1የትጉሃን ቅዱሳን መላእክት ስማቸው ይህ ነው። 2ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ዑርኤል በመብረቅና በነጐድጓድ የተሾመ ነው። 3ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ሩፋኤል በሰዎች ነፍሳት ላይ የተሾመ ነው። 4ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ራጉኤል ስለ ዓለምና ስለ ብርሃናት የሚበቀል ነው። 5ለሰው በሚያደርገው በጎነት ላይ ለሕዝቡ ታዛዥ ነውና ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ሚካኤል ነው። 6ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ሠረቃኤል በሰውነታቸው ኀጢአት በሚሠሩ በሰዎች መናፍስት ላይ የተሾመ ነው። 7ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ገብርኤል በእባቦች ላይ፥ በገነትና በኪሩቤልም ላይ የተሾመ ነው። 8የሚሠራ ሥራ እስከሌለበት ቦታ ድረስ ዞርሁ፥ በዚያም የሚያስፈራ ሥራን አየሁ። የተዘጋጀና የሚያስፈራ ምድረ በዳ ነው እንጂ በላይ ጠፈር፥ በታችም መሠረት የለውም። 9በዚያም እንደ ታላላቆችና በእሳት እንደሚቃጠሉ ተራሮች በአንድነት በእርሱ ላይ የተጋዙ ሰባት የሰማይ ከዋክብትን አየሁ። 10ያንጊዜም “በምን ኀጢአታቸው ታስረው ተግዘዋል? በምንስ ኀጢአታቸው በዚህ ወድቀዋል?” አልሁ። 11ከእኔም ጋር ያለውና የሚመራኝ ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ዑርኤል፥ እንዲህ አለኝ- “ሄኖክ፥ ስለምን ትጠይቃለህ? ስለማንስ ልትረዳ ትፈልጋለህ? 12እኒህ የልዑል እግዚአብሔርን ትእዛዝ የተላለፉ መላእክት 13ከዚያም ከዚህ ይልቅ ወደሚያስፈራ ወደ ሌላ ቦታ ሄድሁ። 14በዚያም የሚያስፈራ ሥራን አየሁ፤ በዚያም የሚነድድና የሚንበለበል ታላቅ ቋያ አለ፤ መጋዝም አለበት፥ ወሰኑም እስከ መጨረሻው ውቅያኖስ ነው። 15ወደዚያው የሚያወርዷቸው ታላላቅ የእሳት አዕማድም አሉ፥ መጠኑንና ከፍታውንም ለማየት አልቻልሁም፤ ዐይኑንም ማየት ተሳነኝ። 16ያንጊዜም “ይህ ቦታ እንዴት የሚያስፈራ ነው? ለማየትም ደዌ ነው” አልሁ። 17ያንጊዜም ከእኔ ጋር ያለው ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ዑርኤል መለሰልኝ እንዲህም አለኝ- 18“ሄኖክ፥ እንደዚህ መፍራትህ ምንድን ነው? ስለዚህ ስለሚያሰፈራው ቦታስ፥ በዚህ መከራ ፊት መደንገጥህ ምንድን ነው? 19እንዲህም አለኝ- ይህ ቦታ ለመላእክት የግዞት ቤታቸው ነው፤ በዚያም እስከ ዘለዓለም ድረስ ይጋዛሉ።” 20ከዝያም ወደ ሌላ ቦታ ሄድሁ፤ በምዕራብ ረጅምና ታላቅ ተራራን፥ የጸና ዓለትንም አሳየኝ። 21ባጠገቡም ያማሩ አራት ቦታዎች አሉ፤ በውስጡም ጥልቅና ሰፊ፥ እንደሚያድጥ ልሙጥ ነገርም ፈጽሞ ልሙጥ አለ፤ ለማየትም ጥልቅና ጨለማ ነው። 22ያንጊዜም ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ከእኔ ጋር ያለው ሩፋኤል መለሰልኝ። 23እንዲህም አለኝ- “እኒህ ያማሩ ቦታዎች የሞቱ ሰዎች ነፍሳት ሊሰበሰቡባቸው እነዚህ ለእነርሱ ተፈጠሩላቸው፤ የሰው ልጆች ነፍሳትንም ሁሉ በዚያ ይሰበስባሉ። 24እስከ ፍርዳቸው ቀንና እስከ ቀጠሮአቸው ጊዜ ድረስ እነርሱን የሚያኖሩባቸውን እነዚህን ቦታዎች ሠሩ። 25ይኸውም በእነርሱ ላይ እስከሚሆነው ታላቅ መከራ ድረስ ብዙ ዘመን ነው።” 26የሰዎች ልጆች ነፍሳትንም አየሁ፤ እነርሱም ሙተው ሳሉ ቃላቸው እስከ ሰማይ ይደርሳል፤ ይከስሳልም። 27ያንጊዜም ከእኔ ጋር ያለውን ሩፋኤልን ጠየቅሁት፤ እንዲህም አልሁት- “ቃሉ እስከ ሰማይ የሚደርስና የሚከስ ይኸ ነፍስ የማን ነው?” 28እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ- “ይህ ነፍስ ወንድሙ ቃየል በግፍ ከገደለው ከአቤል የወጣ ነው፤ ዘሩ ከምድር ፊት እስኪጠፋ ድረስ፥ የልጅ ልጁም ከሰው ዘር ተለይቶ እስኪጠፋ ድረስ እርሱን ይከስሳል።” 29ያንጊዜም ስለ እርሱና ስለ ሁሉም ፍርድ ጠየቅሁ፤ “ለምንስ አንዱ ካንዱ ተለየ?” አልሁ። 30እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ- “እነዚህ ሦስቱ የሞቱ ሰዎች ነፍሳትን ይለዩ ዘንድ ተፈጠሩ፥ የጻድቃንም ነፍስ እንደዚህ ተለየ፤ ይህም በላዩ ብርሃን ያለበት የውኃ ምንጭ ነው። 31እንደዚሁም ለኃጥአን በሚሞቱበትና በምድር በሚቀበሩበት ጊዜ ሊኖሩበት ቦታ ተፈጠረላቸው። 32በሕይወተ ሥጋ ሳሉ በእነርሱ ላይ ፍርድ አልተደረገባቸውም። 33እስከ ታላቅዋም የፍርድ ቀን ድረስ በዚች ታላቅ ጭንቅ ላይ በዚያ ቦታ ነፍሶቻቸው ይለያሉ፤ ለሚራገሙም ሰዎች እስከ ዘለዓለም መቅሠፍትና ጭንቅ አለባቸው፤ ለነፍሳቸውም በቀል አለባት። 34በዚያም ምንም እንኳ ከዓለም ጀምሮ ቢሆንም እስከ ዘለዓለሙ አስሮ ያግዛቸዋል፤ 35እንደዚሁም ለሚከስሱና በኃጥኣን ዘመን በተገደሉ ጊዜ ስለ ጥፋት ለሚያመለክቱ ሰዎች ነፍስ ቦታ ተለየ። 36እንደዚሁም ፍጹማን በደለኞች ኃጥአንን እንጂ ጻድቃንን ላልሆኑ ለክፉዎች ሰዎች ነፍስም ቦታ ተፈጠረ፤ ከበደለኞችም ጋር እንደ እነርሱ ይሆናሉ። 37ነፍሳቸው ግን በፍርድ ቀን አትገደልም፤ ከዚህም አይነሡም።” 38ያንጊዜም የክብር ጌታን አመሰገንሁት፤ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ሁሉን የሚችል የክብርና የጽድቅ ጌታዬም የተመሰገነ ነው አልሁ። 39ከዚያም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ በምዕራብ በኩል ወደ ሌላ ቦታ ሄድሁ። 40ሳያርፍ የሚነድና የሚሮጥ እሳትንም አየሁ፤ መቸም መች እንዲሁ ነው እንጂ በሌትና በቀን ከሩጫው አይገታም። 41“ይህ ዕረፍት የሌለው ምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅሁ። 42ያንጊዜም ከእኔ ጋር ያለው ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ራጉኤል መለሰልኝ፥ እንዲህም አለኝ- “ወደ ምዕራብ ሲሮጥ ሩጫውን ያየኸው ይህ የሚነድ እሳት የሰማይ ብርሃን ሁሉ ነው።”