1በዚያ ቦታ የማይቈጠር የጽድቅ ምንጭን አየሁ። 2በዙሪያውም ብዙ የጥበብ ምንጮች ይከቡታል። የተጠሙ ሰዎችም ሁሉ ከእርሱ ይጠጣሉ፥ ጥበብንም ይሞላሉ። 3ማደሪያቸውም ከጻድቃን፥ ከተመረጡትና ከቅዱሳን ጋር ነው። 4በዚያችም ሰዓት ያ የሰው ልጅ በመናፍስት ጌታ ፊት ተጠራ። 5ስሙም ከዕለታት መጀመሪያ የቀደመ ነው። 6ፀሐይ፥ ምልክትም 7እንዳይወድቁም እርሱን ይመረጐዙ ዘንድ ለጻድቃንና ለቅዱሳን በትር ይሆናል። እርሱም የአሕዛብ ብርሃን ነው፤ በልቡናቸው ላዘኑም እርሱ ተስፋ ይሆናል። 8በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ በፊቱ ወድቀው ይሰግዳሉ፤ ያመሰግኑታል፥ ያከብሩታልም፥ ለመናፍስት ጌታ ስምም ያዘምራሉ። 9ስለዚህም አስታራቂ ሆነን፤ ይህም በመናፍስት ጌታ ፊት ከጥንት ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ የተሰወረ ሆነ። 10እርሱንም የመናፍስት ጌታ ጥበቡ ለጻድቃንና ለተመረጡት ገለጠው። የጻድቃንን ዕድል ፋንታ ጠብቋልና፤ 11ይህን የዐመፅ ዓለም ጠልተው ንቀውታልና፤ ሥራውንና መንገዱንም በመናፍስት ጌታ ስም ጠልተውታልና። 12በስሙ ይድናሉና፤ ድኅነታቸውንም ወደደ። 13በዚያም ወራት በጭንቀታቸውና በመከራቸው ቀን የምድርን ነገሥታትና ምድርን የያዙ ኀያላን ሰውነታቸውን አላዳኑምና ስለ እጃቸው ሥራ አንገታቸውን የደፉ ሆኑ። 14በመረጥኋቸውም ሰዎች እጅ ይጥሏቸዋል። 15ሣር በእሳት እንደሚቃጠል፥ እርሳስም በውኃ ውስጥ እንደሚሰጥም እንዲሁ ከጻድቃን ፊት የተነሣ ይቃጠላሉ፤ ከቅዱሳንም የተነሣ ይሰጥማሉ። 16ፍለጋቸውም አይገኝም፥ በተጨነቁባትም ቀን በምድር ላይ ፍርሀት ትደረጋለች። 17በፊቱም ይወድቃሉ፥ አይነሡምም፤ እጁንም ሰጥቶ የሚያነሣቸው የለም፤ የመናፍስት ጌታን፥ መሲሑንም ክደውታልና፥ የመናፍስት ጌታም ስሙ ይመሰገናል። 18ጥበብ እንደ ውኃ ፈስሶአልና፤ ክብርም በፊቱ ለዘለዓለም አትፈጸምም፤ በጽድቅ ምሥጢር ሁሉ ኀያል ነውና። 19አስታራቂው በመናፍስት ጌታ ፊት ቁሟልና፥ ዐመፅ እንደ ጥላ ያልፋል፥ መቆምያም ቦታ የለም። 20ጌትነቱ ለዘለዓለም ነው፥ ኀይሉም ለልጅ ልጅ ዘመን ነው። 21የጥበብ መንፈስ፥ የማስተዋል መንፈስ፥ የትምህርትና የኀይል መንፈስ፥ በጽድቅ የሞቱትን ሰዎች በእውነት የሚያስነሣቸው መንፈስም በእርሱ ይኖራል። 22እርሱም የተሰወሩትን ይፈርዳል፥ ከንቱ ነገርንም በፊቱ መናገር የሚችል የለም፤ እርሱ እንደ ወደደ በመናፍስት ጌታ ፊት አስታራቂ ነውና። 23በእነዚያም ወራቶች ለቅዱሳንና ለተመረጡት መመለስ ትደረግላቸዋለች፤ የዘመን ብርሃንም በእነርሱ ያድራል፥ ፍጹም ክብርም ለቅዱሳን ይመለስላቸዋል። 24በጭንቅ ቀንም ለኃጥአን መከራ ትደልብላቸዋለች፤ ጻድቃንም በመናፍስት ጌታ ስም ድል ይነሣሉ። 25ንስሓ ይገቡ ዘንድ፥ የእጃቸውንም ሥራ ይተዉ ዘንድ ለሌሎች ይገልጣል። 26በመናፍስት ጌታ ፊትም ክብር ይደረግላቸዋል፥ በስሙም ይድናሉ። 27ቸርነቱ ብዙ ነውና፥ በፍርዱና በጌትነቱም ፊት ጻድቅ ነውና የመናፍስት ጌታ ይቅር ይላቸዋል። 28ዐመፅም በፍርዱ ጊዜ አትጸናም፥ ንስሓ የማይገባም በፊቱ ይጠፋል፥ “ከእንግዲህ ወዲያም የመናፍስት ጌታ ይቅር አልላቸውም” አለ። 29በእነዚያም ወራቶች ምድር አደራዋን ትመልሳለች፤ መቃብርም የተቀበለችውን አደራ ትመልሳለች። 30ሞትም የሚከፍለውን ይመልሳል፥ እነርሱም ይድኑ ዘንድ ቀንዋ ቀርባለችና ጻድቃንንና ቅዱሳንን ከእነርሱ ይመርጣል። 31አስታራቂውም በእነዚያ ወራቶች በዙፋኑ ይቀመጣል፤ የጥበብንም ምሥጢር ሁሉ ከአንደበቱ ያወጣል፤ የመናፍስት ጌታ ሰጥቶ አክብሮታልና። 32በእነዚያም ወራቶች ተራሮች እንደ ጊደሮች ይዘፍናሉ፤ ኮረብቶችም ወተት እንደ ጠገቡ ጠቦቶች ይዘላሉ። 33በእነዚያም ወራቶች አስታራቂው ተነሥትWaልና ሁሉም በሰማይ እንደ መላእክት ይሆናሉ። ፊታቸውም በደስታ ይበራል። 34ምድርም ደስ ይላታል፥ ጻድቃንም በእርሷ ይኖራሉ፥ የተመረጡትም በእርሷ እየተመላለሱ ይኖራሉ።