1ከዚህም በኋላ ብሉየ መዋዕል አዘነ፥ እንዲህም አለ- “በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ በከንቱ አጠፋኋቸው፤” 2ከእንግዲህም ወዲያ በምድር ላይ በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እንዲህ እንደማያደርግ በገናና ስሙ ማለ። 3እንዲህም አለ- “በሰማይ ምልክት አደርጋለሁ፥ ይህም በእነርሱና በእኔ መካከል በምድር ላይ የሰማይን ዘመን ያህል እስከ ዘለዓለም መተማመኛ ይሆናል። 4ከዚህም በኋላ በመላእክት እጅ አጸናባቸው ዘንድ ብወድ በትእዛዜ ነው። 5በችግርና በመከራ ቀን ከዚህ አስቀድሞ መዓቴም፥ መቅሠፍቴም ያድርባቸዋል። 6የመናፍስት ጌታ እግዚአብሔርም በምድር የምትኖሩ ኀይለኞች ነገሥታት! እኔ የመረጥሁትን በጌትነቱ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ ታዩት ዘንድ አላችሁ አለ። 7እርሱም በአዛዝኤልና በማኅበሩ ሁሉ፥ በሠራዊቱም ሁሉ ላይ በመናፍስት ጌታ ስም ይፈርዳል።” 8በዚያም የመቅሠፍት መላእክትን ሠራዊት ሲሄዱ አየሁ፤ የብረትና የብርት ወጥመዶችንም ይዘዋል። 9ከእኔም ጋር የሚሄደውን የሰላም መልአክ “ወጥመዶችን የያዙ እነዚህ ማንን ሊያሥሩ ይሄዳሉ?” ብዬ ጠየቅሁት። 10እርሱም እንዲህ አለኝ- “በሸለቆው ጥልቅ ዋሻ ውስጥ ይወድቁ ዘንድ እያንዳንዳቸው ለመረጡአቸውና ለወደዱአቸው ናቸው። 11ያንጊዜም ያ ሸለቆ ከመረጧቸውና ከወደዷቸው የተነሣ ይሞላል። 12የሕይወትም ቀናቸው ያልቃል፥ የስሕተታቸውም ቀን ከዛሬ በኋላ አይቈጠርም። 13“በእነዚያም ወራቶች አለቆች ተሰብስበው ወደ ጳርቴና ወደ ሜድ ሰዎች ወደ ምሥራቅ ራሳቸውን ይመልሳሉ። 14ነገሥታቱንም ያነቃንቋቸዋል፥ የሁከት መንፈስም ያድርባቸዋል፥ ከዙፋናቸውም ይገለብጧቸዋል። 15እንደ አንበሶች ከመደባቸው፥ እንደ ተራቡ ጅቦችም ከመንጋዎቻቸው መካከል ይወጣሉ። 16“ይዘምታሉ፥ የምርጦቻቸውንም ሀገር ይረግጣሉ፤ የእርሱ ምርጦች ሀገርም በፊታቸው መመላለሻና መገሥገሻ ትሆናለች። 17የጻድቃኔ ከተማ ግን ለፈረሶቻቸው መሰናክል ትሆናለች። 18እርስ በርሳቸውም ጦርነትን ያነሣሉ፤ ቀኝ እጃቸውም በእነርሱ ላይ ትጸናለች፥ ሰውም ባልንጀራውን፥ ወንድሙንም አያውቀውም። 19ልጅም ከሞታቸው የተነሣ ሬሣቸው እስኪቈጠር ድረስ አባቱንና እናቱን አያውቅም። መቅሠፍታቸውም ከንቱ አይሆንም። 20በእነዚያም ወራቶች መቃብር አፏን ትከፍታለች። 21በውስጧም ይቀበራሉ፤ ታጠፋቸዋለችም፥ ከተመረጡት ፊት የተነሣም ሲኦል ትውጣቸዋለች።” 22ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፥ ሰዎች ተቀምጠውባቸው ሌሎች ብዙዎች ሠረገላዎችን አየሁ። 23በነፋሳትም ላይ ሆነው ከምሥራቅና ከምዕራብ እስከ ቀን እኩሌታ ይመጣሉ። 24የሠረገሎቻቸው ድምፅ ቃልም ተሰማ፥ ይህም ሁከት በተደረገ ጊዜ ቅዱሳን በሰማይ ሁነው ዐወቁ። 25የምድር ምሰሶም ከቦታው ተናወጠ። 26ከሰማይ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ባንዲት ቀን ተሰማ። 27ሁሉም ወድቀው ለመናፍስት ጌታ ይሰግዳሉ። 28የሁለተኛውም ምሳሌ መጨረሻ ይህ ነው። 29ስለ ጻድቃንና ስለ ተመረጡት ሦስተኛውን ምሳሌ እናገር ዘንድ ጀመርሁ። 30እናንተ ጻድቃንና የተመረጣችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ ዕድላችሁ ክቡር ነውና። 31ጻድቃን በፀሐይ ብርሃን፥ የተመረጡትም በዘለዓለማዊ የሕይወት ብርሃን ይሆናሉ። 32ለሕይወታቸው ዘመንም ፍጻሜ የለውም፥ ለቅዱሳንም የዘመን ቍጥር የላቸውም። 33ብርሃንንም ይፈልጉታል፥ በመናፍስት ጌታም ዘንድ ጽድቅን ያገኛሉ። 34በመናፍስት ጌታም ዘንድ ለጻድቃን ሰላም ይሆናል። 35ከዚህም በኋላ የሃይማኖት ዕድል ፋንታ የሆነውን የጽድቅ ምሥጢር በሰማይ ይፈልጉ ዘንድ ለጻድቃን ይነገራል። 36እንደ ፀሐይ በምድር ላይ ወጥትWaልና፥ ጨለማም አልፎአልና፤ የማይቈጠር ብርሃንም ይሆናል። 37አስቀድሞ ጨለማ አልፎአልና በዘመን ቍጥር አይገቡም። 38ብርሃንም በመናፍስት ጌታ ፊት ይጸናል፤ የእውነተኛ ፍርድ ብርሃንም በመናፍስት ጌታ ፊት ለዘለዓለም ትጸናለች። 39በእነዚያም ወራቶች ዐይኖቼ የመባርቅትንና የብርሃናትን ምሥጢራት፥ ፍርዳቸውንም አዩ። 40የመናፍስት ጌታም እንደ ወደደ ለበረከትና ለመርገም ያበራሉ። 41በዚያም የነጐድጓድ ምሥጢርን አየሁ፤ በሰማይ ላይም ብልጭ ባለ ጊዜ ቃላቸው ይሰማል። 42የየብሱንም ቦታዎች አሳየኝ። 43የነጐድጓዱም ቃል ለሰላምና ለበረከት ነው፤ ለመርገም ቢሆንም በመናፍስት ጌታ ቃል ነው። 44ከዚህም በኋላ የብርሃናትና የመባርቅት ምሥጢሮች ሁሉ ተገለጡልኝ። 45ለበረከትና ለጥጋብም ያበራሉ።