1ጥበብ የምታድርበትን ቦታ አላገኘችም፤ ማደሪያዋም በሰማያት አለ። 2ጥበብ በሰው ልጆች ታድር ዘንድ ወጣች፤ ማደሪያንም አላገኘችም፤ ጥበብም ወደ ቦታዋ ተመለሰች፤ በመላእክትም መካከል አደረች። 3ዐመፃ ከመዛግብትWa ወጣች፤ ያልወደደችውን አገኘች፤ ዝናም በምድረ በዳ፥ ጠልም በተጠማች ምድር እንደሚያድር በእነርሱ አደረች። 4ሌሎች መብረቆችንና የሰማይ ከዋክብትንም አየሁ። 5ሁሉንም በየስማቸው እንደሚጠራቸው፥ እነርሱም እንደሚሰሙት አየሁ። 6በብርሃናቸውና በቦታቸው ስፋት ይመዘኑ ዘንድ የጽድቅ ሚዛኖችንም አየሁ። 7የፍጥረታቸውንና የመመለሻቸውንም ቀን አየሁ፤ መብረቅ መብረቅን ይወልዳል። አመላለሳቸውም በመልአኮቻቸው ቍጥር ነው፤ ሃይማኖታቸውንም እርስ በርሳቸው ይጠብቃሉ። 8ከእኔ ጋራ የሚሄደውንና የተሰወረውን የገለጠልኝን መልአክ ጠየቅሁት። እንዲህም አልሁት- “እነዚያ ምንድን ናቸው?” 9እርሱም እንዲህ አለኝ- “የመናፍስት ጌታ የእነርሱን ምሳሌ አሳየህ። እነዚህም በምድር ላይ የሚኖሩ፥ በመናፍስት ጌታም ስም ለዘለዓለሙ የሚያምኑ የጻድቃን ስሞች ናቸው። 10ስለ መብረቅም ሌሎችን አየሁ፤ ከከዋክብት እንዴት እንደሚጸኑና መብረቅን እንደሚሆኑ አየሁ። ከእነርሱም ጋር 11ይህም ሁለተኛው ምሳሌ የቅዱሳን ማደሪያንና የመናፍስት ጌታን ስም በሚክዱ ላይ ነው። 12ወደ ሰማይም አይወጡም፤ ወደ ምድርም አይወርዱም፤ የመናፍስትን ጌታ ስም የሚክዱ፥ ለድካምና ለመከራ ቀንም እንደዚህ የሚጠበቁ የኃጥኣን ዕድል እንዲህ ይሆናል፤ በዚያችም ቀን የተመረጠው በጌትነቱ ዙፋን ይቀመጣል። 13ሥራቸውንና ቦታቸውንም ይመርጣል፤ ቍጥርም የላቸውም። 14እኔ የመረጥሁትን፥ ቅዱስና ክቡር ስሙን የሚማጠኑትንም 15በዚያችም ቀን እኔ የመረጥሁትን በመካከላቸው አኖረዋለሁ። 16ሰማይን እለውጣታለሁ፥ ለዘለዓለምም ለበረከትና ለብርሃን አደርጋታለሁ። ምድርንም እለውጣታለሁ፤ ለበረከትም አደርጋታለሁ። 17የመረጥኋቸውንም በውስጧ አኖራቸዋለሁ። ኀጢአትንና በደልን የሚሠሩ ግን አይረግጧትም፤ እኔ ጻድቃንን አይቻቸዋለሁና፤ ሰላምንም አጥግቤአቸዋለሁና፥ በፊቴም አኖርኋቸው። 18ከገጸ ምድር አጠፋቸው ዘንድ የኃጥኣን ፍርድ ወደ እኔ ቀረበች። 19በዚያም ብሉየ መዋዕልነት ያለውን አየሁ፥ ራሱም እንደ ባዘቶ ነጭ ነው። 20መልኩ እንደ ሰው መልክ የሆነ ሌላም ከእርሱ ጋር አለ። ጸጋንም የተመላ ነው፤ ፊቱም ከቅዱሳን መላእክት እንደ አንዱ ነው። 21ከእኔ ጋራ የሚሄደውንና የተሰወረውን ሁሉ የገለጠልኝ ከቅዱሳን መላእክት አንዱን ስለዚሁ የሰው ልጅ ጠየቅሁት። 22እንዲህም አልሁት- “ያ ማን ነው? እርሱስ ከወዴት ይሆን? ከብሉየ መዋዕልስ ጋር ስለምን ይኖራል?” 23እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ- “ጽድቅ የሆነለት፥ ጽድቅም ከእርሱ ጋር የኖረ የሰው ልጅ ነው። ጌታ እርሱን መርጧልና እርሱ የተሰወሩ መዛግብትን ሁሉ ይከፍታል። 24ዕድሉ በመናፍስት ጌታ ፊት ለዘለዓለም በርትዕ ሁሉን ድል ያደረገ ነው። 25“ይህም ያየኸው የሰው ልጅ ነገሥታቱንና ኀያላኑን ከአልጋዎቻቸው፥ ጽኑዓኑንም ከዙፋኖቻቸው ያስነሣቸዋል። 26የጽኑዓኑንም ልጓሞች ይፈታል፥ የኃጥአንንም ጥርሶች ይሰብራል፤ ከፍ ከፍ አያደርጉትምና፥ አያመሰግኑትምምና፥ መንግሥትም ከየት እንደ ተሰጠቻቸው አያምኑምና ነገሥታትን ከዙፋናቸውና ከመንግሥታቸው ይገለብጣቸዋል። 27የጽኑዓኑንም ፊት ይገለብጣል፤ ኀፍረትንም ይመላባቸዋል፥ ማደርያቸውም ጨለማን ይሆንባቸዋል። 28ትሎችም ምንጣፍ ይሆኗቸዋል፤ የመናፍስትን ጌታ ስም ከፍ ከፍ አያደርጉምና ከመኝታቸው ይነሡ ዘንድ ተስፋ አያደርጉም። 29እነርሱም የሰማይ ከዋክብትን የሚገዙ ሆነዋል፤ እጆቻቸውንም ወደ ልዑል ይዘረጋሉ፥ በምድር ይሄዳሉ፥ በውስጧም ይኖራሉ። 30ዐመፅ ሥራቸውንም ሁሉ ይገልጣሉ፤ ሥራቸውም ሁሉ ዐመፅ ነው፥ ኀይላቸውም በባለጸግነታቸው ላይ ነው። 31ሃይማኖታቸውም በእጃቸው ለሠሯቸው ጣዖታት ሆኗል፥ የመናፍስትን ጌታ ስምም ክደዋል። 32ከእርሱና በመናፍስት ጌታ ስም ከሚያምኑ ምእመናን ማደሪያዎችም ይሰደዳሉ። 33“በዚያም ወራት የጻድቃን ጸሎት ከምድር ዐረገች፥ የጻድቁም ደም በመናፍስት ጌታ ፊት ተወደደ። 34በእነዚህም ወራቶች በሰማያት የሚኖሩ ቅዱሳን አንድ ይሆናሉ፤ በአንድ ቃልም ይማልዳሉ፥ ይጸልያሉም፥ ያመሰግናሉም። 35ስለ ፈሰሰውም የጻድቃን ደም በመናፍስት ጌታ ስም ያመስግናሉ፥ ይባርካሉም። 36የጻድቃንም ጸሎታቸው ለዘለዓለም ፍርድ ይደረግላቸው ዘንድ፥ መዘግየትም ለዘለዓለም እንዳይሆንባቸው በመናፍስት ጌታ ፊት አትቋረጥም።” 37በእነዚያም ወራቶች ብሉየ መዋዕልን በጌትነቱ ዙፋን ተቀምጦ አየሁት፤ የሕያዋን መጻፎቻቸውም በፊቱ ተገለጡ። 38በሰማያት የሚኖሩ ሠራዊትም ሁሉ በዙሪያው ሆነው በፊቱ ይቆማሉ። 39የቅዱሳን ልብ ደስታን ትሞላለች፤ የጽድቅ ቍጥሯ ሞልትWaልና፥ የጻድቃንም ጸሎት ተሰምትWaልና። 40የጻድቁም ደም በመናፍስት ጌት ፊት ተወደደ።