1ሄኖክ ከተሰወረ በኋላ በአምስት መቶ ዓመት፥ በሰባተኛውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ከሰማያት በላይ ያለች ሰማይ ታላቅ ንውጥውጥታን እንደምትነዋወጥ፥ የልዑልም ሠራዊት እንደሚነዋወጡ በዚያ ምሳሌ አየሁ። 2ብዙ፥ የብዙ ብዙ መላእክትም ታላቅ ሁከትን ታወኩ። 3ያንጊዜም ብሉየ መዋዕልን በጌትነቱ ዙፋን ተቀምጦ አየሁ። 4መላእክትና ጻድቃንም በዙሪያው ቆመው አየሁ፤ እኔንም ጽኑ እንቅጥቅጥ ፈጽሞ ያዘኝ። 5ፍርሀትም ያዘኝ፥ ወገቤም ጐበጠ፤ ተለያየም፤ ሁለመናዬም እንደ ሰም ቀለጠ፤ በግንባሬም ወደቅሁ። 6ቅዱስ ሚካኤልም ከቅዱሳን መላእክት አንዱን ሌላ መልአክ ልኮ አነሣኝ። 7ባነሣኝም ጊዜ ነፍሴ ተመለሰች፤ ያን ተአምራትና ያንም ሁከት፥ የሰማይንም መነዋወጥ ከማየት የተነሣ መታገሥን አልቻልሁምና። 8ቅዱስ ሚካኤልም እንዲህ አለኝ- “ምን ራእይ ስላየህ እንደዚህ ታወክህ?” 9የምሕረቱ ቀንም እስከ ዛሬ አለች፤ መሓሪውም አለ፤ በምድር በሚኖሩ ላይም መዓቱ የራቀ ነው። 10የመናፍስት ጌታ ለእውነተኛ ፍርዱ ለሚሰግዱ፥ እውነተኛ ፍርዱንም ለሚክዱ፥ ስሙንም በከንቱ ለሚያነሡ ያዘጋጃት፥ የኀይል፥ የመቅሠፍትና የፍርድ ቀን በምትመጣበት ጊዜ፥ 11ያች ቀን ለተመረጡት የቃል ኪዳን፥ ለኃጥኣንም የምርመራ ቀን ሆና ተዘጋጅታለች።” 12በዚያችም ቀን ሁለቱ አንበሬዎች ይለያያሉ፤ ሌዋታን የምትባለው አንስታይ አንበሪ ከውኃዎች ምንጮች በላይ በባሕሩ ጥልቅ ትኖር ዘንድ ትለያለች። 13የማይታየውን ምድረ በዳ በደረቱ የሚይዝ፥ ስሙ ብሔሞት የሚባለው ተባዕት አንበሪም ይለያል። 14የቦታውም ስም ጻድቃንና የተመረጡት በሚኖሩበት፥ የመናፍስት ጌታ ለፈጠራቸው ሰዎች መጀመሪያቸው ከሆነው ከአዳም ሰባተኛ የሆነ አያቴ በተወሰደበት በገነት ምሥራቅ ያለ ዴንዳይን ይባላል። 15እኔም ባንዲት ቀን እንዴት እንደ ተለዩ፥ አንዱ በባሕሩ ጥልቅ፥ አንዱም በምድረ በዳ እንዴት እንደሚኖሩ የእነዚያን አንበሬዎች ኀይላቸውን ይገልጥልኝ ዘንድ ያን ሁለተኛውን መልአክ ጠየቅሁት። 16እርሱም አለኝ- “አንተ የሰው ልጅ፥ የተሰወረን ነገር በዚህ ልታውቅ ትወዳለህ?” 17ከእኔ ጋር የሚሄደው፥ የተሰወረውን የፊተኛውንና የኋለኛውን፥ በላይ በሰማይ፥ በምድርም በጥልቁ፥ በሰማይ ዳርቻና በሰማይ መሠረትም፥ በነፋሳትም መዛግብት ያለውን የገለጠልኝ ሁለተኛው መልአክ፥ 18ነፋሳት እንዴት እንደሚከፈሉና እንደሚመዘኑ፥ ምንጮችና ነፋሳትም በመንፈስ ኀይል እንደሚከፈሉ፥ የጨረቃም የብርሃኑ ኀይል፥ የእውነት ሥራ እንደ መሆኑ፥ የከዋክብትም ክፍሎች በየስማቸው እንደሚከፈሉ ንገረኝ። 19ክፍሉም ሁሉ ይከፈላል፤ ነጐድጐዶችም በመውደቂያቸው ይሰማሉ፤ ለሚከፈለው ክፍል ሁሉ መጠን አለው። 20መብረቁ ይበራ ዘንድ፥ ሠራዊታቸውም ፈጥነው ይሰሙ ዘንድ ለነጐድጓድ ማረፊያ አለውና በትዕግሥት ለቃሉ ተሰጠው። 21ነጐድጓድና መብረቅ አይለያዩም፤ እያንዳንዳቸውም ሁለቱ በነፋስ ይሄዳሉ። 22መብረቅ ብልጭ ባለ ጊዜ ነጐድጓድ ቃሉን ይሰጣልና አይለያዩም፤ ነፋሱም ወዲያውኑ ያርፋል። 23በመካከላቸውም እኩል ይከፍላል፤ የሚወጡበት ቅፅበት እንደ አሸዋ ነውና። 24ከእነርሱም እያንዳንዳቸው ወዲያውኑ በልጓም ይገታሉ። 25በነፋስም ኀይል ይመላለሳሉ፤ እንደ ምድር ዳርቻዎች ብዛትም እንዲሁ ይነዳሉ። 26የባሕሩም መንፈስ 27እንዲህም ትነዳለች፤ በምድር ተራሮችም ሁሉ ትበተናለች። 28የውርጩም ነፋስ የእርሱ መልአክ ነው፤ የበረዱም ነፋስ ቸር መልአክ ነው። 29የአመዳዩ ነፋስም ስለ ብርታቱ ቆመ፤ ለብቻውም መልአክ አለው። 30ከእርሱም የሚወጣው እንደ ጢስ ያለ ነው፥ ስሙም ደደክ ይባላል። 31የጉም ነፋስም ከእነርሱ ጋር በመዛግብታቸው አይተባበርም፤ ነገር ግን አካሄዱ በጌትነት፥ በብርሃንና በጨለማ፥ በክረምትና በበጋ ነውና ለብቻው መዝገብ አለው። 32የእርሷም ቦታ 33ከዝናም መዛግብትም ጋር አንድ ነው፤ መሄጃውም በክረምትና በበጋ ነው። 34ደመናውም ከጉም ደመና ጋር አንድ ነው፤ አንዱ መግቦ ለሌላዉ ይሰጣል። 35የዝናሙ ነፋስ ከመዝገቡ በሚናወጥ ጊዜ መላእክት ይወጣሉ፤ መዝገቡንም ከፍተው ያወጡታል። 36በምድር ሁሉ ላይ ዝናሙ በሚበተን ጊዜ በምድር ላይ ካለው ውኃ ሁሉ ጋር አንድ ይሆናል። 37ዝናሙም በየጊዜው ሁሉ በምድር ላይ ካለው ውኃ ጋራ በሚተባበርበት ጊዜ ውኃዎች በምድር ለሚኖሩ ሰዎች ለጥቅም ናቸው፤ ከሰማይ ከልዑል ዘንድ ለምድር ምግቧ ናቸውና። ስለዚህም ለዝናሙ መጠን አለው፤ መላእክትም ይቀበሉታል። 38እነዚህንም ሁሉ እስከ ጻድቃን ገነት ድረስ አየሁ። 39ከእኔም ጋር የሚኖረው የሰላም መልአክ እንዲህ አለኝ- “እነዚህ ሁለቱ አንበሬዎች በታላቋ የእግዚአብሔር ቀን 40የመናፍስት ጌታ መቅሠፍት በእነርሱ ላይ ባረፈች ጊዜ ልጆች ከእናቶቻቸውና ከአባቶቻቸው ጋር ይገደላሉ። 41የመናፍስት ጌታ መቅሠፍቱም በከንቱ እንዳትመጣ በቸርነቱና በትዕግሥቱ ኋላ በእነርሱ ላይ ፍርድ ትሆናለች።