1ከእነዚያም ወራቶች በኋላ የተሰወሩትን ራእዮች ሁሉ ባየሁበት በዚያ ቦታ በነፋስ ሠረገላ ተነጥቄ ነበርና፥ ወደ ምዕራብም ወስደውኝ ነበርና፥ 2በዚያ በምድር ላይ ይደረግ ዘንድ ያለውን የሰማይ ምሥጢር ሁሉ ዐይኖቼ አዩ። 3የብረት ተራራንና የናስ ተራራን፥ የብር ተራራንና የወርቅ ተራራን፥ የዕይር ተራራንና የርሳስ ተራራን አዩ። 4ከእኔም ጋር የሚሄደውን መልአክ “በስውር የማያቸው እኒህ ምንድን ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት። 5እርሱም እንዲህ አለኝ- “እኒህ ያየሃቸው ሁሉ ያዝዝ ዘንድ፥ በምድርም ላይ ኀያል ይሆን ዘንድ ለመሲሑ ሥልጣን ይሆናሉ።” 6ያም የሰላም መልአክ እንዲህ ሲል መለሰልኝ- “ጥቂት ቈይ፥ ታያለህም፥ የመናፍስት ጌታ ያጸናው፥ የተሰወረውም ሁሉ ይገለጥልሃል። 7ያየሃቸው እነዚህ ተራሮችም የብረቱ ተራራና የናሱ ተራራ፥ የብሩ ተራራና የወርቁ ተራራ፥ የዕይሩ ተራራና የርሳሱም ተራራ፥ እነዚህ ሁሉ በአስታራቂው ፊት በእሳት ፊት እንዳለ አደሮማር ይሆናሉ። 8ከላይ በእነዚያ ተራሮች ላይ እንደሚወርድ ውኃም ይሆናሉ። ከእግሩም በታች ደካሞች ይሆናሉ። 9“በእነዚያም ወራቶች እንደዚህ ይሆናል፥ በወርቅም ቢሆን በብርም ቢሆን አይድኑም፥ ማምለጥና መሸሽም አይቻላቸውም። 10ብረትም ለጠብ አይሆንም፥ ልብስም ለደረት ጥሩር አይሆንም፥ ብረትም አይረባም፥ ቅልቅልም አይጠቅምም፥ አይቈጠርምም፥ ርሳስም አይወደድም፥ ነገር ግን እኒህ ሁሉ ይካዳሉ። 11አስታራቂውም በመናፍስት ጌታ ፊት በተገለጠ ጊዜ ከምድር ፊት ይጠፉ ዘንድ አላቸው።” 12በዚያም ዐይኖቼ ጥልቅ ሸለቆን አዩ፥ አፉም የተከፈተ ነው። 13በየብስና በባሕር፥ በደሴቶችም የሚኖሩ ሁሉ እጅ መንሻ፥ ገጸ በረከትና ግብርን ያመጡለታል፤ ይህም ጥልቅ ሸለቆ አይመላም። 14እጆቻቸውም በደልን ያደርጋሉ፥ ኃጥአንም ለበደል የሚደክሙበትን ሁሉ ይበላሉ፤ 15ከመናፍስት ጌታ ፊትም የተነሣ ኃጥአን ይጠፋሉ፤ ኃጥአንም በምድሩ ፊት ይቆማሉ። 16ለዘለዓለሙ አያልቁም፥ የመቅሠፍት መላእክትን ሄደው ለሰይጣን ዙሃውን ሁሉ ሲያዘጋጁ አይቻቸዋለሁና። 17ከእኔም ጋር የሚሄደውን የሰላም መልአክ ጠየቅሁት፥ እንዲህም አልሁት- “እነዚህን ዙሃዎችን ለማን ያዘጋጃሉ?” 18እርሱም አለኝ- “በእነርሱ ይጠፉ ዘንድ፥ ለዚህ ዓለም ነገሥታትና ኀያላን እነዚህን ያዘጋጃሉ። 19ከዚህም በኋላ እውነተኛው አስታራቂ በመሰብሰቢያው ቤት ይገለጣል። 20ከእንግዲህ ወዲያም በመናፍስት ጌታ ስም አይከለከሉም። 21ተራሮች ሁሉ በፊቱ እንደ ምድር ይሆናሉ፤ ኮረብቶችም እንደ ውኃ ምንጭ ይሆናሉ፤ ጻድቃንም ከኃጥአን ድካም ያርፋሉ።” 22ተመልሼም ሌላ ገጸ ምድር አየሁ፥ በዚያም እሳት ሲነድ ጥልቅ ሸለቆን አየሁ። 23ነገሥታቱንና ኀያላኑንም አምጥተው በዚያ ጥልቅ ሸለቆ ውስጥ ጣሏቸው። 24በዚያም ዐይኖቼ ዙሃዎችን ሚዛን የሌላቸው የብረት ማሠሪያዎችን አድርገው ሲሠሯቸው አዩ። 25ከእኔም ጋር የሚሄደውን የሰላም መልአክ “እነዚህ የዙሃዎች ማሠሪያዎች ለማን ይዘጋጃሉ?” ብዬ ጠየቅሁት። 26እርሱም እንዲህ አለኝ- “ተቀብለው ከገሃነም በታች ይጥሏቸው ዘንድ እነዚህ ለአዛዝኤል ሠራዊት ይዘጋጃሉ። 27የመናፍስት ጌታም እንዳዘዘ በፊታቸው ጠማማ ድንጋዮችን ይገጥሙባቸዋል። 28ሚካኤልና ገብርኤል፥ ሩፋኤልና ፋኑኤል እነርሱ በዚያች በታላቅዋ ቀን ያጠኑባቸዋል። 29በዚያም ቀን የሰይጣን መልእክተኞች ስለሆኑ፥ በምድር ላይ የሚኖሩትንም ስላሳትWaቸው በዐመፃቸው የመናፍስት ጌታ ከእነርሱ በቀልን ይመልስ ዘንድ እሳት ወደሚነድድበት ምድጃ ይጥሏቸዋል። 30“በዚያም ወራት የመናፍስት ጌታ መቅሠፍት ይወጣል። 31ከሰማያት በላይ ያሉ የውኃዎች መዛግብት ሁሉ፥ ከሰማያት በታችና፥ ከምድር በላይ ያሉ ምንጮችም ይከፈታሉ። 32ውኆችም ሁሉ ከሰማያት በላይ ካሉ ውኃዎች ጋር ይጨመራሉ። 33ከሰማያት በላይ ያለ ውኃ ግን ተባዕታይ ነው፥ ከምድር በታች ያለችው ውኃም አንስታይ ናት። 34በምድር ላይ የሚኖሩና ከሰማይ ዳርቻ በታች የሚኖሩ ሁሉ ይደመሰሳሉ። 35ስለዚህም በምድር ላይ የሠሯትን ኀጢአታቸውን ዐወቋት፤ ስለዚህም ይጠፋሉ።”