1ክፉዎችንና ዝንጉዎችን ለማራቅ፥ በመከራ ቀን ይገኙ ዘንድ ያላቸውን ምርጦችንና ጻድቃንን እንደ ባረከ የሚናገረው የሄኖክ ቃለ በረከት፤ 2ሄኖክም ተናገረ፤ እንዲህም አለ- “ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ጻድቅ ሰው ዐይኖቹ ተገልጠው ሳለ- መላእክት ያሳዩኝን በሰማያት ያለ ቅዱስ ራእይ ያይ ነበር። ከእነርሱም ሁሉን ሰማሁ። እኔም የማየውን ዐወቅሁ። 3ለዚህም ትውልድ አይደለም። ነገር ግን ለሚመጣው ለሩቁ ትውልድ ነው። 4ስለ ተመረጡት ተናገርሁ። ስለ እነርሱም በምሳሌ እንዲህ አልሁ። ቅዱሱና ገናናው የዓለም ፈጣሪ ከማደሪያው ይወጣል። 5ከዚያም በደብረ ሲና ተራራ ላይ ይቆማል፤ በሰፈሩ ይታያል፤ በኀይሉም ጽናት ከሰማይ ይገለጣል፤ ሁሉም ይፈራል፤ መላእክትም ይነዋወጣሉ፤ እስከ ምድር ዳርቻም ድረስ ፍርሀትና ታላቅ እንቅጥቅጥ ይይዛቸዋል። ረጃጅሞች ተራሮች ይደነግጣሉ። ረጃጅም ኮረብታዎችም ዝቅ ይላሉ። ከትኩሳቱም የተነሣ እንደ አደሮ ማር ይቀልጣሉ። ምድርም ትሰጥማለች። በምድርም ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል። 6ፍርድ በሁሉም ላይ በጻድቃንም ሁሉ ላይ ይሆናል። 7ለጻድቃን ግን ሰላምን ያደርግላቸዋል፤ የተመረጡትንም ይጠብቃቸዋል፤ ለእነርሱም ይቅርታ ይደረግላቸዋል። 8ሁሉም የአምላክ ገንዘቦች ይሆናሉ። ይከናወናሉ፤ ይባረካሉ፤ የአምላክም ብርሃን ይበራላቸዋል። 9ፍርድን ያደርግላቸው ዘንድ እነሆ፥ ከብዙ ቅዱሳን ጋር ይመጣል፤ ዝንጉዎችንም ያጠፋቸዋል፤ ኃጥኣንና ዝንጉዎች ፈጽመው በእርሱ ላይ ስለ አደረጉት ሁሉ ሥጋዊዉን ሁሉ ይወቅሳል። 10በሰማይ የሚኖሩ ብርሃናት መንገዳቸውን እንዴት እንደማይለውጡ፥ ሁሉም እንደሚወጣና እንደሚገባ፥ ሁሉም በየዘመኑ እንደ ተሠራ፥ ከሥርዐታቸውም እንደማይተላለፉ በሰማይ ያለውን ሥራ ሁሉ ተረዱ። 11ምድርን እይዋት፥ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ በእርሷ ላይ ከሚሠራው ሥራ የተነሣ የሚታይ የአምላክ ሥራው ሁሉ እንደማይለወጥ አስተውሉ። 12በጋውን፥ ክረምቱንም እዩት፤ ምድር ሁሉ ውኃን እንደ ተመላች፥ ደመናውና ጤዛውም፥ ዝናቡም በእርሷ ላይ እንደሚያርፉባት ተመልከቱ። 13ከአረጀው ጀምሮ አዲሱ እስከሚመጣ ድረስ ለሁለትና ለሦስት ዓመት ከሚቈዩትና ከማይረግፉት ከዐሥራ አራት ዛፎች በቀር ዛፎች ሁሉ ደርቀው፥ ቅጠሎቻቸውም ሁሉ ረግፈው እንዴት እንደሚታዩ ተረዱ፤ እዩም። 14ዳግመኛም ፀሐይ በምድር ላይ አስቀድሞ እንደሚጸና የበጋውን ወራት ተረዱ። 15እናንተ ግን ስለ ፀሐይ ዋዕይ ጥላና መጠለያ ትፈልጋላችሁ፤ ምድርም ከሐሩሩ ትኩሳት የተነሣ ትቃጠላለች። 16እናንተ ግን ስለ ዋዕይዋ ምድርንና ድንጋይዋን መርገጥ አትችሉም። 17ዛፎች በቅጠል ልምላሜ እንዴት እንደሚሸፈኑና እንደሚያፈሩ ተረዱ። 18ስለ ሁሉም አስተውሉ፤ ለዘለዓለሙ ሕያው ሆኖ የሚኖር እርሱ እነዚህን ሁሉ እንደ ፈጠረላችሁም ዕወቁ። 19በየዓመቱ የሚሆነው ሥራውም በፊቱ ነው፥ ፍጥረቱም ሁሉ ለእርሱ ይገዛሉ። አይለወጡምም፥ ነገር ግን አምላክ እንደ ሠራው ሁሉ እንዲህ ይደረጋል። 20ባሕሮችና ፈሳሾችም አንድ ሆነው ሥራቸውን እንዴት እንደሚፈጽሙ እዩ። 21እናንተ ግን አልታገሣችሁም፤ የጌታንም ትእዛዝ አላደረጋችሁም። ነገር ግን ተላልፋችሁ በረከሰች አፋችሁ በገናናነቱ ላይ ታላላቅና የጸኑ ቃላትን አማችሁት። እናንተ ልበ ድንጋዮች ሰላም አትሆንላችሁም። 22ስለዚህም እናንተ ዘመናችሁን ትረግማላችሁ፤ የሕይወት ዘመናችሁንም ታጣላችሁ፤ የዘለዓለም መርገምም ይበዛል። ይቅርታም አይሆንላችሁም። 23በዚያም ወራት በዘለዓለም ርግማን ለጻድቃን ሁሉ ሰላማችሁን 24ለተመረጡ ግን ብርሃን፥ ፍቅር፥ 25እነርሱም ምድርን ይወርሷታል። ለእናንተ ለዝንጉዎች ግን ርግማን ይሆንባችኋል። 26ያንጊዜም ለተመረጡት ሰዎች ጥበብ ይሰጣቸዋል፤ እነርሱም ሁሉ በሕይወት ይኖራሉ፤ በመዘንጋትም ቢሆን ወይም በትዕቢት ዳግመኛ አይበድሉም፤ ነገር ግን ጥበብ ያላቸው ለእርሱ ይገዛሉ። 27ዳግመኛም አይበድሉም፤ በሕይወት ዘመናቸውም ሁሉ አይፈረድባቸውም። የሕይወት ዘመናቸውን ቍጥር ይፈጽማሉ እንጂ በመቅሠፍትና በመዓት አይሞቱም። 28ሕይወታቸውም በሰላም ይበዛል። የደስታቸው ዓመታትም በሐሤትና በዘለዓለም ሰላም፥ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ይበዛሉ።