1ከነገር ሁሉ አስቀድሞ ሄኖክ ተሰወረ። 2ከሰው ልጆችም የተሰወረበትንና ያለበትን ቦታ፥ ምን እንደሆነም የሚያውቅ አልነበረም። 3በዘመኑ ሥራው ሁሉ፥ ከቅዱሳንና ከትጉሃን ጋር ነበር። 4እኔም ሄኖክ ታላቁን ጌታ የዓለምን ንጉሥ አመሰግን ጀመር። 5እነሆም ትጉሃን- እኔን ጸሓፊውን ሄኖክን ጠሩኝ። 6እንዲህም አሉኝ- “የጽድቅ ጸሓፊ ሄኖክ፥ ከፍተኛውን ሰማይና ዘለዓለማዊዉን ቅዱስ ቦታ ለተዉ ለሰማይ ትጉሃን ሂድና ንገር፥ 7ከሴቶችም ጋር ጠፉ፤ የሰው ልጆችም እንደሚያደርጉ አደረጉ። 8ለራሳቸውም ሚስቶችን አገቡ፥ በምድርም ላይ ታላቅ ጥፋትን ጠፉ። 9በምድርም ላይ ሰላምና የኀጢአት ስርየት አይሆንላቸውም። 10በልጆቻቸውም ደስ አይላቸውምና፥ የወዳጆቻቸውን ሞት ያያሉ፤ በልጆቻቸውም ጥፋት ጮኸው ያለቅሳሉ። 11ለዘለዓለም ይለምናሉ፥ ምሕረትም፥ ሰላምም አይደረግላቸውም።” 12ሄኖክም ሄዶ አዛዝኤልን አለው- “ሰላም አይደረግልህም። 13ሊያጠፋህ ታላቅ ፍርድ በአንተ ላይ ወጣ። 14ግፍን ስለ አስተማርህ፥ ለሰው ልጆችም ስላሳየኸው የፅርፈት፥ የግፍና የኀጢአት ሥራ ሁሉ ዕረፍትና ልመና፥ ይቅርታም አይደረግልህም።” 15ያንጊዜ ሄጄ ለሁሉም በአንድነት ነገርኋቸው። 16እነርሱም ሁሉ ፈሩ፤ ፍራት፥ መንቀጥቀጥም ያዛቸው። 17የኀጢአት ማስተስረያ እንዲሆናቸው ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሔር የልመናቸውን መታሰቢያ እንዳሳርግላቸው የልመናቸውን መታሰቢያ እጽፍላቸው ዘንድ ለመኑኝ። 18እነርሱ ከዛሬ ጀምረው መነጋገር አይችሉምና፥ ከተፈረደባቸው የበደል ኀፍረት የተነሣም ዐይኖቻቸውን ወደ ሰማይ አቅንተው ለማየት አይችሉምና። 19ያንጊዜም ስለ ሰውነታቸውና ስለ እያንዳንዳቸው ሥራ፥ የኀጢአት ማስተስረያና የዘመን ርዝመት ይሆንላቸው ዘንድ ስለሚለምኑ የልመናቸውንና የምልጃቸውን መታሰቢያ ጻፍሁ። 20ሄጄም በዳን ውኃዎች አጠገብ በዳን ተቀመጥሁ፤ ይህቺውም ከአርሞን ምዕራብ በቀኝ ያለች ናት። 21እስካንጎላችም ድረስ የልመናቸውን መታሰቢያ ተናገርሁ። 22እነሆም፥ ሕልም መጣብኝ፤ ራእዮችም ተገለጡልኝ። 23ለሰማይ ልጆች እነግር ዘንድ፥ እዘልፋቸውም ዘንድ የመቅሠፍት ራእይን አየሁ። 24ነቅቼም ወደ እነርሱ መጣሁ፤ ሁሉም በሊባኖስና በሴንሴር መካከል ባለች በኡብልስያኢል ፊታቸውን ተሸፋፍነው እያለቀሱ ተሰብሰበው ነበር። 25እኔም ተኝቼ ያየሁትን ራእይ ሁሉ በፊታቸው ተናገርሁ። 26እነዚያንም የጽድቅ ቃላት እናገር ዘንድ፥ ለሰማይ ትጉሃንም አስተምር ዘንድ ጀመርሁ። 27ቅዱሱና ገናናው በዚች ራእይ እንዳዘዘ የጽድቅና ከጥንት ጀምሮ የነበሩ የትጉሃን የዘለፋ መጽሐፍ ይህ ነው። 28በሥጋ አንደበትና በመንፈሴ እኔ ዛሬ የምናገረውን ነገር ተኝቼ አየሁ፤ ገናናው አምላክ ይናገሩበት ዘንድ፥ እንደ ፈጠረም በልብ ያስተውሉ ዘንድ ለሰዎች አፍን ሰጠ፤ ያስተውሉም ዘንድ ለሰዎች የዕውቀት ቃልን ሰጠ። 29ለእኔም ፈጠረልኝ፥ ለትጉሃን የሰማይ ልጆችም አስተምራቸው ዘንድ ሰጠኝ። 30እኔ ልመናችሁን ጻፍሁ። 31በራእዬም እንዲህ አሳየኝ፥ በዓለም ዘመን ሁሉ ልመናችሁ አትደረግላችሁምና። 32ፍጽምት ፍርድም በእናንተ ላይ ወጣች፤ አይሆንላችሁምም። 33ከዛሬ ጀምሮ ዓለም ሁሉ እስኪያልፍ ድረስ ወደ ሰማይ አትወጡም። 34በዓለም ዘመን ሁሉ ያስራችሁ ዘንድ በምድር ተነገረ። 35ከዚህም አስቀድሞ የምትወዷቸው የልጆቻችሁን ጥፋት አያችሁ። 36በፊታችሁ በሰይፍ ያልቃሉ እንጂ ጥሪትነታቸው አይኖራችሁም። 37ስለ እናንተና ስለ እነርሱም የለመናችሁት ልመና አይደረግላችሁም። 38እናንተም እያዘናችሁና እያለቀሳችሁ ከጻፍሁላችሁ መጽሐፍ ምንም ቃል አትናገሩም። 39ለእኔም እንዲህ ያለ ራእይ ታየኝ። 40እነሆ፥ ደመናዎች በራእይ ይጠሩኛል፥ ጉምም ይጠራኛል። 41ኮከቦችና መብረቆችም በሩጫ ያስቸኩሉኛል፥ ያስጨንቁኛልም። 42ነፋሶችም በራእይ ያበርሩኛል፥ ያስቸኩሉኛልም። ወደ ላይ ወደ ሰማይም ወሰዱኝ። 43በእብነ በረድ ወደ ተሠራች ግንብ እስክቀርብ ድረስ ገባሁ። 44የእሳትም ላንቃ ይከብባታል፥ እኔንም ያስፈራኝ ጀመረ። 45ወደ እሳቱም ላንቃ ገባሁ፥ በእብነ በረድም ወደ ተሠራው ታላቅ ቤት ቀረብሁ። 46የዚያም ቤት ግድግዳ ከእብነ በረድ እንደ ተሠራ ወለል ነው። 47ምድሩም በረድ ነው፥ ጠፈሩም እንደ ኮከብና መብረቅ ሩጫ ነው። 48በመካከላቸውም እሳታውያን ኪሩቤል አሉ። ሰማያቸውም ውኃ ነው። 49በቅጥሩም ዙሪያ የሚነድ እሳት አለ፥ ደጃፉም በእሳት ይቃጠላል። 50ወደዚያም ቤት ውስጥ ገባሁ፥ እንደ እሳትም ይሞቃል፤ እንደ በረድም ይቀዘቅዛል። 51ምንም ደስታና ሕይወት በውስጡ የለም፤ ፍርሀት ሸፈነኝ፥ እንቅጥቅጥም ያዘኝ፤ እየታወክሁና እየተንቀጠቀጥሁም በግንባሬ ወደቅሁ፥ በራእይም አየሁ። 52እነሆም፥ ከዚህ ቤት የሚበልጥ ሌላ ቤት አለ። 53በፊቴም ደጃፉ ሁሉ የተከፈተ ነው፥ በእሳት ላንቃም የተሠራ ነው። 54ስለ ክብሩና ስለ ገናናነቱ ልነግራችሁ እስከማልችል ድረስ በሁሉም በብርሃንና በክብር፥ በገናናነትም ይበልጣል። 55ወለሉም እሳት ነው፥ በላዩም መብረቅና የኮከቦች መሮጫ አለበት፤ ጠፈሩም የሚነድ እሳት ነው። 56በውስጡም ከፍ ያለ ዙፋንን ፈጽሜ አየሁ። 57መልኩም እንደ ውርጭ ነው፥ ክበቡም እንደሚያበራ ፀሐይ ነው፥ የኪሩቤልም ቃል ይሰማል። 58ከታላቁ ዙፋንም በታች የሚነድ የእሳት ፈሳሾች ይወጣሉ፤ ማየትም አይቻላቸውም። 59የክብር ጌታም በእርሱ ላይ ተቀምጧል፤ መጐናጸፊያውም ከፀሐይ ይልቅ ያበራል፥ ከበረድም ሁሉ ይልቅ ይነጣል። 60ከመላእክትም ማንም ወደ እርሱ መግባት፥ የክቡሩንና የምስጉኑንም ፊት ማየት አይችልም፤ ማንም ሥጋዊ ሰውም ያን እሳት ያይ ዘንድ አይችልም። 61በዙሪያውም የሚነድ እሳት አለ፥ በፊቱም ታላቅ እሳት ይቆማል። 62በዙሪያው ካሉም ወደ እርሱ የሚቀርብ የለም፥ የብዙ ብዙ መላእክትም በፊቱ አሉ። 63እርሱ ግን ልዩ ምክርን አይሻም። 64ወደ እርሱ የሚቀርቡ ቅዱሳንም በቀንና በሌሊት አይርቁም፥ ከእርሱም አይወገዱም። 65እኔም እስከዚህ ድረስ እየተንቀጠቀጥሁ ፊቴን ተከናንቤ ነበርሁ። 66ጌታም በአንደበቱ ጠርቶ “ሄኖክ! ወደዚህ ወደ ቅዱስ ቃሌ ቅረብ” አለኝ። 67አንሥቶም እስከ ደጃፉ ድረስ አቀረበኝ፥ እኔ ግን ፊቴን ደፍቼ ወደታች እመለከት ነበር። 68መለሰልኝ፥ በቃሉም እንዲህ አለኝ- “ጽድቅን የምትጽፍ ጻድቅ ሰው ሄኖክ፥ ስማ፥ አትፍራም። 69ወደዚህ ቅረብ፥ ቃሌንም ስማ፤ ስለ እነርሱ ልትለምንላቸው ለላኩህ ለሰማይ ትጉሃንም ሄደህ እንዲህ በላቸው- 70እናንተ ስለ ሰው ልትለምኑ ይገባችሁ ነበር፤ ሰዎች ግን ስለ እናንተ አይደለም። 71ከፍ ያለውን ሰማይና ለዘለዓለም ቅዱስ የሆነውን ቦታ ስለምን ተዋችሁት? 72ከሴቶችም ጋር ተኛችሁ፥ ከሰው ሴቶች ልጆች ጋርም ረከሳችሁ። 73ለራሳችሁም ሚስቶችን አገባችሁ፤ እንደ ምድር ልጆችም አደረጋችሁ፥ ረዓይት ልጆችንም ወለዳችሁ። 74ለዘለዓለም በሕይወት የምትኖሩ ቅዱሳን መንፈሳውያን እናንተ ግን በሴቶች ረከሳችሁ። 75በሥጋዊ ደም አስወለዳችሁ፥ የሰውን ደምግባትም ተመኛችሁ፥ እነርሱም ሥጋዊና ደማዊ ሥራን እንደሚሠሩ ሠራችሁ። 76እነዚህም የሚሞቱና የሚጠፉ ናቸው፥ ስለዚህም ዘራቸውን በእነርሱ ላይ ይዘሩ ዘንድ፥ ልጆችም ከእነርሱ ይወለዱ ዘንድ ሴቶችን ሰጠኋቸው። 77በምድርም ላይ እንደዚህ ያለ ሥራ ሲሠራ ይኖራል። 78እናንተ ግን ከዚህ አስቀድሞ በልጅ ልጅ ዘመን በማይጠፋ፥ በዘለዓለማዊ ሕይወት ሕያዋን የሆናችሁ መንፈሳውያን ነበራችሁ። 79ስለዚህም ለእናንተ ሴቶችን አላደረግሁላችሁም፥ የመንፈሳውያን ማደሪያቸው በሰማይ ነውና። 80አሁንም ከመንፈስና ከሥጋ 81ማደሪያቸውም በምድር ይሆናል። 82ክፉዎች ነፍሳትም ከሥጋቸው ወጡ፤ መሠረታቸው ከሚሆኑ ከቅዱሳን ትጉሃን ከላይ ተፈጥረዋልና። 83መጀመሪያ መሠረት የነበሩ በምድር ላይ ክፉ መንፈስ ይሆናሉ፤ ክፉ መንፈስም ተብለው ይጠራሉ። 84ለሰማይ መናፍስትም ማደሪያቸው በሰማይ ይሆናል፤ በምድር ለተወለዱ መናፍስትም ማደሪያቸው በምድር ይሆናል። 85ደመናትን የሚገፉ የረዓይት መናፍስትም ይጠፋሉ፤ ይወድቃሉም፥ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ በምድርም ያደቅቃሉ። 86ኀዘንንም ያደርጋሉ፥ የሚበሉትንም እህል ምንም አያገኙም። 87አይጠሙም፥ አይታወቁምም። 88በሰልፍና በጥፋት ወራት ተወልደዋልና እነዚህ ሰዎች በሰዎች ወንዶች ልጆችና በሴቶች ላይ አይነሡም።”