1ከዚያም በመድበራ ተራራ መካከል ወደ ምሥራቅ ሄድሁ። 2ምድረ በዳውንም ብቻ አየሁ። 3ነገር ግን ከዚህ ዘር ዛፎችን የተመላ ነው። 4ውኃም ከወደ ላይ ይመነጫል፤ ሻሻቴውም በዝቶ እንደሚንሻሽ በላዩ ይታያል። 5በመስዕ በኩል እንደሚፈስስ ወደ ምዕራብ ይፈስሳል፤ ከአራቱም ማዕዘን ይወጣል፥ ከዚያም ውኃና ጠል አለ። 6ከመድበራም ወደ ሌላ ቦታ ሄጄ ወደዚህ ተራራ ምሥራቅ ቀረብሁ። 7በዚያም የፍርድ እንጨቶችን አየሁ፤ ይልቁንም የነጭ ዕጣንና የከርቤ መዓዛ ያላቸውን ዛፎች አየሁ፥ ዛፎቹም አይመሳሰሉም። 8በእርሱ ላይ፥ በእነርሱም ላይ፥ ሩቅም ባይደለ በምሥራቅ ተራራ ላይ፥ 9የማይገታ ውኃ ያለባቸው የሸለቆዎችን ሌላ ቦታ አየሁ። 10ያማረ ዛፍንም አየሁ፤ ሽታውም እንደ ለውዝ ሽታ ነው። 11በእነዚህ ሸለቆዎች አጠገብም መዓዛ ያለው ሽቱን አየሁ። 12ከእነዚህም በላይ ወደ ምሥራቅ ቀረብሁ፥ በውስጡ ዛፎች ያሉበት ሌላ ተራራንም አየሁ። 13ከእርሱም ስሙ ሰሪራ፥ ከልበኔም እንደሚባል እንደ ነቄጥሮ ያለ ውኃ ይፈስሳል። 14በዚያም ተራራ ላይ ሌላ ተራራን አየሁ፤ በውስጡም ዋግራ የሚባሉ ዛፎች አሉበት። 15እነዚያም ዛፎች እንደ ከርካዕ ምሉኣንና ጽኑዓን ናቸው፤ ይህንም ፍሬ በያዙት ጊዜ ከሽቱ ሁሉ ይበልጣል። 16ከእነዚህም ሽቱዎች በኋላ በተራሮች ላይ ወደ መስዕ ስመለከት፥ 17ያማረ ሽቱን፥ ቀናንሞስና ፕፕሬ የሚባል መዓዛ ያላቸው ዛፎችንም የተመሉ ሰባት ተራራዎችን አየሁ። 18ከዚያም በእነዚያ ተራሮች ራስ ላይ ርቄ ወደ ምሥራቅ ሄድሁ። 19በኤርትራ ባሕርም ሄድሁ፤ ከዚያም የራቅሁ ሆንሁ። 20ዙጡኤል በሚባል መልአክ ላይም አልፌ ሄድሁ፤ ወደ ጽድቅ ገነትም መጣሁ። 21ከእነዚህ ዛፎችም ወዲያ ብዙዎችንና ታላላቆች ዛፎችን በዚያ በቅለው አየሁ። 22ሽታቸውም ያማረ ሲሆን ታላላቆች ነበሩ። ብርሃናቸውም ብዙ ነው፤ እነርሱም ያበራሉ። 23ከእርሱም በልተው ታላቅዋን ጥበብ የሚያውቁበት የጥበብ ዛፍን አየሁ፤ እርሱም ተረርቃሞ ይመስላል። 24ፍሬውም እንደ ወይን ዘለላ እጅግ ያማረ ነው፤ የዚያም ዛፍ ሽታው ሄዶ ከሩቅ ይደርሳል። 25እንዲህም አልሁ- “ይህ ዛፍ መልካም ነው፤ መልኩም ያማረና ደስ የሚያሰኝ ነው።” 26ከእኔ ጋራ ያለው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤልም መለሰልኝ፥ እንዲህም አለኝ- 27“የቀደሙህ ሽማግሌው አባትህና ባልቴቷ እናትህ ከእርሱ የበሉ የጥበብ ዛፍ ይህ ነው። 28ጥብብንም ዐወቋት፤ ዐይኖቻቸውም ተገለጡ፤ ዕራቁታቸውንም እንዳሉ ዐወቁ፤ ከገነትም ተሰደዱ።” 29ከዚያም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሄድሁ፤ በዚያም ታላላቅ አውሬዎችን አየሁ። 30አንዱ ከሌላው ልዩ ነው፤ የወፎችም ፊታቸው ይለያያል፥ መልካቸውም፥ ቃላቸውም አንዱ ከሌላው ይለዋወጣል። 31ከእነዚህ አውሬዎችም በስተምሥራቅ ሰማዩ በላዩ ያረፈበትን የምድር ዳርቻንና የተከፈቱ ደጆችን አየሁ። 32የሰማይ ከዋክብትም እንዴት እንደሚወጡ አየሁ፤ ከእርሱ የሚወጡባቸው ደጃፎችንም ቈጠርሁ። 33የእያንዳንዱን መውጫ ሁሉ በየቍጥራቸው፥ በየስማቸውና በየደረጃቸው፥ በየመኖሪያቸው፥ በየጊዜያቸውና በየወራታቸው ከእኔ ጋር ያለው መልአኩ ዑርኤል እንዳሳየኝ ጻፍሁ። 34ሁሉንም ለእኔ አሳየኝ፥ እርሱም ጻፈው፤ ዳግመኛም ስማቸውን፥ ሥርዐታቸውንና ሥራቸውን ጻፈልኝ። 35ከዚያም በምድር ዳርቻ ወደ መስዕ ሄድሁ፤ በዚያም በምድር ሁሉ ዳርቻ ታላቅና የከበረ ተአምራትን አየሁ። 36በዚያም የተከፈቱ ሦስት የሰማይ ደጃፎችን በሰማይ አየሁ፤ ከእነዚያም በየአንዳንዱ ነፋሳት ይወጣሉ። 37በመስዕ በኩል ነፋስ በነፈሰ ጊዜ ቀቅና በረዶ፥ ውርጭና አመዳይ፥ ጤዛና ዝናምም ይፈስሳል፤ ካንዲቱም መስኮት በበጎ ይነፍሳል። 38በሁለቱ መስኮቶችም በኀይል በነፈሱ ጊዜ በምድር ላይ ጭንቅ ይሆናል። በኀይልም ይነፍሳሉ። 39ከዚያም በምድር ዳርቻ ወደ ምዕራብ ሄድሁ፤ በዚያም በመስኮቶቹ ልክና በመውጫው ልክ በምሥራቅ እንዳየሁ የተከፈቱ ሦስት መስኮቶችን አየሁ። 40ከዚያም በምድር ዳርቻ ወደ አዜብ ሄድሁ። 41በዚያም የተከፈቱ ሦስት የሰማይ መስኮቶችን አየሁ፤ ከዚያም ከአዜብ ዋዕይ ጤዛና ዝናም፥ ነፋስም ይወጣል። 42ከዚያም በሰማይ ዳርቻ ወደ ምሥራቅ ሄድሁ። 43በዚያም በምሥራቅ በኩል የተከፈቱ ሦስት የሰማይ ደጃፎችን አየሁ። 44በእነዚህ በትናንሽ ደጃፎችም በእያንዳንዱ በኩል ታናናሾች የሰማይ ከዋክብት ያልፋሉ። 45በታየችላቸውም ጎዳና ወደ ምዕራብ ይሄዳሉ። 46ይህንም ባየሁ ጊዜ አመሰገንሁ፤ የፍጥረቱንም ገናናነት ለመላእክቱና ለሰዎች ነፍሳት ይገልጥ ዘንድ፥ ሥራውንም ያመሰግኑ ዘንድ፥ ፍጥረቱም ሁሉ የኀይሉን ሥራ ያዩ ዘንድ፥ ታላቅ የሆነ የእጁንም ሥራ ያከብሩ ዘንድ፥ እርሱንም ለዘለዓለሙ ያመሰግኑት ዘንድ ታላላቅና የከበሩ ተአምራትን ያደረገ የክብር ጌታን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ።