1የረዓይትም ሞት መናፍስት ከሥጋቸው በወጡበት ይሆናል። 2የሚጠፋም ይሁን። 3ፍርድም ሳይደረግ እንዲሁ ይጠፋሉ፤ እስከ ታላቋ የፍጻሜ ዕለት ድረስ ከታላቋ ዓለም ከትጉሃንና ከዝንጉዎች የተነሣ ፍርድ ይፈጸማል። 4አሁንም ስለ እነርሱ ልትለምንላቸው የላኩህን አስቀድሞ በሰማይ የነበሩ ትጉሃንን እንዲህ በላቸው። 5“ዛሬም እናንተ በሰማይ አላችሁ፥ ምሥጢራትም ገና አልተገለጡላችሁም። 6የተናቀ ምሥጢርንም ዐወቃችሁ፥ በልቡናችሁም ጽናት ይህን ለሴቶች ነገራችሁ። 7በዚህም ምሥጢር ሴቶችና ወንዶች በምድር ላይ ክፋትን ያበዛሉ፤ እንግዲህስ ሰላም የላችሁም።” 8እንደ ቋያ የሚቃጠሉ ሰዎች ወዳሉበት አንድ ቦታ ወሰዱኝ፤ በወደዱም ጊዜ እንደ ሰው ይታያሉ። 9ጥቅል ነፋስ ወዳለበት ቦታ፥ ራሱም እስከ ሰማይ ወደሚደርስ ተራራ ወሰዱኝ። 10የሚያበሩ አራት ቦታዎችንም አየሁ፤ በጥልቁም ዳርቻ ነጐድጓድ አለ፤ የእሳት ቀስትና ጐራንጕሪያቸውም፥ የእሳት ሰይፍና መብረቆችም ሁሉ አሉ። 11የሚናገር የሕይወት ውኃና የምዕራብ እሳት እስካለበት ድረስ ወሰዱኝ፤ ይኸውም የፀሐይን መግቢያ ሁሉ የሚይዝ ነው። 12እሳቱ እንደ ውኃ እስከሚፈስስ እስከ እሳት ፈሳሽ ድረስ መጣሁ፤ በምዕራብ ወዳለው ወደ ታላቁም ባሕር ይፈስሳል። 13ታላላቅ ወንዞችንም ሁሉ አየሁ፤ እስከ ታላቁ ጨለማም ድረስ ደረስሁ፥ ሥጋዊ ሁሉ ወደሚመላለስበትም ሄድሁ። 14የክረምት ጭጋጎች ያሉባቸው ተራሮችንም፥ የወንዙም ሁሉ ውኃ የሚፈስበትን አየሁ። 15የምድር ወንዞችን ሁሉ አፋቸውን፥ የጥልቁንም አፍ አየሁ። 16የነፋሶችንም ሁሉ ቦታዎች አየሁ፤ ፍጥረቱንና የምድሩን ሁሉ መሠረቶች በእነርሱ እንዳስጌጠ አየሁ። 17የምድርንም የማዕዘን ድንጋይ አየሁ፤ ምድርንና ጠፈርንም የሚሸከሙ አራቱን ነፋሳት አየሁ። 18የሰማይንም ከፍታ ነፋሳት እንደ ዘረጓት አየሁ። 19እነርሱም በሰማይና በምድር መካከል ይቆማሉ፤ እነርሱም የሰማይ ምሰሶዎች ናቸው። 20ሰማይን የሚመልሷት፥ የፀሐይን ክበብና ከዋክብትን ሁሉ የሚያገቡ ነፋሳትንም አየሁ። 21በምድር ላይ ደመናትን የሚሸከሙ ነፋሳትንም አየሁ። 22የመላእክትንም መንገድ አየሁ፤ በምድር ዳርቻም በላይ ያለ ጠፈርን የሚያጸና አድማስን አየሁ። 23ወደ አዜብ፥ ከከበረ ድንጋይም ይልቅ ወደሚያበሩ ወደ ሰባት ተራሮች ሄድሁ። 24ሦስቱ በምሥራቅ በኩል፥ ሦስቱም በአዜብ በኩል ናቸው። በምሥራቅ በኩል ያለው ግን አንዱ ከቅጥልጣል ዕንቍ ነው፤ አንዱ ከባሕርይ ዕንቍ ነው፤ አንዱም ደምርፅ ከሚባል ዕንቍ ነው፤ በአዜብ በኩል ያለውም ከቀይ ዕንቍ ነው። 25መካከለኛው ግን ፔካ ከሚባል ዕንቍ እንደ ተሠራ እንደ እግዚአብሔር ዙፋን እስከ ሰማይ ይደርሳል። 26አጎበሩም ሰንፔር ከሚባል ዕንቍ ነው፤ በተራራው ሁሉ ያለ የሚነድድ እሳትንም አየሁ። 27በዚያም በታላቅ ምድር መጨረሻ የሚሆን ቦታን አየሁ፤ በዚያም ውኃዎች ይሰበሰባሉ። 28በሰማይ እሳት ምሰሶዎችም ጥልቅ የሆነ የምድር ጕድጓድን አየሁ። 29በውስጣቸውም የሚቃጠሉና የሚወርዱ፥ በላይ በኩልና በታች በኩልም የማይቈጠሩ የሰማይ አዕማድን አየሁ። 30በጕድጓዱም ላይ ቦታን አየሁ፥ ለዚያም ቦታ በላይ ጠፈር በታችም የምድር መሠረት የለውም። 31በላዩም ውኃ የለም፤ ወፎችም የሉበትም፤ ነገር ግን ምድረ በዳ ነው። 32በዚያም እንደሚቃጠሉ ታላላቅ ተራሮች ሰባት ከዋክብትን በሚያስፈራ ሁኔታ አየሁ። 33መልአኩም የሚጠይቀኝ መንፈስ እንደ መሆኑ እንዲህ አለኝ- “ይህ ቦታ የሰማይና የምድር መጨረሻ ነው። 34ይህም- ለሰማይ ከዋክብትና ለሰማይ ሠራዊት፥ በእሳት ላይ ለሚገለባበጡ ከዋክብትም የግዞት ቤት ሆናቸው። 35እነዚህም በጊዜያቸው አልመጡምና ከመውጣታቸው አስቀድሞ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የተላለፉ ናቸው። 36በምሥጢር ዘመንም እስከ ኀጢአታቸው መጨረሻ ድረስ ተቈጥቶ አጋዛቸው።” 37ዑርኤልም እንዲህ አለኝ- “መላእክት 38መንፈሶቻቸውም ብዙ መልክ ሆነው ሰዎችን ያረክሷቸዋል፤ እስከሚፈጸሙባት እስከ ታላቅዋ የፍርድ ቀን ድረስም እንደ አማልክት ለአጋንንት ይሠዉ ዘንድ ሰዎችን ያስትWaቸዋል። 39ሴቶቻቸውም የሰማይ መላእክትን አስተው እንደ ሰላማውያት ሴቶች ይሆናሉ።” 40እኔ ሄኖክ የሁሉን ፍጻሜ ራእይ ብቻዬን አየሁ፤ እኔም እንዳየሁ ከሰዎች ወገን ያየ የለም።