1ያንጊዜም ልዑሉና ገናናው፥ ቅዱሱም ተናገረ፥ ወደ ላሜህ ልጅ ወደ ኖኅም አርሰየላልዩርን ላከው። 2እንዲህም በለው አለው- በእኔ ስም ራስህን ሰውር፤ ምድር ሁሉ ትጠፋለችና የሚመጣውን ፍጻሜ ግለጽለት። 3በምድር ሁሉ ላይ የጥፋት ውኃ ይመጣል፤ በውስጥዋም ያለው ሁሉ ይጠፋል። 4አሁንም እርሱ ይሸሽ ዘንድ፥ ዘሩም በምድር ሁሉ ይኖር ዘንድ አስተምረው።” 5ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን እንዲህ አለው- “አዛዝኤልን እጁንና እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ አግዘው። 6በዱዳኤል ያለች ምድረ በዳዋንም ክፈታት፤ እርሱንም በዚያ በጨለማው ውስጥ ጣለው፤ በላዩም ጠማማና ሻፎ ድንጋዮችን ግጠምበት። 7ጨለማንም አልብሰው፤ በዚያም ለዘለዓለሙ ይኑር፤ ብርሃንንም እንዳያይ፥ በታላቅዋም የፍርድ ቀን ወደ ገሃነም እንዲላክ ፊቱን ሸፍነው። 8መላእክት 9ትጉሃን 10ምድርም ሁላ በአዛዝኤል ሥራ ትምህርት ጠፋች፤ ኀጢአትን ሁሉ በእርሱ ጻፍበት።” 11ገብርኤልንም እግዚአብሔር አለው- “በዘፋኞችና በተናቁ ሰዎች ላይ፥ በአመንዝራ ልጆች ላይም ሂድ፥ የአመንዝራዪቱን ልጆችና የትጉሃንን 12እርስ በርሳቸውም አስወጥተህ ስደዳቸው፤ የዘመን ርዝመት የላቸውምና እነርሱ ራሳቸው በጦርነት ይጠፋፋሉ። 13የዘለዓለም ሕይወትን ሊኖሩ ተስፋ ያደርጋሉና፤ ከእነርሱ እያንዳንዱ አምስት መቶ ዘመንን ሊኖር ተስፋ ያደርጋልና ሁሉም ይለምኑሃል፤ ስለ እነርሱም ለአባቶቻቸው አይሆንላቸውም።” 14ሚካኤልንም እግዚአብሔር አለው- “ሄደህ ለስምያዛ ንገረው፤ በርኵሰታቸው ሁሉ ከእነርሱ ጋር ይጠፉ ዘንድ ከሴቶች ጋር ለተባበሩ ከእርሱ ጋራ ላሉ ለሌሎችም ንገራቸው። 15ልጆቻቸውም ሁሉ በሚዋጉበት ጊዜ፥ የወዳጆቻቸውንም ጥፋት በሚያዩበት ጊዜ እስከ ፍርዳቸው ዕለትና እስከ ፍጻሜያቸው ድረስ፥ የዘለዓለም ፍርድ እስኪፈጸም ድረስ ሰባውን ትውልድ በምድር ኮረብታ በታች እሰራቸው። 16“በዚያም ወራት ከእሳቱ በታች ወደ አለው ቦታ በጭንቅ ይወስዷቸዋል፤ በግዞት ቤትም ለዘለዓለም ይዘጋባቸዋል። 17ያንጊዜም ከእነርሱ ጋር የተባበረ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይቃጠላል፤ ይጠፋልም፤ እስከ ልጅ ልጅ ዘመን መጨረሻ ድረስም ይጋዛሉ። 18ሰዎችን በድለዋቸዋልና የዋዛ ሰዎችን ሁሉና የትጉሃን ልጆችን አጥፋቸው፤ ግፉንም ሁሉ ከገጸ ምድር አጥፋ፤ ክፉ ሥራም ሁሉ ይጥፋ፤ የጽድቅና የርትዕ ተክልም ለዘለዓለም ይገለጣል። 19ሥራውም ሁሉ ለበረከት ይሆናል፤ ጽድቅና ርትዕም ለዘለዓለም በደስታ ይተከላሉ። 20አሁንም ጻድቃን ሁሉ ያመልጣሉ፤ ሺህ ልጆችንም እስኪወልዱ ድረስ ሕያዋን ይሆናሉ። 21የሕፃንነታቸውንና የሽምግልናቸውን ዘመን ሁሉ በሰላም ይፈጽማሉ። 22በእነዚያም ወራቶች ምድር ሁሉ በእውነት ትታረሳለች፤ በመላዋም ዛፎች ይተከሉባታል፤ በረከትንም ትሞላለች። 23የደስታ ዛፎችም ሁሉ በእርሷ ላይ ይተከላሉ፤ ወይኖችም በእርስዋ ላይ ይተከላሉ፤ በእርስዋም ላይ የሚተከለው ወይን፥ በእርስዋም ላይ የሚዘራው ዘር ለጥጋብ ፍሬን ያደርጋል። 24አንዲቱ መስፈሪያ ሺህ መስፈሪያ ታፈራለች፤ አንዲቱ የዘይት መስፈሪያም ዐሥር የዘይት ዐውድማን ትመላለች። 25አንተ ግን ከግፉ ሁሉ፥ ከዐመፅም ሁሉ፥ ከኀጢአትም ሁሉ፥ ከበደልም ሁሉ፥ በምድር ላይም ከሚሠራው ርኵሰት ሁሉ ምድርን አንጻት። 26በምድር ላይም አጥፋቸው፤ የሰው ልጆችም ሁሉ ጻድቃን ይሁኑ፤ አሕዛብም ሁሉ እኔን የሚያመልኩና የሚያመሰግኑ ይሁኑ። 27ሁሉም ለእኔ ይሰግዳሉ፤ ምድርም ከጥፋት ሁሉ፥ ከኀጢአትም ሁሉ፥ ከመቅሠፍትም ሁሉ፥ ከጭንቅም ሁሉ ትነጻለች። 28ለልጅ ልጅ ዘመንና እስከ ዘለዓለም ድረስ በእርሷ የጥፋትን ውኃ አልደግምም። 29“በእነዚያም ወራቶች በሰዎች ልጆች ሥራና ድካም ላይ ወደ ምድር አወርዳቸው ዘንድ በሰማያት ያሉ የበረከት መዛግብትን እከፍታለሁ። 30ሰላምና ርትዕ በአንድነት በዚህ ዓለም ዘመን ሁሉና በልጅ ልጅ ዘመን ሁሉ አንድ ይሆናሉ።”