1የሰው ልጆች ከበዙ በኋላ እንዲህ ሆነ። 2በእነዚያ ወራት መልከ መልካሞችና ደመ ግቡዎች ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። የሰማይ ልጆች መላእክትም 3እርስ በርሳቸውም- “ኑ ለእኛ ከሰው 4አለቃቸው ስማዝያ- “እኔስ ይህ ሥራ ይሠራ ዘንድ ምናልባት አትወድዱ እንደ ሆነ እፈራለሁ። የዚህችም ታላቅ ኀጢኣት ፍዳ ተቀባይ እኔ ብቻ እሆናለሁ” አላቸው። 5“ይችን ምክር እንዳንለውጣት፥ ይችንም ምክር ቁም ነገር እንድናደርጋት ሁላችን መሐላ እንማማል፤ እርስ በርሳችንም እንወጋገዝ” ብለው ሁሉም መለሱለት። 6ያንጊዜም ሁሉም አንድ ሆነው ማሉ፤ እርስ በርሳቸውም በነገሩ ተወጋገዙ፤ ሁሉም ሁለት መቶ ሆኑ። 7አርዲስ ወደሚባል ቦታም ወረዱ፤ ይኸውም የኤርሞን ተራራ ራስ ነው። እርስ በርሳቸው ተወጋግዘው ምለውበታልና የኤርሞን ተራራ ብለው ጠሩት። 8የአለቆቻቸውም ስሞች ይህ ነው፤ አለቃቸው ስማዝያ፥ ዑራኪ፥ በራምኤል፥ ኮከቢኤል፥ ጣምኤል፥ ራሙኤል፥ ዳንኤል፥ ኢዜቂኤል፥ ሱሩቃያል፥ አሣኤል፥ አርማሮስ፥ በጥርኤል፥ አናንኤል፥ ዘቄቤ፥ ሳምሳፒኤል፥ ሰርትኤል፥ ጡሩኤል፥ ዮምያኤል፥ አራዝያል፤ የሁለቱ መቶ መላእክት አለቆች እኒህ ናቸው፤ ሌሎቹም ሁሉ ከእነሱ ጋር ነበሩ። 9ለራሳቸውም ሚስቶችን አገቡ፤ ሁሉም ለየራሱ አንድ አንድዋን መረጠ። 10ወደ እነርሱም ይገቡ ዘንድ ጀመሩ፤ ከእነርሱም ጋር አንድ ሆኑ። 11ሟርትንና ምታት ማሳየትን አስተማሯቸው። ሥር መማስንና ቅጠል መበጠስንም አመለከትWaቸው። 12እነርሱም ፀንሰው ረጃጅሞች ረዓይትን ወለዱ። ቁመታቸው ሦስት ሦስት ሺህ ክንድ ነበር። 13እነዚህም ሰዎች እነርሱን መመገብ እስኪሳናቸው ድረስ ሰው የደከመበትን ሁሉ በሉ። 14ረዓይትም ሰዎችን ይበሏቸው ዘንድ ተመለሱባቸው። 15በወፎችና በአራዊት፥ በሚንቀሳቀሱና በዓሣዎችም ይበድሉ ዘንድ ጀመሩ። 16እርስ በርሳቸውም ሥጋቸውን ተባሉ፤ ከእርሷም ደምን ጠጡ። 17ያንጊዜም ምድር ዐመፀኞችን ከሰሰቻቸው። 18አዛዝዔልም ለሰዎች ሰይፍና ሾተል፥ ጋሻና ጥሩር መሥራትን አስተማራቸው። 19ከእነርሱም በታች ላሉት አምባሮችን፥ ጌጥን፥ ዐይን መኳልንና ቅንድብ መሸለልን፥ ከተመረጠና ከከበረ ከዕንቍም ሁሉ በከበረውና በተመረጠው ዕንቍ ማጌጥን፥ እንሶስላ መሞቅን ሁሉና የዓለሙን ለውጥ አሳያቸው። 20ታላቅ ዝንጋዔና ብዙ ዝሙትም ተደረገ። ሳቱ፤ አመነዘሩም፤ መንገዳቸውም ሁሉ ጠፋ። 21አሚዛራክ ምታት ማሳየትን፥ ሥር መማስን ሁሉ አስተማረ። አርማሮስም ጋኔን መሳብን አስተማረ። 22በራቅኤልም ኮከብ መቍጠርን አስተማረ። 23ኮከብኤልም ምልክት ማሳየትን አስተማረ። 24ጥሞኤልም ኮከብ መቍጠርን አስተማረ። 25አስራድኤልም የጨረቃን አካሄድ አስተማረ። 26በሰዎችም ጥፋት ሰዎች ጮኹ፤ ቃላቸውም ወደ ሰማይ ደረሰ። 27ያንጊዜም ሚካኤልና ገብርኤል፥ ሱርያልና ዑራኤል በሰማይ ሆነው ጐበኙ። 28በምድር ላይ የሚፈስሰውን ብዙ ደምና በምድር ላይ የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አዩ። 29እርስ በርሳቸውም በጩኸታቸው ድምፅ እንዲህ አሉ- “ምድር ብቻዋን እስከ ሰማይ በር ጮኸች። 30አሁንም የሰማይ ቅዱሳን ሆይ፥ የሰዎች ነፍሳት ፍርድን ወደ እግዚአብሔር አግቡልን እያሉ እናንተን ይማጠናሉ። 31ለጌታቸው ለንጉሡም እንዲህ አሉት- የጌቶች ጌታ፥ የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታትም ንጉሥ አንተ ነህና። 32የጌትነትህም ዙፋን ለልጅ ልጅ ዘመን ለዘለዓለም ነው። ስምህም ለልጅ ልጅ ዘመን ቅዱስና ክቡር የተመሰገነም ነው። አንተም ክቡር ምስጉን ነህ። 33ሁሉንም አንተ ፈጠርህ፤ የሁሉም ሥልጣን ከአንተ ጋር ነው፤ ሁሉም በፊትህ ፈጽሞ የተገለጠ ነው። 34አንተም ሁሉን ታያለህ፤ ከአንተም ሊሰወር የሚቻለው የለም። 35“አዛዝኤል በምድር ላይ ግፍን ሁሉ እንደ አስተማረ፥ በሰማያት የሚሠሩትን፥ በዓለም የተሰወሩትን ሁሉ እንደ ገለጠ፥ ያደረገውን እይ። 36“ከእርሱ ጋር በአንድነት ያሉትን ይገዛ ዘንድ አንተ ሥልጣን የሰጠኸው ስማዝያም ምታት ማሳየትን እንደ አመለከተ፥ 37በአንድነትም ወደ ሰው ሴቶች ልጆች እንደ ሄዱ፥ ከእነዚያም ሴቶች ጋር እንደ ተኙ፥ እንደ ረከሱ፥ እኒህንም ኀጢአቶች እንደ ገለጡላቸው፥ 38ሴቶችም ረዓይትን እንደ ወለዱ፥ በዚህም ምድር ሁላ ደምንና ግፍን እንደ ተመላች እይ። 39አሁንም እነሆ፥ የሞቱት ሰዎች ነፍሳት ይጮኻሉ፤ እስከ ሰማይ ደጅም ድረስ ይከስሳሉ። 40ጩኸታቸውም ወጣ። በምድር ላይ ከሚሠራው ዐመፅ ፊትም መውጣት አይችሉም። 41አንተም ሳይሆን ሁሉን ታውቀዋለህ፤ ይህንና የእነርሱንም አንተ ታውቀዋለህ። 42የምትነግረንም ነገር የለም። ስለዚህም ምን እናደርጋቸው ዘንድ ይገባል?”