰዎች ፊትም የተነሣ ዝንጉዎች ይታወካሉ። 13ከዛሬም ጀምሮ ምድርን የሚገዟት ሰዎች አዛዦችና ልዑላን አይሆኑም። 14የቅዱሳንንም ፊት ማየት አይችሉም። ለቅዱሳን ጻድቃንና ለተመረጡ ሰዎች ፊት የመናፍስት ጌታ ክብሩ ተገልጧልና። 15ያንጊዜም አዛዦች ነገሥታቱ ይጠፋሉ፥ በጻድቃንና በቅዱሳን እጅም ይሰጣሉ። 16ከዚያ ወዲያ የእነርሱ ሕይወት ተፈጽሞአልና በመናፍስት ጌታ ዘንድ ለእነርሱ የሚያማልድ የለም። 17በዚያም ወራት እንዲህ ይሆናል፥ የተመረጡና ቅዱሳን ልጆች 18በዚያም ወራት ሄኖክ የቅንዐትና የቍጣ መጻሕፍትን፥ የችኮላና የሁከት መጻሕፍትንም ያዘ። 19የመናፍስት ጌታም ምሕረት አይደረግላቸውም አለ። 20በዚያም ጊዜ ደመናና ጥቅል ነፋስ ከምድር ፊት ነጥቆ በሰማያት ዳርቻ አኖረኝ። 21በዚያም ሌላ ራእይ አየሁ፤ የጻድቃንን ማደሪያቸውንና የቅዱሳንን ማረፊያቸውን አየሁ። 22በዚያም ዐይኖቼ ከመላእክት ጋራ ማደሪያቸውን፥ ከቅዱሳንም ጋር ማረፊያቸውን አዩ። 23ስለ ሰው ልጆች ይለምናሉ፥ ይማልዳሉ፥ ይጸልያሉም። 24ጽድቅም በፊታቸው እንደ ውኃ ይፈስሳል፤ ምሕረትም በምድር እንደ ጠል ይሆናል፤ በመካከላቸውም ለዘለዓለሙ እንዲህ ይሆናል። 25በዚያም ወራት ዐይኖቼ በጽድቅና በሃይማኖት የተመረጡ ሰዎችን ቦታ አዩ። 26በዘመናቸውም ጽድቅ ይሆናል፥ ለጻድቃንና ለተመረጡትም ለዘለዓለሙ በእርሱ ፊት ቍጥር የላቸውም። 27ከመናፍስት ጌታ ክንፍ በታችም ማደሪያቸውን አየሁ። 28ጻድቃንና የተመረጡትም ሁሉ በፊቱ እንደ እሳት ብርሃን ያበራሉ። 29አፋቸውም በረከትን ይሞላል፥ ከንፈሮቻቸውም የመናፍስት ጌታን ስም ያመሰግናሉ። 30ጽድቅም በፊቱ አያልቅም፥ ርትዕም በፊቱ አይፈጸምም። 31በዚያም እኖር ዘንድ ወደድሁ፥ ነፍሴም ያን ቦታ ወደደችው። 32በመናፍስት ጌታ ፊት ስለ እኔ እንዲህ ጸንቶአልና ጥንቱን እድል ፋንታዬ በዚያ ሆነ። 33በዚያም ወራት የመናፍስት ጌታን ስም አመሰገንሁ፥ ከፍ ከፍም አደረግሁ፤ የመናፍስት ጌታም በበረከትና በክብር እንደ ወደደ እርሱ አጽንቶኛልና በረከትንና ክብርን ሰጠሁ። 34ቈይቶም ዐይኖቼ ያን ቦታ አዩ። 35እንዲህም እያልሁ አከበርሁት፥ አመሰገንሁትም- “ቡሩክ ነው፥ ከጥንትም ጀምሮ እስከ ዘለዓለሙ ይመስገን። 36በፊቱም ፍጻሜ የለም። 37ዓለም ሳይፈጠር ይህ ዓለም ምን እንደ ሆነ እርሱ ያውቃል፤ ለልጅ ልጅ ዘመን የሚሆነውንም ነገር ያውቃል። 38የማያንቀላፉ ያመሰግኑሃል፥ በጌትነትህም ፊት ይቆማሉ። 39የመናፍስት ጌታ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ነህ፥ ፍጥረትህም 40በዚያም የማያንቀላፉትን ሁሉ በፊቱ ቁመው ሲያመሰግኑ ዐይኖቼ አዩ። 41“አንተ ቡሩክ ነህ፥ የመናፍስት ጌታም ስም ለዘለዓለም ቡሩክ ነው” ይላሉ። 42ማየት እስኪሳነኝም ድረስ ፊቴ ተለወጠ።