1ከዚህም በኋላ ፈጽመው የበዙ፥ የብዙ ብዙ የሚሆኑ መላእክትን አየሁ፤ በመናፍስት ጌታ ፊት የሚቆሙ መላእክትም ቍጥርና ግምት የላቸውም። 2በመናፍስት ጌታ አራት ክንፎችም ከሚቆሙት የተለዩ ሌሎች አራት ገጻትን አየሁ። 3ስማቸውንም ዐወቅሁ፤ ስማቸውንም የነገረኝ ከእኔ ጋራ የመጣው መልአክ ነው። 4የተሰወረውንም ሁሉ ገለጠልኝ፥ የእነዚያን የአራቱን ገጻት ቃላትም በክብር ጌታ ፊት ሲያመሰግኑ ሰማሁ። 5መጀመሪያውም ቃል የመናፍስት ጌታን ለዘለዓለሙ ያመሰግነዋል። 6ሁለተኛውንም ቃል የተመረጠውንና በመናፍስት ጌታ የታመኑ ምርጦችን ሲያመሰግናቸው ሰማሁ። 7ሦስተኛውንም ቃል በምድር ስለሚኖሩ፥ በመናፍስት ጌታ ስምም ስለሚማልዱ ሰዎች ሲለምንና ሲጸልይ ሰማሁ። 8አራተኛውንም ቃል ሰይጣናትን አስወጥቶ ሲሰዳቸው ሰማሁ። 9በምድር የሚኖሩ ሰዎችንም ያጣሏቸው ዘንድ ወደ መናፍስት ጌታ እንዲገቡ አይተዋቸውም። 10ከዚህም በኋላ ከእኔ ጋራ የሚሄደውን፥ የተሰወረውንም ሁሉ የገለጠልኝን የሰላም መልአክ፥ 11ያየኋቸውና ቃላቸውን የሰማኋቸው፥ የቈጠርኋቸውም እነዚህ አራቱ ገጻት እነማን እንደ ሆኑ ጠየቅሁት። 12እንዲህም አለኝ- “ይህ መጀመሪያው ቃል ይቅር የሚልና ከመዓት የራቀ ቅዱስ ሚካኤል ነው። 13ሁለተኛውም በበሽታው ሁሉ ላይና በሰው ልጆች ቍስል ላይ የተሾመ ቅዱስ ሩፋኤል ነው። 14ሦስተኛውም በሠራዊት ሁሉ ላይ የተሾመ ቅዱስ ገብርኤል ነው። 15አራተኛውም የዘለዓለም ሕይወትን ለሚወርሱ ሰዎች ተስፋ በንስሓ ላይ የተሾመ ፋኑኤል ነው። 16እኒህም አራቱ የልዑል እግዚአብሔር መላእክት ናቸው፤ በዚያም ወራት አራቱን ቃላት ሰማሁ።