1ከዚህም በኋላ የሰማያትን ምሥጢሮች ሁሉ አየሁ። 2መንግሥት እንዴት እንደምትከፈል፥ የሰዎች ሥራም በሚዛን እንደሚመዘን አየሁ። 3በዚያም የተመረጡትን ሰዎች ማደሪያቸውን፥ የጻድቃንንም ማደሪያቸውን አየሁ። 4ዐይኖቼም የመናፍስት ጌታን ስም የካዱ ኃጥአን ሁሉ ከዚያ ሲሰደዱ አዩ። 5ስበውም ያወጧቸዋል፥ ከመናፍስት ጌታ በምትወጣ መቅሠፍትም መቆም የላቸውም። 6በዚያም የመብረቆችንና የነጐድጓድን ምሥጢራት፥ በምድርም ላይ ይነፍሱ ዘንድ እንዴት እንደሚከፈሉ የነፋሳትን ምሥጢራት፥ የደመናና የጠል ምሥጢራትንም አየሁ። 7በዚያም ቦታ የሚወጡበትን አየሁ፥ ከዚያም የምድር ትቢያን ይጠግባሉ። 8በዚያም የተዘጉ መዛግብትን አየሁ፤ ከእነዚያም ነፋሳት ይከፈላሉ። 9የበረድን መዝገብና የጉምን መዝገብ፥ የደመናዎችንም መዝገብ አየሁ፤ ደመናውም ከጥንት ጀምሮ ከምድር በላይ ይኖራል። 10የፀሐይና የጨረቃ መዛግብትንም ከየት እንደሚወጡና ወዴት እንደሚገቡ አየሁ፤ አመላለሳቸውም ብሩህ ነው። 11አንዱም ከሌላው እንደሚከብር አየሁ፥ አካሄዳቸውም የከበረ ነው። ቀን አያሳልፉም፥ ከመሄዳቸውም አይጨምሩም፥ አያጐድሉምም። 12ጸንተው በሚኖሩበት ሥርዐትም አንዱ ከሌላው ጋር ሃይማኖታቸውን ይጠብቃሉ። 13ፀሐይ ከሁሉ አስቀድሞ ይወጣል፤ በመናፍስት ጌታ ትእዛዝም ጎዳናውን ያደርጋል፤ ስሙም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል። 14ከዚህም በኋላ የተሰወረና የተገለጠ የጨረቃን ጎዳና አየሁ፥ የጎዳናውንም መሄጃ በዚያ ቦታ በሌሊትና በቀን ይጨርሳል። 15በመናፍስት ጌታ ፊትም አንዱ ሁለተኛውን ያየዋል። 16ለእነርሱ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው ነውና ያመሰግናሉ፥ ያከብራሉም፤ አያርፉምም፥ ለሚያበራ ፀሐይ ለበረከትና ለመርገም ብዙ መለዋወጥ አለውና። 17የጨረቃ ጎዳና መመላለሻም የብርሃንና የጨለማ ማእከልን በፈጠረ በመናፍስት ጌታ ስም ለጻድቃን ብርሃን ነው፤ ለኃጥአን ግን ጨለማ ነው። 18ለሰውም ዕውቀትን አደለ፥ በጽድቁም ስም የጻድቃንን ዕውቀት አጸና። 19አለቃው አይከለክልም፥ ንጉሡም መከልከል አይችልም፥ ሁሉን የሚመረምር ፈራጅ አለና፤ እነዚህንም ሁሉ እርሱ በፊቱ ይገዛል።