1ከዚያም ወደ ሌላ ምድራዊ ቦታ ሄድሁ፤ በቀንና በሌሊት የሚቃጠል የእሳት ተራራንም አሳየኝ። 2በዚያም በኩል ሄድሁ፥ የከበሩ ሰባት ተራሮችንም አየሁ። 3ሁሉም አንዱ ካንዱ ልውጥ ነው፤ የከበሩና ያማሩ ድንጋዮችንም አየሁ፥ ሁሉም የከበረ ነው። 4መልካቸውም የበራ ነው፥ ፊታቸውም ያማረ ነው፥ ሦስቱም በምሥራቅ በኩል ናቸው፥ አንዱም ባንዱ ላይ የጸኑ ናቸው። 5ሦስቱም በሰሜን በኩል ናቸው፤ አንዱም ባንዱ ላይ የጸኑ ናቸው፤ ጥልቆች ቆላዎችም አሉ፥ ጠማሞችም ናቸው፥ አንዲቱም አንዲቱን አትቀርባትም። 6ሰባተኛውም ተራራ በእነዚህ መካከል ነው፥ ቁመታቸው ግን እንደ አትሮንስ ወንበር ሁሉም ይመሳሰላሉ። 7መዓዛ ያላቸው ዛፎችም ይከቡታል፤ በመካከላቸውም አንድ ዛፍ አለ፥ ከእነርሱ አንዱ ስንኳ ለእኔ የሸተተበት ጊዜ ከቶ የለም። 8እንደ እርሱም ያሉ ሌሎች አይሸቱም፤ ከሸቱውም ሁሉ ይልቅ ይሸታል። 9ቅጠሉና አበባው፥ እንጨቱም ለዘለዓለም አይጠወልግም። 10ፍሬውም ያማረ ነው፤ ፍሬው ግን እንደ ዘንባባ ፍሬ ነው። 11ያንጊዜም “ይህ ዛፍ እነሆ፥ ያማረ ነው፥ ለማየትም ያማረ ነው፥ ቅጠሉም መልካም ነው፥ ፍሬውም ለማየት ፈጽሞ የተወደደ ነው” አልሁ። 12ያንጊዜም ከእኔ ጋር ያለው፥ በላያቸውም የተሾመው ከቅዱሳንና ከክቡራን መላእክት አንዱ ሚካኤል መለሰልኝ። 13እንዲህም አለኝ- “ሄኖክ፥ ስለዚህ ዛፍ ሽታ ለምን ትጠይቃለህ? ልታውቅስ ስለምን ትመራመራለህ?” 14ያንጊዜም እኔ ሄኖክ እንዲህ ብዬ መለስሁለት- “ስለ ሁሉ ላውቅ እወዳለሁ፥ ይልቁንም ስለዚህ ዛፍ ላውቅ እወዳለሁ።” 15እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰልኝ- “ይህ ያየኸው፥ ራሱ የጌታን ዙፋን የሚመስለው ረጅም ተራራ፥ ቅዱሱና ታላቁ የዘለዓለም ንጉሥ የክብር ጌታ ምድርን በበጎ ሊጐበኛት በወረደ ጊዜ የሚቀመጥበት ዙፋኑ ነው። 16ይህንም የመልካም መዓዛ ዛፍ ጌታ ሁሉን እስከሚበቀልበት እስከ ታላቁ የፍርድ ጊዜና ለዘለዓለም እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ አንድ ሰው እንኳ ሊነካው ሥልጣን የለውም። 17ይህም ለጻድቃንና ለትሑታን ይሰጣል፤ ከፍሬውም ለተመረጡ ሰዎች ሕይወት ይሰጣል። 18በዘለዓለማዊው ንጉሥ በጌታ ቤት አንጻር በመስዕ በኩል በቅዱስ ቦታ ይተከላል። 19ያንጊዜም ደስ ይላቸዋል፥ ሐሤትንም ያደርጋሉ። 20በየወገናቸውም በቅዱስ ቦታ ሽቱን ያቀርቡለታል፥ አባቶችህ ብዙ ዘመን እንደ ኖሩ እነርሱም በምድር ላይ ብዙ ዘመን ይኖራሉ። 21በዘመናቸውም ኀዘንና መከራ፥ ድካምና መቅሠፍት አይዳስሳቸውም።” 22ለጻድቃን ሰዎች እንደዚህ አዘጋጅትWaልና፥ እንደዚህም ፈጥሮ ይስጧቸው ብሏልና የዘለዓለም ንጉሥ የክብር ጌታን አመሰገንሁት። 23ከዚያም ወደ ምድር መካከል ሄድሁ፥ የተባረከና የለመለመ፥ ከተቈረጠ ዛፍም አቈጥቍጠው የሚኖሩ ቅርንጫፎች የጋረዱት ቦታን አየሁ። 24በዚያም ቅዱስ ተራራን አየሁ፥ ከተራራውም በታች በምሥራቁ በኩል ውኃ አለ፤ የሚፈስሰውም ወደ ሰሜን ነው። 25በምሥራቅም በኩል ከዚህ የሚረዝም ሌላ ተራራን አየሁ። 26በመካከላቸውም ጥልቅ ሸለቆ አለ። ስፋትም የለውም፤ በእርስዋም ውኃ ወደ ተራራው ይፈስሳል። 27በዚህም በሁለተኛው ተራራ ምዕራብ በኩል ከእርሱ የሚያንስ ተራራ አለ። ርዝመትም የለውም፥ በመካከላቸውም በበታቹ ሸለቆ አለ። 28በሦስቱ ተራሮች ዳርቻ በኩልም ጥልቅ የሆኑና የደረቁ ሌሎች ሸለቆዎች አሉ። 29ሸለቆዎች ሁሉ ጥልቆች ናቸው፥ ከጽኑ ዓለት ድንጋይ የተነሣም ስፋት የላቸውም። 30በእነርሱ ላይም ዛፍ ይተከላል፥ ስለ ዓለቱም አደነቅሁ፥ ስለ ሸለቆውም አደነቅሁ፤ እጅግም አደነቅሁ። 31ያንጊዜም እንዲህ አልሁ- “የተባረከችና ሁለመናዋ ዛፎችን የተመላች ይህች ምድር ስለምን ናት? 32ይህችስ በመካከላቸው የተረገመች ሸለቆ ስለምን ናት?” 33ያንጊዜም ከእኔ ጋራ ያለው ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ዑራኤል መለሰልኝ እንዲህም አለኝ- “ይህች የተረገመች ሸለቆ እስከ ዘለዓለሙ ለተረገሙ ናት። 34በአንደበታቸውም በእግዚአብሔር ላይ የማይገባ ነገርን የሚናገሩ ሁሉ በዚያ ቦታ ይሰበሰባሉ። 35ስለ ክብሩም ጭንቅ ነገርን ስለ ተናገሩ በዚያ ይሰበሰባሉ፤ በኋለኛውም ዘመን ፍርዳቸው በዚያ ይሆናል። 36በእውነት የሚሆን የፍርድ ዐይነትም በጻድቃን ፊት ለዘለዓለም በእነርሱ ላይ ይሆናል። 37ምሕረትን የሚያደርጉም- የዘለዓለም ንጉሥ የክብር ጌታን በዘመኑ ሁሉ በዚያ ያመሰግኑታል። 38በተፈረደባቸውም ወራት እንዳደላቸው በቸርነቱ ያመሰግኑታል።” 39እኔም ያንጊዜ የክብር ጌታን አመሰገንሁት፥ ለገናናነቱም እንደሚገባ ተናገርሁለት፥ ስሙንም ጠራሁ።